Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮቪድ-19 ሕሙማን ቤት ውስጥ የማገገም ተፅዕኖ

የኮቪድ-19 ሕሙማን ቤት ውስጥ የማገገም ተፅዕኖ

ቀን:

ከቤተሰብ አባላት፣ ከጎረቤት፣ ከጓደኛና ከሥራ ቦታ ራስን አግልሎ መኖር ከባድ ሆኖባታል፡፡ ከቤተሰብ አባላት ጋር አብሮ መመገብ ዛሬ የለም፡፡ ሕፃናት ልጆቿንም ቤተሰብ ጋር ልካለች፡፡ እሷና አንድ ልጇ ብቻ ቤታቸውን ዘግተው ሕመማቸውን ያስታምማሉ፡፡

ይህ ምናልባትም ከወር ላልበለጠ ጊዜ የሚቆይ ቢሆንም፣ አስቸጋሪ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ የጎላ የሕመም ስሜት ባይኖራትም ጭንቀቱ፣ አብሯት ያለው ልጇ ከዛሬ ነገ ያመው ይሆን ወይ? ብላ ማሰላሰሏ፣ ዘመድ ዘንድ ኳራንታይን እየተደረጉ ያሉት ልጆቿና ባለቤቷ የመጀመሪያውን ዙር ምርመራ ነፃ ቢሆኑም የቀጣዩን እንዴት ይሆኑ ይሆን? የሚለውም ያስጨንቃታል፡፡

ይህን የነገረችን በወጣትነት የዕድሜ ክልል የምትገኘው የሕክምና ባለሙያ፣ በኮቪድ-19 መያዟን ካወቀች ሳምንት አልፏታል፡፡

የሕክምና ባለሙያዋ እንደምትለው፣ የኮቪድ-19 ታማሚ ሆኖ ቤት ማገገም በተለይ በኢትዮጵያ የአኗኗር ደረጃ በጣም ከባድ ነው፡፡ የቤተሰብ አባላት በተለይ ሕፃናት ልጆች ባሉበት ቤት ውስጥ የተትረፈረፈ ክፍል ቢኖርም፣ ራስን ነጥሎና ተጠንቅቆ መኖር ይቻላል ማለት  አይቻልም፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በሚያስቀምጠው መልኩ መፀዳጃን ከተቻለ መለየት፣ የሚጠቀሙበትን ዕቃ መለየት፣ የታማሚን ክፍል በሌሎች አለማፀዳት፣ የታማሚን ልብስ በጥንቃቄ ለብቻ በማሽን ማጠብና ሌሎችም እንዲህ በቀላሉ የሚተገበሩም አይደሉም፡፡ ቤት ውስጥ ልጆች ሲኖሩ ደግሞ የእናታቸው ወይም የአባታቸው መታመም ለእነሱ ጉዳት መሆኑ አይታያቸውም፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ከቤተሰብ ሥር አለመውጣትን ይመርጣሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ኑሮን ማስተዳደር ከባድ ነው፡፡

የጥንቃቄ መንገዶቹ በተለይ የሕክምና ሙያ ለሌላቸው ሰዎች አሰልቺ ናቸው የምትለው የጤና ባለሙያዋ፣ በዚህ ሁኔታ ተጠንቅቆ የቤተሰብ አባላትን ማዳን ስለማይቻል፣ ከሷና ከአንድ ልጇ በስተቀር ሌሎቹ ቤተሰቦቿ ዘመድ ጋር እንዲሆኑ የወሰነችውም ለዚሁ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እቤት በቀሩት እሷና ልጇ ዘንድ ድብርትን ፈጥሯል፡፡

‹‹እኔ የጤና ባለሙያ ስለሆንኩና ኃላፊነቴን መወጣት ስላለብኝ ችዬ እቀመጣለሁ፡፡ ነገር ግን በቤታቸው እንዲቀመጡ የተደረጉ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ቤት ይቀመጣሉ ብዬ አላምንም ፡፡ የታመመ ሰው ብቻውን ቤት ውስጥ ይቀመጣል ማለትም ከባድ ነው፤›› ትላለች፡፡ እሷ አማራጩ ስላላት ቀሪ ቤተሰቧን ዘመድ ትላክ እንጂ ይህ ለብዙዎች የሚሆንም አይደለም፡፡

