Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ ሊመሰክሩ የነበሩ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በኮሮና ምክንያት...

በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ ሊመሰክሩ የነበሩ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በኮሮና ምክንያት ሳይሰሙ ቀሩ

ቀን:

የእነ አቶ በቀለ ‹‹ዳኛው ይነሱልን›› ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ ለአንድ ወር ያህል የሰበሰበውን የምስክሮች ቃል ማስረጃ በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት አስመስክሮ ማስረጃውን ለማቆየት ነሐሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ምስክሮቹን ፍርድ ቤት ያቀረበ ቢሆንም፣ በምርመራ መዝገቡ ከተካተቱት 14 ተጠርጣሪዎች አምስቱ በኮሮና ቫይረስ በመያዛቸው ምስክሮቹ ሳይሰሙ ቀሩ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምስክሮቹ በኮሮና ቫይረስ በያዛቸው ተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ በመሆናቸው መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበትን ጉዳይ እያዩት ያሉት የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ የወንጀል ችሎት ዳኛ ገለልተኛ ሆነው ጉዳያቸውን ሊያዩላቸው እንደማይችሉ በመግለጽ ያቀረቡት ‹‹ዳኛው ይነሱልን›› አቤቱታ በማስረጃ ተደግፎ ያልቀረበ መሆኑን ጠቁሞ፣ ዳኛው ሊነሱ እንደማይገባ በመግለጽ አቤቱታውን የመረመረው ሌላ ችሎት አቤቱታውን ውድቅ በማድረጉ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለነሐሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

በዕለቱ የፌዴራል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንዳስታወቀው፣ በመዝገቡ ከተካተቱት ተጠርጣሪዎች ውስጥ አምስቱ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በመረጋገጡ ሊያቀርባቸው እንዳልቻለ መናገሩን ዓቃቤ ሕግ ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡

የፍርድ ቤት የችሎት ውሎ ለመዘገብ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ተረኛ ወንጀል ችሎት ልደታ ማስቻያ ችሎት የተገኙ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፣ ከነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተጠርጣሪዎች በሚታደሙበት ችሎት መግባት ተከልክለው፣ በሌላ ችሎት ሆነው በፕላዝማ ሒደቱን እንዲከታተሉ ማድረግ ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ነሐሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በእነ አቶ ጃዋር ላይ የሚሰሙ ምስክሮችንና አጠቃላይ የችሎት ውሎን ለመዘገብ በተመደበላቸው ችሎት የተገኙ ቢሆንም፣ ፕላዝማው ምስል እንጂ ድምፅ ማስተላለፍ ባለመቻሉ የችሎቱን ውሎና ሒደት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የተሰጠው በዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡

በመሆኑም በዕለቱ ዓቃቤ ሕግ ሦስት ምስክሮችን አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ምስክርነት የሚሰጡባቸው ተጠርጣሪዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውንና ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ፌዴራል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በማሳወቁ፣ በሌሎቹ ላይ የሚመሰክሩትን ምስክሮች ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ መጠየቁ ዓቃቤ ሕግ ተናግሯል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች (አራት ናቸው) በዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ላይ ተቃውሞ ማቅረባቸውን እንደገለጹ ዓቃቤ ሕግ ተናግሯል፡፡ ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች ባልተመረመሩበት ሁኔታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረግ ለችሎቱም ሆነ ለእነሱ ጥሩ አለመሆኑን ተናግረው፣ ምስክርነቱ እንዲቋረጥ መጠየቃቸው ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው ሊንከባከባቸውና ሊጠብቃቸው እንደሚገባም ጠበቆቹ መናገራቸውን አክሏል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የፍትሕ አካል ሆኖ የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጥ ከማድረግ ይልቅ፣ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ አቤቱታዎችን በማቅረብ እንደፈለገው ሲያመለክት ችሎቱ ዝም ብሎ መቀበሉ ተገቢ እንዳልሆነ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች መቃወማቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሌላው አንስተውት የነበረው ጥያቄ የባንክ ሒሳባቸው በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ቢሆንም፣ ‹‹ይህ ጥያቄ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት የሚቀርብ አይደለም፡፡ ለሚመለከተው አካል አቅርቡ፤›› በማለት ፍርድ ቤቱ እንዳለፈው ዓቃቤ ሕግ ተናግሯል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ አያያዝን በሚመለከት ጠበቆቹ ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት፣ ቤተሰቦቻቸውን እያገኙ እንዳልሆነና መቀየሪያ ልብስ ለአንድ ወር ያህል እንዳልገባላቸው ተናግሯል፡፡

አቶ ጃዋር በራሱ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ አብረውት የታሰሩት ግለሰቦች የታሰሩት ጥፋት አጥፍተው ሳይሆን የእሱ አጃቢዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ምንም ያጠፉት ነገር ስለሌለ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡ አገራቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ ፖሊሶች መሆናቸውን በመጠቆም መጠየቅ ካለበትም እሱ መጠየቅ እንዳለበት መናገሩን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪ ሐምዛ አዳነ ባቀረበው አቤቱታ ቀደም ባለው ችሎት ውክልና እንዲሰጥ ጠይቆ ተፈቅዶለት እንደነበር አስታውሶ፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም ከታች ያሉት አስፈጻሚ አካላት ሊፈጽሙ አልቻሉም ወይም አልፈጸሙም፤›› በማለት በድጋሚ እንዲታዘዝለት መጠየቁን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ ምስክሮችን ማቅረቡና ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ መስጠቱ ተገቢ እንደሆነና ተጠርጣሪዎች እስር ላይ ስለሆኑ የተፋጠነ ፍትሕ ማግኘት ስላለባቸው ተገቢ አካሄድ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ሁሉም የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንደተደረገላቸውና ውጤቱ እየተጠበቀ መሆኑንም እንዳስረዳ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት እንደገለጸው ፍርድ ቤት ቶሎ ቶሎ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገቢ ነው፡፡ ምስክሮችንም በተራ በተራ ባልተቆራረጠ ሁኔታ መሰማት አለባቸው፡፡ የተጠርጣሪዎችን አያያዝ በሚመለከት ግን የፌዴራል ፖሊስ እስረኞች አስተዳደር ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተጠርጣሪዎቹን የምርመራ ውጤት እንዲያሳውቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ከኮሮና ነፃ በሆኑት ተጠርጣሪዎች ላይ የተቆጠሩት ምስክሮችን ዓቃቤ ሕግ ለነገ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. አቅርቦ እንዲያሰማ ቀጠሮ መስጠቱን ዓቃቤ ሕግ ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...