Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኮቪድ-19 ሕይወታቸውን ያጡት ሐኪምና የዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፍሥሐዬ ዓለምሰገድ (ዶ/ር) (1970-2012)

በኮቪድ-19 ሕይወታቸውን ያጡት ሐኪምና የዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፍሥሐዬ ዓለምሰገድ (ዶ/ር) (1970-2012)

ቀን:

በኢትዮጵያ በመጋቢት ወር የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ፈጣን ግብረ መልስ ቡድን መሪ በመሆን ኅብረተሰቡን ከቫይረሱ ለመታደግ ሌተቀን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ዩኒቨርሲቲው የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት በኢፒዲሚዮሎጂ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ፍሥሐዬ ዓለምሰገድ (ዶ/ር)፣ የትግራይ ጤና ቢሮ ባደረገላቸው ጥሪ በኮሮና ቫይረስ መረጃ ትንተና እና ትንበያ ክፍል በመሥራት ላይ እያሉ ነበር በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ሕክምና ሲደረግላቸው ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

በነሐሴ መባቻ ሕይወታቸው ላለፈው ዶ/ር ፍሥሐዬ 17 ዓመታት ያገለገሉበት ጅማ ዩኒቨርሲቲም፣ ‹‹ሳትሰስት ሕይወትህን ስለሰጠህለት ሙያዊ አገልግሎትህ እናመሰግናለን! እናከብርሃለንም!›› በሚል መሪ ቃል ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።

1995 እስከ 2011 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው አካዴሚክ ባልደረባ በመሆን በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችና የትምህርት ዘርፎች አርአያነት ያለው ተግባር በመፈጸም ማገልገላቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡ በቆይታቸው በመማር ማስተማር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በጥናትና ምርምር ሰፊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተገልጿል፡፡

በወባ፣ በቲቢ፣ ደም ግፊት፣ ሥነ ተዋልዶ ጤናና ኤችአይቪ ኤድስ፣ የአመጋገብ ሥርዓትን (ሥነ ምግብ) ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ 50 በላይ የምርምር ሥራዎችን በተናጠልም ሆነ በቡድን ማካሄዳቸውንና ሥራዎቻቸው በታዋቂ ጆርናሎች (የጥናት መጽሔቶች) ታትሞላቸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ዓድዋ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ይሓ በተባለ ቦታ 1970 .ም. የተወለዱት ዶ/ር ፍሥሐዬ፣ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የሕክምና ትምህርታቸው በስኬት በመጨረስ በጠቅላላ ሐኪምና በኅብረተሰብ ጤና የማስተርስ ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ ሐዘኑን የገለጸው አክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፍሥሐዬ (ዶ/ር) በእናቶችና ሕፃናት ሕክምና፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣ በሥነ ምግብ፣ በወባ፣ በኤችአይቪ ኤድስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ጨምሮ በሌሎች የኅብረተሰብ ጤና ዘርፎች 50 በላይ ችግር ፈቺ ጥናቶችን በታዋቂ ጆርናሎች በማሳተም አዳዲስ ዕውቀቶች በማፍለቅ ለዓለም አሻራቸውን አሳርፈዋል ብሏል።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማኅበረሰብ ነሐሴ 6 ቀን ባከናወነው ሥነ ሥርዓት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ጧፍ በማብራት ገልጿል፡፡  

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት  ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር)፣ ‹‹ዶ/ር ፍሥሐዬ ለዩኒቨርሲቲያችን ብሎም ለአገራችን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለኛ ከፍተኛ ትምህርት የሚሆን ነው›› ሲሉ፣ ‹‹ባለሙያዎቻችንን በዚህ መልኩ ማጣታችን ከባድ ሐዘን ውስጥ  ከቶናል›› በማለት በማኅበራዊ ገጽ ሐዘናቸውን የገለጹት ደግሞ የጤና  ሚኒስትር  ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የሕክምና ማኅበር አባላትም የዶ/ር ፍሥሐዬን ቤተሰብ ለማጽናናትና ለማገዝ ኮሚቴ አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...