Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእነ አቶ እስክንድር ነጋ ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን አስመዘገቡ

በእነ አቶ እስክንድር ነጋ ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን አስመዘገቡ

ቀን:

መንግሥት ያቆመላቸውን ተከላካይ ጠበቃ ‹‹አንፈልግም›› ብለው አሰናብተዋል

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ፣ ለሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮልና በወ/ሮ ቀለብ ስዩም ላይ ከቆጠራቸው ሰባት ምስክሮች ውስጥ አራቱን በቀዳሚ ምርመራ መዝገብ አስመዘገበ፡፡

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠርጥረው በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ማስረጃ ሲሰበስብባቸው በከረሙት የተጠቀሱት ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን በፍርድ ቤት ለማረጋገጥና አስጠብቆ ለማቆየት የቆጠራቸውን ምስክሮች ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲያሰማ  ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በትዕዛዙ መሠረት ዓቃቤ ሕግ ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. አራት ምስክሮችን ያቀረበ ሲሆን፣ ሁለቱ በአቶ እስክንድር ላይ፣ ሁለቱ ደግሞ በአቶ ስንታየሁ ላይ መስክረዋል፡፡ በወ/ሮ ቀለብ ላይ ምስክርነት አልተሰጠም፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ምርመራ የተገኘን የምስክሮችን የምስክርነት ቃል ማስረጃ ጠብቆ ለማቆየት፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት በከፈተው የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ስለሚያቀርብላቸው ምስክሮች እነ አቶ እስክንድር ነጋ ያቀረቡት መቃወሚያ በፍርድ ቤት ውድቅ በመደረጉ ጠበቆቻቸውን አሰናብተዋል፡፡

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተፈጠረው የሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ወ/ሮ ቀለብ ስዩም ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ተቃውሞ፣ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 669/03 በመጥቀስ ከሚያቀርባቸው ሰባት ምስክሮች ውስጥ ሦስቱ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩና አራቱ ምስክሮች ደግሞ በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ  ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ በፖሊስ የተገኘው የምርመራ ውጤት በቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ላይ በፍርድ ቤት እንዲጠበቅለት ለማስደረግ የወሰነበት ሰነድና የምስክሮች ስም ዝርዝር ሊደርሳቸው እንደሚገባ ጠይቀው ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ አዋጅ ቁጥር 699/03 ጠቅሶ ስለ ምስክሮች ጥበቃ የገለጸ ቢሆንም፣ አዋጁ ስለቀዳሚ ምርመራ ሥርዓት ምንም የሚጠቅሰው ነገር ስለሌለና ጥያቄው የሕግ ድጋፍ የለውም ተብሎ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ በምስክሮቹ ላይ ጥበቃ ሊደረግ የሚገባውም በአዋጁ አንቀጽ 3(1ሀ) ድንጋጌ መሠረት የወንጀሉ ድርጊት ያለምስክሩ በሌላ መንገድ ሊረጋገጥ የማይችል ከሆነ ብቻ እንደሆነ ቢጠቅስም፣ ይህንን ግን ዓቃቤ ሕግ አለመግለጹን ጠቁመው የአዋጁን መስፈርት ባላሟላበት ሁኔታ ሊፈቀድለት እንደማይገባም በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 3(1ለ) ተደንግጎ እንደሚገኘው በምስክሮቹ ላይ ከባድ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ሲታመን ለምስክሮቹ ጥበቃ እንደሚደረግ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ‹‹በምስክሮቼ ላይ ከባድ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል›› ከማለት ባለፈ ድምዳሜ ላይ ስላደረሰው ነገር ማስረጃ አለማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡ እንዲያውም በአዋጁ አንቀጽ 6(1) ድንጋጌ መሠረት ጥበቃ የሚደረግለት ምስክር (ሰው) ጥበቃ እንዲደረግለት ራሱ ማመልከቻ እንዲያቀርብ እንደሚገልጽ ጠቁመው፣ ዓቃቤ ሕግ በራሱ ተነሳሽነት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ስለሌለውና የሕግም መሠረትም ስለሌለው ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

