በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ አስተባብሮ ባደረገው እልህ አስቸጋሪ ሙግት፣ የመጀመሪያውን ሙሌት ለማጠናቀቅ አስችሎታል፡፡ ሙግቱ በከፍተኛ ጫና ወደ ፊት የሚቀጥል ቢሆንምና መንገጫገጭም ሊኖር ቢችልም፣ ከአሁን ወዲያ የህዳሴን ግድብ ከኢትዮጵያውያን ሌላ ሊያስቆመው የሚችል ኃይል የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን“ ብለው እንደተነሱ አሁንም የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ከፍለው የታሪክ አሻራ ያሳርፋሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተባብረው ይሄንን ግድብ ለመሥራት የፈለጉበትን ምክንያት በሁለት ምክንያቶች ማጠቃለል ይቻላል፡፡ አንደኛው፣ ግብፅ ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጃ ዓባይን እንዳትነኪ የሚለው ለኢትዮጵያውያን እንደ ሉዓላዊነት መደፈር አድርገው ስለቆጠሩትና ከአባቶቻቸው የወረሱት ለጠላት አልነኬ ባይነትን ስላንገበገባቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የልማት ጥማት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ምዕት ዓመት ሲቀበሉ “ድህነት ይብቃ፣ ካደጉት አገሮች ተርታ ለመሰለፍ፣ የልማት ጉዞ እንጀምራለን፣ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ይጀመራል“ ብለው የተነሱትን እውን ለማድረግ ይሄንን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ሥራ ጀመሩ፡፡ እንደዚህ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ያስፈለገበት ምክንያቱ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ፣ ከዓለም 12ኛ በመሆኗና ሕዝቦቿንም ከድህነት በፍጥነት ለማውጣትና ሥራ ፈትነትን ለመቀነስ፣ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ዓይነተኛ መፍትሔ በመሆናቸው ነው፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በግዙፍነቱ በዓለም ላይ ካሉ ከአሥሩ አንዱ የሚሆን ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ6,000 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ግድቡም 246 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው የውኃ መያዣ ሐይቅ ይፈጥራል፡፡ የግድቡ መገንባት የሚሰጠውን ጥቅም ከማየታችን በፊት፣ በዚሁ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የተገነባው የግብፅ ትልቁ አስዋን ግድብ እየሰጠ ያለውን ጥቅም እንመልከት፡፡ የአስዋን ግድብ ከኢትዮጵያው ህዳሴ ግድብ የሚያነስ ሲሆን፣ ቁመቱ 111 ሜትር፣ ርዝመቱ 3,830 ሜትር፣ ስፋት 980 ሜትር ሲሆን፣ ግድብ በ12ቱ ተርባይን አማካይነት፣ 2,100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል፡፡ በተጨማሪም ግድቡ 132 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ የሚይዝ ናስር የሚባል ሐይቅ ፈጥሯል፡፡ ግድቡ እ.ኤ.አ. በ1967 ሥራውን ሲጀምር፣ ግብፅ አጠቃላይ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ግማሽ ያህሉን የሸፈነ ስለነበረ፣ በዚህም ኃይል የተነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግብፅ የገጠር ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኛ ምንጭ ሆኗቸዋል፡፡ በተጨማሪም ግድቡና የተፈጠረው ሐይቅ፣ ለግብፅ ከፍተኛ የሀብት ምንጭ በመሆን ወደ መካከለኛ ኑሮ ደረጃ እንዲተላለፉ አድርጓቸዋል፡፡ ከተፈጠረው ሐይቅ ውኃ በመውሰድ፣ እ.