ቤት ውስጥ መሆን ከምርጫ ማጣት የመጣ ቢሆንም፣ ዋጋ እንዳያስከፍል እፈራለሁ የምትለው፣ የጤና ባለሙያ፣ በሽታው በተለይ እንደ እሷ ቤተሰቦቹን ሌላ ቦታ አስቀምጦ ራሱን ለይቶ ማገገም ለማይችል ሰው እዚያው እየተዘዋወረ በቤተሰብ መሀል ለረዥም ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል ትገልጻለች፡፡

አንድ የቤተሰብ አባል ታሞ ቤት ሲቀመጥ በወቅቱ አብረው ምርመራ የተደረገላቸውና የቤተሰብ አባላት ነፃ የሆኑት ወጥተው ሠርተው መመለሳቸው የማይቀር መሆኑ፣ ዛሬ ነፃ የሆኑ የቤተሰብ አባላት ቤት ውስጥ ታማሚ እስካለ በየትኛውም ጊዜ በቫይረሱ ሊጠቁ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖሩና በየዕለቱ እየተመረመሩ ስለማይረጋገጥ የበሽታውን የመሰራጨት ዕድል ያሰፋዋል፡፡

እንደ ጤና ባለሙያዋ ሁሉ ሌሎች ጤና ባለሙያዎችና ከ3,000 በላይ ሰዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ ተደርጓል፡፡ ሥርጭቱ እየጨመረ በመጣው ቫይረስ ምክንያትም የጤና ተቋማት የመቀበል አቅምም እየተሟጠጠ ነው፡፡ ይህንን ከግንዛቤ በማስገባትና ሕሙማን ቤታቸው ሆነው ለማገገም እየጠየቁ መሆኑን በማየት፣ ምልክት የማያሳዩ ወይም መለስተኛ ምልክት አሳይተው ተጓዳኝ በሽታ የሌለባቸውና ቤታቸው አመቺ የሆኑ የኮቪድ-19 ታማሚዎች፣ ቤታቸው የሚያገግሙበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ይህ ሲሆን ግን በርካታ ችግሮች አሉት፡፡

በቤት ውስጥ ያሉትን ቤተሰቦች ከበሽታው ተከላክሎ የማቆየት ዕድሉ ጠባብ መሆን፣ በየጊዜው በጤና ባለሙያ የመታየት ዕድልን ለማመቻቸት የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ከገንዘብም ሆነ ከሰው ኃይል አኳያ አለመቻሉ ችግሩን ያጎላዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሀብታም አገሮች ችግር የሆነው ኮቪድ-19፣ ሰዎችን በሆስፒታል ብቻ አክሞ ለማዳን አስቸጋሪ በመሆኑ አገሮች ታማሚዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ አድርገዋል፡፡ በቤታቸው እንዲያገግሙ የሚደረጉ ሕሙማንም ምልክት የማያሳዩ ወይም ዝቅተኛ ሕመም ያላቸው ናቸው፡፡

ሆኖም የአገሮች አቅም ማጣት እንጂ ከቫይረሱ ባህሪ አንፃር የኮቪድ-19 ታማሚን እቤት እንዲያገግም ማድረግ አማራጭ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አመዘነ ታደሰ (ዶ/ር) እንደሚሉትም፣ ቤት ውስጥ ሆኖ ማገገም የሚመረጥ አይደለም፡፡ ሆኖም የታማሚው ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት መሸከም ስለማይችል ምልክት የማያሳዩ፣ ዝቅተኛ ሕመም ያላቸውና ተጓዳኝ በሽታ የሌለባቸው የኮቪድ-19 ታማሚዎች ቤታቸው እንዲያገግሙ እየተደረገ ነው፡፡

‹‹ሳንወድ ተገደን ነው ያደረገግነው›› የሚሉት ዶ/ር አመዘነ፣ ሰዎች በቤታቸው ባገገሙ ልክ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉም እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡

ከአንዳንድ ሰዎች ባገኘነው መረጃ መሠረት ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ከጥቂት ቀናት በኋላ ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ በሚሊኒየም ወይም በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እንደሚደረገው ጠብቆ ማቆየትም አይቻልም፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል ያልናቸው ዶ/ር አመዘነ፣ ቤት ውስጥ የሚያገግሙ ሰዎች ከቤት ውስጥ ሊወጡ የሚችሉበት አጋጣሚ አለ፡፡ በመሆኑም ህሊናቸውን ዳኛ አድርገው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አካባቢያቸውን ከቫይረሱ መጠበቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

ሁሉን በጤና ጣቢያ ማከም አንችልም፣ ቤት ውስጥ የሚያገግም ሰው የኢኮኖሚ ሁኔታው፣ የትምህርት ደረጃው፣ ለቫይረሱ ያለው ግንዛቤ ታይቶ ቢሆን ጥሩ ነበር ያሉት ዶ/ር አሁን እየጨመረ ባለው የሥርጭት መጠን ያክል  ከቀጠለ አቅም እንደማይኖርና ቤት የማገገም አማራጭ እንደማይቀር ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶክተር አመዘነ፣ ታማሚም ሆነ ጤና ባለሙያው መተሳሰብ አለበት፡፡ የሚቻለውን ጥንቃቄ ማድረግም ይጠበቅበታል፡፡ የባህሪ ለውጥ ማምጣትም ግድ ነው፡፡ ባህሉም ልማዱም የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም፣ ሰዎች ከቤሰተብም ሆነ ከጓደኛ ጋር  ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው መኖር አለባቸው፡፡ ሕመምተኛ ሆነ አልሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

በአዲስ አበባ ብቻ ከ3000 በላይ የኮቪድ-19 ሕሙማን ቤታቸው አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን መጎብኘቱና የምክር አገልግሎት መስጠቱ የሚቻል አይደለም፡፡ ይሞከር ቢባል እንኳን ቀድሞውንም በፈተና ውስጥ ያለውን የጤና ሥርዓት ይበልጥ ይጎዳዋል፡፡ በሌላ በሽታ የሚታመሙና ድንገተኛ አደጋ የሚደርስባቸውን ለማከምም ትልቅ ፈተና ይሆናል፡፡  

በቤት ውስጥ ማገገም በግድ የሚገባበት አማራጭ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን የታመሙም ሆነ ያልታመሙ ሰዎች ከፍተኛውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ በተለይ የግልና አካባቢ ንፅህናና መጠበቅ፣ ታማሚው የሚጠቀማቸውን ዕቃዎች በተገቢው ማፅዳትና የማይፀዱትን ማስወገድ ግድ ይላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአንድ ቤት ውስጥም ቢሆን አኗኗርን መለየት ግድ ነው፡፡ ከጤና ተቋማት ደግሞ የሰው ኃይል መድቦ ታማሚዎችን በየቤቱ መድረስ ስለማይቻል የየቀን ሁኔታቸውን በስልክ ድምፅ ጽሑፍ መልዕክት መከታተልና መረጃ የሚለዋወጡበትን መንገድ በቅርበት ከሚያገኙት ወረዳ ጋር ማስተሳሰር ይጠበቃል፡፡

የጤና ሥርዓቱ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የቫይረሱ ታማሚዎች ቢመጡ መሸከም የማይችለውን ያህል፣ የአንድ ቤተሰብ አባላትም ከመሀላቸው አንዱ ቢታመም የተቀመጡ የመከላከያና የጥንቃቄ መስፈርቶችን ለማሟላት ይቸገራሉ፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ኮቪድ-19 የሚፈልገውን የባህሪ ለውጥ ማምጣትም ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ ቀላል የሆኑትን የመከላከያ መንገዶች ሳይሰላቹ በመተግበር ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከቫይረሱ መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡   

ዕለት ዕለት የሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሰዎችን በበሽታውመያዝ ዕድል የሚወስን መሆኑን በማስታወስ፣ የኮሮና ቫይረስ መከላከያን መተግበር የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል ያስችላል፡፡

አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በተደጋጋሚ በውኃና በሳሙና መታጠብ፣ አስገዳጅ ካልሆነ ቤት ውስጥ መቆየትና አፍና አፍንጫን መሸፈን ከሁሉም የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...