የመቃወሚያ አቤቱታቸውን የተመለከተው ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ ምላሽ እንዲሰጥበት ጠይቆ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ እንዳብራራው፣ ምስክሮቹ ሥጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ አዋጁም ሚኒስትሩ (ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) ለፍርድ ቤት እንደሚያሳውቅ ስለሚገልጽ ያንን ማሳወቁንም ጠቁሟል፡፡ ምስክርነቱ በግልጽ ችሎት የሚሰማ ቢሆን ኖሮ ለፍርድ ቤት ማመልከት እንደማያስፈልገው ገልጾ፣ ዋናው ዓላማ ማስረጃን ማስጠበቅ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው በቡድን መሆኑን የገለጸው ዓቃቤ ሕግ፣ ምስክሮቹ በማመልከታቸውና ከወንጀሉ አንፃር ጉዳት እንደሚደርስም ምዘና ተደርጎበት የቀረበ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ምስክሮቹ የተጠርጣሪዎችን መብት ለመጉዳት ሳይሆን እውነቱንና የደረሰውን ወንጀል ብቻ በሚመለከት የሚመሰክሩ መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጾ፣ እነሱም ቢሆኑ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነታቸው የመጠበቅና ከለላ ሊሰጣቸው እንደሚገባም አስረድቷል፡፡ ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል በመግለጽ፣ ፍርድ ቤት ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ካላደረገ በስተቀር በተደራጀ ቡድን ውስጥ ምስክርነት መስጠት እንደማይፈልጉ መናገራቸውን አስታውቋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ጉዳቱ በማኅበረሰቡ ላይ የደረሰና ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የወንጀል ድርጊቱ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገና ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ  ከባድ የወንጀል ድርጊት በመሆኑ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ መክፈት እንዳስፈለገው ጠቁሞ፣ ድርጊቱ በአገር ሰላምና በሕዝብ ደኅንነት ላይ የተቃጣ ከመሆኑ አንፃር የምስክርነቱን ሐሳብ እንጂ የምስክሮቹን አካላዊ ቁመና ማወቅ ከተጠርጣሪዎቹ መብት ማጣት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ በማስረዳት ምስክሮቹ በአዋጅ ቁጥር 699/03 ድንጋጌ መሠረት ጥበቃ ተደርጎላቸው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር ከአንቀጽ 80 እስከ አንቀጽ 93 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች መሠረት እንዲሰሙለት ጠይቋል፡፡ ምንም እንኳን ተጠርጣሪዎቹ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) ድንጋጌ የተሰጣቸውን መብት እንደሚያሳጣቸው የገለጹ ቢሆንም፣ ይህ የመብት ጥያቄ መነሳት ያለበት በከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚመሠረት ክስ ላይ መሆኑንና የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎትም አስገዳጅ ትርጉም እንደሰጠበት ተናግሯል፡፡

የእነ አቶ እስክንድር ጠበቆች በድጋሚ ባቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ እንደተናገሩት፣ መከላከል ማለት በምስክር ማንነት ላይ መከራከር ነው፡፡ ይህ በየትኛውም ዓለም የሚደረግ ነው፡፡ የምስክሩን ባህሪ ፊት ለፊት በማየትና ማንነቱን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ጐስት መሰከረ›› በሚል ደረጃ መሆን የለበትም፡፡ የምስክሩን ሙሉ ስምና ማንነቱን የማወቅ መብት እንዳላቸውና ተገቢም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በብይኑ እንደገለጸው፣ ዓቃቤ ሕግ ቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ሊከፍት የቻለው በወንጀለኛ ሕግ ሥነ ሥርዓት ከአንቀጽ 80 እስከ አንቀጽ 93 ድንጋጌዎች በተሰጠው የሕግ መሠረት ነው፡፡ የምስክርነቱ አስፈላጊነት ማስረጃን ከመጠበቅ አንፃር እንጂ ፍርድ ቤቱ መርምሮና አጣርቶ ውድቅ የሚያደርገው ወይም ውሳኔ የሚሰጥበት አይደለም፡፡ የማጽናትና ውድቅ የማድረግ ሥልጣን ደግሞ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) ድንጋጌን በሚመለከት መደበኛ ክስ ሲቀርብ የሚሰጥ አስተያየት መሆኑንና ክስ ባልቀረበበት ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ መብት ታልፏል ሊባል እንደማይችል ተናግሯል፡፡ ክስ ባልቀረበበት ሁኔታ ሕገ መንግሥቱን ጠቅሶ ተቃውሞ ማቅረብም እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ማስረጃ መቀበል አለመቀበል፣ ማስረጃን የመመዘንና ያለመመዘን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም አዋጅ ቁጥር 699/03 የተጠቀሰው ምስክሮችን ከመጠበቅ አንፃር የተነሳ ጥያቄ በመሆኑና ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመውታል የተባለው ወንጀል በሚቀርቡት ምስክሮች ብቻ የሚረጋገጥ ሳይሆን በከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ የሚመረመር ከመሆኑ አንፃር የተጠርጣሪዎች አቤቱታ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግሯል፡፡ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰሙት የሚደርስባቸው ጉዳት አዋጁ ከግምት ውስጥ አስገብቶ የተደነገገ በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱም ያመነበት ከመሆኑ አንፃር በመሆኑና በአዋጁ አንቀጽ 5(3) ድንጋጌ መሠረት መስቀለኛ ጥያቄ የሚቀርበው ክስ ከተመሠረተ በከፍተኛው ፍርድ ቤት በመሆኑ እንዳልተቀበለው ገልጾ መቃወሚያውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ሦስት ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩና አራት ምስክሮች ደግሞ በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩ ብይን ሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዴት እንደሚያቀርብ ፍርድ ቤቱ በመጠየቅ ላይ እንዳለ አቶ እስክንድር በመሀል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከብይን በኋላ ይግባኝ ከማለት ባለፈ መናገር እንደማይቻልና ዕርምጃ እንደሚወስድ እየተናገረ፣ አቶ እስክንድር ንግግሩን ቀጥሎ እንደገለጸው፣ ይህ የወንጀል ጉዳይ ወደ ዘር ማጥፋት ያዘነበለ ነው፡፡ በመሆኑም የክስ ሒደቱ መሰማት ያለበት በግልጽ ችሎት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በተቃራኒው ቢወስንም በዝግ ችሎት መታየት የለበትም፡፡ ነገር ግን  ፍርድ ቤቱ  በዝግ ችሎት መሆን እንዳለበት ብይን በመስጠቱ ሦስቱም ተጠርጣሪዎች የሒደቱ አካል ላለመሆን መወሰናቸውን ተናግሯል፡፡ በመሆኑም ጠበቆቻቸውን ከዕለቱ ጀምሮ ማሰናበታቸውንና እንደማይፈልጓቸውም ተናግሯል፡፡ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲመለሱና በሌሉበት ምስክርነቱ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ መሰናበታቸውን በሚመለከት ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ፣ የጥብቅና አገልግሎት በውል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ደንበኞቻቸው (ተጠርጣሪዎቹ) እንደማይፈልጓቸውና እንዳሰናበቷቸው በመናገራቸው አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎቹ በፈለጉት ሰው የመወከል ሕገ መንግሥታዊ መብትም ስላላቸው ይኸው ተመዝግቦ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሰጠው አስተያየት የሁሉም ተጠርጣሪዎች አቋም በመሆኑ፣ ወንጀሉ ከባድ ከመሆኑና በተጠርጣሪዎቹ ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት አንፃር መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ተደርጎ የምስክሮቹን ማሰማት እንዲቀጥል ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም፣ የጠበቆቹን መሰናበት አረጋግጦ፣ የመንግሥት ተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ለተጠርጣሪዎቹ የሚቆም ተከላካይ ጠበቃ እንዲመድብ ትዕዛዝ በመስጠት ለነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ዓቃቤ ሕግ አራት ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት ለተጠርጠሪዎቹ ተከላካይ ጠበቃ ተመድቦ የተሰየመ ቢሆንም፣ ተርጣሪዎቹ የሒደቱ አካል እንዳልሆኑና ተከላካይ ጠበቃውን እንደማይፈልጉት በመግለጻቸው ፍርድ ቤቱ አሰናብቶታል፡፡ በመቀጠልም ሁለት ምስክሮች በአቶ እስክንድር ላይ ሁለት ምስክሮች ደግሞ በአቶ ስንታየሁ ላይ መስክረዋል፡፡ በወ/ሮ ቀለብ ላይ ምስክርነት አልተሰጠም፡፡ እነ አቶ እስክንድር መስቀለኛ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ቢጠየቁም የችሎቱ አካል እንዳልሆኑና ምንም ነገር መናገር እንደማይፈልጉ በመግለጻቸው፣ ፍርድ ቤቱ ቀሪ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...