ኤ.አ. በ1972-73 እና በ1983-87 የተከሰቱትን ድርቆች ለመቋቋም ያስቻላት ሲሆን፣ ሰፋፊ መስኖዎችን በማዘጋጀት፣ ከ840,000 ሄክታር መሬት በላይ በማልማት፣ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ገበሬዎችን በማስፈር፣ በዓመት ሁለት ጊዜ በመዝራት እንደ ሩዝ፣ ስንዴ የመሳሰሉትን በማምረት፣ በከፍተኛ ደረጃ ከውጭ የምታስገባውን ቀንሳለች፡፡ በተጨማሪም የአስዋን ግድብ በፈጠረው ሐይቅ በመጠቀም፣ ለተለያዩ የአግሮ ኢንዱስትሪ፣ እንደ ስኳር፣ ፍራፍሬና የፍራፍሬ ጭማቂ ወዘተ፣ የዓሣ ኢንዱስትሪ፣ የቱሪስትና የመዝናኛ፣ የውኃ ትራንስፖርት ወዘተ በማደራጀት ዛሬ ግብፅ ለደረሰችበት የኢኮኖሚ ዕድገት የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡
ወደ አገራችን መለስ ስንል፣ የምንገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከአስዋን ግድብ በትንሹ ከሁለት ጊዜ በላይ ይሆናል፡፡ ይሄም ማለት በግድባችን ላይ በአግባቡ ከሠራን፣ በቀላሉ አስዋን ግድብ ከሚሰጠው አጥፍ የልማት ጥቅም ልናገኝበት እንችላለን፡፡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት ኢትዮጵያ በሦስት ዓበይት ጉዳዮች ከፍተኛ ጥቅም ልታገኝ ትችላለች፡፡ አንደኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ሲሆን፣ ይሄም የህዳሴ ግድቡ የሚሰጠውንና የሌሎች ግድቦችን ኃይል በመጨመር፣ የራሷን ፍጆታ አሟልታ፣ ከፍተኛ ኃይል ለሰሜንና ለምሥራቅ አፍሪካ በማቅረብ በውጭ ምንዛሪ የመሸጥ ዕድል ይሰጣታል፡፡ ሁለተኛው የውኃ ሀብት ሲሆን፣ ይሄም ቢሆን ወደ ፊት በከፍተኛ ሁኔታ ውኃውን በማበልፀግና ወደ ውጭ በማስተላለፍ በራሷ ልጆች የሸጠችውን ወደብ ማካካሻ በመሆን፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሀብት ማግኛ ሊሆናት ያስችላታል፡፡ እንዴት ሀብት እንደሚሆን፣ ጦጣ “…በፊት መቀመጪያዬን” እንዳለቸው፣ አሁን ጊዜው ስላይደለ በቆይታ ይቀመጥ፡፡ ሦስተኛው በህዳሴ ግድብና እሱ በሚፈጥረው ሐይቅ የሚዘጋጁት ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ሴክተሮችን በማስጠናት፣ እንደ የመስኖ እርሻ፣ የአሣ ሀብት፣ የቱሪስት መዝናኛ፣ የውኃ ትራንስፖርት፣ የመጠጥ ውኃ ወዘተ የመሳሰሉትን በማልማት፣ አገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ያደርሷታል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ውስበስብ ችግሮች አሉባት፡፡ ከነዚህም አንዱ የወጣት ሥራ አጥነት ነው፡፡ በገበሬው አካባቢ ልጆቹ የእርሻ መሬት በማጣት ካለ ሥራ ተቀምጠዋል፡፡ በከተማም ወጣቱ እንደ አቅሙ ተምሮ ሥራ ሳይዝ ቤቱ የተቀመጠ በሚሊዮን ነው፡፡ ይሄን ትኩስ ኃይል ቶሎ ብሎ ሥራ ካልተሰጠው፣ አገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ትገባለች፡፡ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት፣ መፍትሔው የኢትዮጵያ የዕድገት አካሄዷ መሆን ያለበት የሥራ ዕድል በሚፈጥሩ ትላልቅ ዘመናዊ እርሻና ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ሴክተሮች ላይ ሲተኮር ነው፡፡ ከነዚህም አንዱ በደንብ ከተጠቀምንበት፣ ከላይ በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጥነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ትሩፋቶች ማለትም በግድቡና በእርሱ ከሚፈጠረው ሐይቅ ዙሪያ የኢኮኖሚ ሴክተሮችን ስንዘረጋ ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ ከኤሌክትሪክ ኃይል ሌላ፣ ሌላም የኢኮኖሚ ጥቅም እንደሚሰጠን አውቀን፣ እነዚህን ለመጠቀም ጎን ለጎን የኢኮኖሚ አውታሮች ማዘጋጀት አለብን፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይሉ ብዙ የተባለለት ስለሆነ፣ በዚህ ላይ ጊዜ ሳናጠፋ በሦስተኛ ደረጃ ወደ ተቀመጠው የታላቁ ህዳሴ ግድብና በዚሁ ግድብ ምክንያት በተፈጠረው ሐይቅ ላይ ሊገነቡ ወደ ሚችሉ አንዳንድ የኢኮኖሚ ሴክተሮች ዘርዘር አድርገን እንያቸው፡፡
