Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ኢትዮጵያን የእኩልነትና የነፃነት አገር የማያደርግ ሥርዓት ፋይዳ ቢስ  ነው!

  በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እኩልነት፣ ነፃነት፣ ፍትሕ፣ ሰላምና ደኅንነት የሚያስገኝ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ መገንባት ያለበት ሥርዓት ዕውን መሆን የሚችለው፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ያለ ምንም ይሉኝታ ተነሳሽ ሲሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከድህነት፣ ከኢፍትሐዊና አምባጓሮ ከበዛበት አኗኗር ውስጥ በፍጥነት መውጣት አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣኑን በተረኝነት ስሜት እየዘወሩ አድልኦና መገለል ከሚፈጥሩ ራስ ወዳዶች መገላገል አለባቸው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ እየተኖረ አንዱ ባለቤት ሌላው መጤ የሚሆንበት አስነዋሪ ሥርዓት መገታት አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በብሔራቸው፣ በእምነታቸው፣ በቋንቋቸው፣ በባህላቸው፣ በፖለቲካ አቋማቸውና በመሳሰሉት ልዩነቶች የሚከፋፍል ሥርዓት ሊኖር አይገባም፡፡ ማንነትን ከመሬት ባለቤትነት ጋር አዳብሎ አድልኦና መገለል የሚፈጥር ሥርዓት፣ ግጭት ከመቀስቀስ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በየደረሱበት ባለቤትና ባይተዋር የሚያደርግ ሥርዓት ለሰላም ጠንቅ ከመሆን ባለፈ፣ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የኖሩ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን እያፈራረሰ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ለአገራቸው በኅብረት ማስቆም የማይችል ሥርዓት ተወግዶ፣ በነፃነትና በእኩልነት የሚኖርባት አገር እንድትኖር የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አለበት፡፡ 

  በዓለም ላይ የተዋጣለት የፌዴራል ሥርዓት የገነቡ አገሮች አሉ፡፡ በፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ስም ