ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት በድርድር ለመፍታት ወደ ተቋረጠው ድርድር ለመመለስ መወሰኗ ተገለጸ።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የተጀመረው ድርድር ለሦስት ተከታታይ ጊዜ የተቋረጠ ሲሆን፣ ለድርድሩ መቋረጥም ሱዳንና ግብፅ የተለያዩ ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ ማቅረባቸው ነው።
ድርድሩ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ መቋረጡ ዳግም የመቀጠሉ ጉዳይን አጠያያቂ አድርጎት ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ድርድሩ ላትመለስ እንደምትችል ጭምር ስትገልጽ የነበረችው ሱዳን፣ ሰሞኑን አዲስ አቋም በመያዝ ወደተቋረጠው ድርድር ለመመለስ መወሰኗን አስታውቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ያቋቋሙትን የሱዳን ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሰበው ካነጋገሩ በኋላ፣ አገራቸው ወደ ተቋረጠው ድርድር እንድትመለስ መወሰኑን የአገሪቱ የውኃና መስኖ ሚኒስትር አባስ ያሲር በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
‹‹የተፈጠረውን አለመግባባት በድርድር ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ወደ ተቋረጠው ድርድር በመመለስ በሦስቱ አገሮች መካከል የጋራ መፍትሔ እንዲደረስ ተወስኗል፤›› ሲሉ የሱዳኑ ሚኒስትር ገልጸዋል።
በመሆኑም በቀጣይ በሚኖረው ድርድር የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር፣ እንዲሁም ከህዳሴ ግድቡ በላይ ወደፊት በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የውኃ ልማቶችን ያካተተ አጠቃላይ ስምምነት ሦስቱ አገሮች ለማድረግ እንደሚገናኙ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በድርድር የሚደረሰው ስምምነት ተፈጻሚነት የሚወሰንበት የሕግ ማዕቀፍም በድርድር ስምምነት እንደሚደረስበት ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሦስቱ አገሮች ዳግም ድርድራቸውን ለመጀመር ለሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዘዋል።
ሦስቱ አገሮችን እያወዛገበ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከተ ኢትዮጵያ የራሷን ሰነድ ከሁለት ሳምንት በፊት ያቀረበች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህንን ማድረጓን ተከትሎ ግብፅና ሱዳን ሰነዱን ለመመርመር ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ድርድሩ በተደጋጋሚ እንዲራዘም ማድረጋቸው ይታወቃል።
ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድቡ ድርድር አጀንዳዎች መካከል ኢትዮጵያ በቀጣይ በዓባይ ውኃ ላይ የሚኖራት የወደፊት የውኃ አጠቃቀም እንዲካተት መጠየቃቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ የወደፊት የዓባይ ውኃ በማንም ፈቃድ ላይ የሚመሠረት እንደማይሆን ፅኑ አቋም የያዘች ሲሆን፣ የወደፊት የውኃ አጠቃቀም ከተነሳ ሁሉንም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የሚመለከት የውኃ ክፍፍል ስምምነት መደረግ አለበት የሚል አቋም ይዛለች።
ወደዚህ የሚገባ ከሆነ ደግሞ ሌሎቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2010 የፈረሙት ነገር ግን ግብፅና ሱዳን ረግጠው የወጡት የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ዶሴን የሚከፈትባቸው ይሆናል።