ከግድባችን በሚገኝ ትሩፋት ከፍተኛ የመስኖ ልማት ማካሄድ ይቻላል፡፡ በሁሉም አካባቢ የሚገኙትን የወጣት ሥራ ፈት በብዛት በማሰባሰብና በማስፈር በመስኖ ዘመናዊ እርሻ እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ማንጎ፣ አቦካዶ፣ ብርትኳን፣ መንደሪን፣ ሙዝ፣ ወዘተ የመሳሰሉትን አምርተው ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ ይቻላል፡፡
በባዮማስ ላይ የተመሠረተ ተያያዥ የልማት ኢንተርፕራይዞች መፍጠር
ባዮማስ ማለት ሕይወት ባላቸው አካላት በዕድገት ምክንያት የሚከማች ቁስ ሲሆን በዋናነትም ዕፀዋትን ያካትታል፡፡ በባዮማስነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የደን ሀብት፣ የሸንኮራ ተክል፣ የእርሻ ሰብልና ቃርሚያ፣ የእርሻና ኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት ወዘተ ይገኙበታል፡፡ በግድቡ አካባቢ ከፍተኛ የባዮማስ ሀብት እንደ ዘንባባና የጎማ ዛፍ ማልማት የሚቻል ሲሆን፣ እነዚህንም በፋብሪካ ውስጥ በመጭመቅ የምግበ ዘይትና ለመኪና ጎማ የሚሆን ጥሬ ዕቃ ማምረት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል የመስኖ ውኃን በመጠቀም በአገራችን የተለመደውን የባዮማስ ዓይነት የሆነውን የሸንኮራ ተክልን በዚሁ ግድብ በሚያመጣው ልማት በሰፊው በማልማትና ወደ ፋብሪካ በመውሰድ በባዮሪፋይነሪ የተለያዩ ምርቶች ማምረት ይቻላል፡፡ ግብፅም በአስዋን ግድብ ከሸንኮራ ተክል ልማቷ ስኳር ታመርታለች፡፡
እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ሸንኮራ ተክለን ወደ ኢንዱስትሪ እንወሰደው ስንል፣ አሁን እያመረትንበትን መንገድ እንከተል ማለት አይደለም፡፡ የአሁኑ አሠራራችን ኋላ ቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በላይ ስኳርን ከሸንኮራ ተክል እያመረተች ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ ፋብሪካዎች ኤታኖል ከማምረት በስተቀር፣ የሸንኮራ ተክልን በባዮሪፋይነሪ ወደ ተለያዩ ምርቶች በመቀየር ያመረተችው ምርቶች ከሁለት አይበልጡም፡፡ ይሄም የሚያሳየው ከዚህ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያው ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ በሌላ በኩል እንደ ብራዚል፣ ህንድ፣ ኩባ፣ ታይላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና፣ አሜሪካ ያሉ አገሮች ቴክኖሎጂያቸውን በማዘመን በርካታ የተለያዩ ምርቶችን ከሸንኮራ ተክል ጥሬ ዕቃ በማምረት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አግኝተውበታል፡፡ ለምሳሌ ብራዚልን ብንወስድ ከሸንኮራ ተክል በመነሳት ኤታኖልን ከ500 በላይ ፋብሪካዎች ውስጥ በማምረት ከ50 በመቶ በላይ የሆኑትን መኪኖቻቸውን (40 ሚሊዮን መኪና) ሙሉ በሙሉ ቤንዚንን በመተካት በኤታኖል እንዲነዱ አድርገዋል፡፡ ህንድ በተመሳሳይ መንገድ ምርቶቹን ከመጠቀሟም በላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሸንኮራ ተክል እርሻና፣ በዚሁ ኢንዱስትሪ አሰልፋለች፡፡
በአገራችንም ልክ እንደሌሎቹ አገሮች ከሸንኮራ ተክል በመነሳት፣ ባሉት የስኳር ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት በእኔ የሚመሩ ታዋቂ መሐንዲሶችና ሳይንቲስቶች በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ፣ በፖሊሲ ጥናት ምርምር ኢንስቲትዩትና በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አስጠኚነት ወደ አራት ዓመት የሚጠጋ ጥናት አጥንተናል፡፡ አሁን ያሉትን የስኳር ኢንዱስትሪዎች ዓለም ላይ በአሁኑ ጊዜ ወደ ደረሰበት ቴክኖሎጂ በማሸጋገር፣ በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ የሆኑ እንደ ኤታኖል፣ ፐልፕ (ወረቀት)፣ ቅንጣጢት ቦርድ (Cheap wood)፣ ማዳበሪያ፣ የእንሰሳት መኖ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ወዘተ በስኳር ኢንዱስትሪዎች እንዲመረቱ ያቀረብነውን ጥናት ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከነካቢኔያቸው፣ ለሁለት ክልሎች ማለት ለትግራይና ለደቡብ ፕሬዚዳንቶችና ካቢኔዎቻቸው፣ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች፣ ለስኳር ኢንዱስትሪዎች ኃላፊዎች፣ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ወዘተ አቅርበን ተቀባይነት ካገኘ በኋላ፣ ለውጡ ስለመጣ እስከ አሁን ሳይተገበር ቆይቷል፡፡ አሁን ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ጥሩ ዕድል ስላመጣ፣ በመስኖ ሸንኮራ ተክል በማልማት የተለያዩ ለአገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ምርቶች ከማምረት በተጨማሪ ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ልናደርገው እንችላለን፡፡
የዓሳ ሀብት
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ይዞልን ከሚመጣው አንዱ ትሩፋት፣ ለዓሳ መራቢያ የሚሆን ሐይቅ መፈጠሩ ነው፡፡ በዚህም ሐይቅ ከፍተኛ ግምት ያለው ዓሣ ሊገኝ ስለሚችል የዓሣ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በማዘጋጀት ቀላል ለማይባል ወጣት የሥራ ዕድል ከመፈጠሩም በላይ፣ የአገርን ኢኮኖሚ ሊደግፍ ይችላል፡፡
ፍራፍሬና የፍራፍሬ ጭማቂ
ግብፅ አንዱ የምትኩራራበትና ለዓለም በፊልም የምታሳየው በአስዋን ግድብ የምታመረተውን የተለያዩ ፍራፍሬዎች በተለይ ብርቱካንና መንደሪን ናቸው፡፡ እኛም ከ300 ኪ.ሜ. በላይ ባለው የግድቡ ሐይቅ ዳርና ዳር ተከትለን ብርቱካን፣ መንደሪን፣ ማንጎ፣ አቦካዶ፣ ሙዝ ወዘተ ተክለን፣ እንዳለ ወይም በፋብሪካ በማቀነባበር ለውጭ ገበያና ለአገር ውስጥ በማቅረብ ለኢኮኖሚው ማደግ ጉልህ ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከሚፈጥረው አንዱ ትሩፋት ሰው ሠራሽ ሐይቅና ከ50 በላይ ትናንሽ ደሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ውብ ደሴቶች፣ ለቱሪስት መዝናኛ የሚመረጡ ናቸው፡፡ እነዚህን መዝናኛ ደሴቶች በማልማት፣ ከሚሊዮን ሕዝብ በላይ በቱሪስት በማስተናገድ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ መታደግ ይቻላል፡፡ የቱሪስት ኢንዱስትሪን በማሳደግ ለመጠቀም ግን በመጀመሪያ ሕዝቡ፣ ዓመታዊ ዕረፍትንም ሆነ በሌላ መልኩ አርፎ የመዝናናት ባህል ማዳበር አለበት፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕረፍቴን ከቤቴ ወጥቼ አንድ ቦታ ሄጄ ላሳልፍ የሚል ባህል የለም፡፡ ለዚህም ምናልባት በባህል ያልተለመደ ወይም የገንዘብ እጦት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይሄ የሚቀረፍበትን መንግሥት ማመቻቸት አለበት፡፡ ቻይና ካደገችበት አንዱ ምስጢር ዜጎቿን በአገር ውስጥ ጉብኝት እንዲያደርጉ በማመቻቸት ዛሬ ከ400 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በአገር ውስጥ ዓመታዊ ዕረፍታቸውን ከአካባቢያቸው ውጪ በመሄድ ኢኮኖሚውን ይደግፋሉ፡፡
በአጠቃላይ በታላቁ የህዳሴ ግድብ መብራት ብቻ አመንጭተን ከተውን፣ ዓለም ይስቅብናል፡፡ ግድብ ይዞ ብልፅግና፣ ልክ እባብ ይዞ ዱላ፣ ሥጋ ይዞ ቢላዋ ወዘተ እንደ መፈለግ እንደሚባለው ነው፡፡ ዛሬ ግብፅ ታሪካችንን እያወቀች፣ እኛ ላይ ያዙኝ ልቀቁኝ ያለችው፣ ከኛ በፊት የአስዋን ግድብ ገንብታ ባፈራቸው ሀብት ነው፡፡ እኛም ዛሬ ትልቅ የልማት በር በታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሊከፈትልን ነው፡፡ ይሄንን በር ሙሉ በሙሉ ከፍተን በመጠቀም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገራችንን ወጣቶች በማስፈር፣ በእርሻ ላይ በማሰማራት፣ በመስኖ እንደ ሩዝ፣ ስንዴ የመሳሰሉትን በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ራሳችንን እንድንችል፣ በኢንዱስትሪ ላይ በማሰማራት፣ ከሸንኮራ ተክል፣ ከዘንባባና ከጎማ ዛፍ፣ ከፍራፍሬና የፍራፍሬ ጭማቂ ወዘተ ልዩ ልዩ ምርቶችን ማምረት እንድንችል፣ በዓሣ ማቀነባበሪያ ውስጥ የተለያ ምርቶች በማምረት አገሪቷ ከራሷ ተርፋ ለውጭ የምታቀርብበትንና የቱሪስትና የመዝናኛ፣ የውኃ ትራንስፖርት ወዘተ በማስፋፋት ዜጎች የአገራቸውን ትሩፋት የሚቋደሱበትን ማስቻል አለብን፡፡
ከላይ የዘረዘርናቸውን የኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት ቀላል አይደለም፡፡ መንግሥት፣ በከፍተኛ ውጥረት ላይ እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ አገርን ለማፍረስ አፋቸውን ሞልተው የሚንቀሳቀሱ በአገር ውስጥም በውጪም አሉ፡፡ መንግሥት ማድረግ ያለበት የፖለቲካ ሥራና የመንግሥትን ሥራ መለየት አለበት፡፡ የብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካውን ይሥራ፡፡ የመንግሥት ሥራ እንደ ልማት የመሳሰሉትን፣ ሙሉ በሙሉ ሚኒስትሮች፣ የድርጅት ኃላፊዎች ወዘተ ሌት ተቀን ሥራቸው ይሁን፡፡ የሕግ የበላይነቱን የፍትሕ አካላትና ፖሊስ በማያወላዳ ሁኔታ ያስከብሩ፡፡ መከላከያም ቢሆን አፈንግጠው፣ የአገርን መንሸርሸር ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች ሲጋጥሙ የማያዳግም ውሳኔ ወስዶ አገርን መጠበቅ አለበት፡፡ ይሄ በሚሆንበት ጊዜ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግሥት ጋራ ሆኖ ድህነት ይብቃ፣ አገራችንን እናልማ ብሎ በመጀመርያ ቃል ኪዳን መግባት አለበት፡፡ በምን ያህል ጊዜ እንደምናለማ መወሰን አለበት፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ልማት የሚዘረጋና ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጠው “የዓባይ ተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን” የሚል በውስጡ የተለያዩ ተጠሪ መሥርያ ቤቶች የያዘ ግዙፍ ተቋም መመሥረት አለበት፡፡ ይሄም መሥርያ ቤት በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በመንግሥት፣ በአገር ባለሀብትና በውጪ ሊለሙ የሚችሉትን በመለየት ሥራውን ይመራል፡፡
ይሄ ልማት ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሆነ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ከዚህም የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ስንል የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለታችን ነው፡፡ ሕዝቡ ማመን ያለበት አገሪቱን ሊያሳድግ የሚችለው ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ ይሄም ልማት በቀላሉ አይመጣም፡፡ ምናልባትም በጊዜው ላለው ትውልድ ልማት ማምጣት መራራ ሊሆን ይችላል፡፡ ትውልድ ለራሱ አይደለም የሚሠራው፣ ለመጪው እንጂ፣ ሕዝቡ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ቀበቶውን ጠበቅ አድርጎ ከመሥራት በስተቀር፡፡ የውጭ አገሮች የሚጥሩት በአንድ አገር ላይ ሸቀጣቸውን ለማራገፍ እንጂ የባዕድን አገር ችግር ቀርፎ፣ ከድህነት ለማውጣት እንደማይሠሩ አፍ ሞልቶ መናገር ባይቻልም፣ መጠርጠር ግን ኃጢአት አይደለም፡፡ ስለዚህ “እኛው እንደጀመርነው እኛው እንጨርሰዋለን“ የሚባለው አባባል አሁንም ደግመን ግድባችንን በማልማት ከድህነት መውጣት አለብን፡፡
የሕዝብ አካል የሆነው አንዱ መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት ሀብት ደግሞ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ልማት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከሕዝቡ አሰባስቦ ለልማት ማዋል አለበት፡፡ ግድቡ ሲጀመር ይሄን ያህል ገንዘብ በሕዝቡ ተዋጥቶ ይሠራል ብሎ ማሰብ እብደት ሊመስል ይችል ነበር፡፡ ግን እየተሳካ ነው ያለው፡፡ አሁንም ከግድቡ በተጨማሪ፣ ግድቡ የሚሰጠውን ሌሎች ትሩፋቶች ለማልማት፣ ባለሥልጣኑ የሚለማውን ልማት ማለትም ግብርናና ኢንዱስትሪ ከለየና የአዋጪነት ጥናት ካስጠና በኋላ ለልማት የሚያስፈልገው ገንዘብ ይታወቃል፡፡
እንግዲህ ዋናው ቁልፍ ችግር የሚሆነው ለልማቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማዘጋጀት ነው፡፡ መንግሥት ለዚህ ልማት የሚሆን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የመሸፈን አቅም አይኖረውም፡፡ ከመንግሥት የሚጠበቀው፣ ያለውን ገንዘብ ለማይቀሩ ተፈላጊ ሥራዎች በበጀት መድቦ፣ የተቀረውን ለዚህ ልማት ማዋል ነው፡፡ በተጨማሪም የመንግሥት ሥራ የሚሆነው፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ነው፡፡ ከአገር ውስጥ የሚሰበሰበውና ዋናው የገንዘብ ምንጭ የሚሆነው ከሕዝቡና ከድርጅቶች የሚሰበሰበው ነው፡፡ ሕዝቡ ለህዳሴው ግድብ ከሚበላው ቆርሶ እንደሰጠው፣ ለዚህም ልማት እንደገና፣ ከትንሽ እስከ አዋቂ በነብስ ወከፍ ገንዘብ ተመድቦበት እንዲያዋጣ መደረግ አለበት፡፡ ሕዝቡ ሌቦች ሲበሉበት ይናደዳል እንጂ፣ ለልማት ነው ከተባለ፣ ቁርሱን ወይም እራቱን ትቶ እንደሚከፍል አይተናል፡፡ ሠራተኛውና ገበሬው፣ በግል የሚተዳደረውም ወዘተ፣ መንግሥት የልማቱን ዓላማና ለምን እንደሚያለማ ለሕዝቡ ከነገረውና ካሳመነው፣ ማሳመን ቀላል ነው፡፡ ዓይኑን ሳያሽ የተመደበለትን ይከፍላል፡፡ ለመንግሥት ሌላው የገንዘብ ማግኛ ዘዴ የሚሆነው፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንደ ባንክና ኢንሹራንስ፣ የተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት ወዘተ፣ ከትርፋቸው ላይ ልክ ህንድ እንዳደረገው የልማት ቀረጥ (Development Fund) ተጥሎ እንዲከፍሉ መንግሥት መደንገግ አለበት፡፡ በአጠቃላይ፣ ተቸግረንም ቢሆን ኢትዮጵያን ካለማን፣ ካላት ታላቅ ታሪክ ጋራ እንደ ግብፅ መሪዎች ዓይነት፣ በኢትዮጵያ ላይ አፋቸውን የሚከፍቱባት አትሆንም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው በላይ ወልደየስ (ዶ/ር፣ኢንጂነር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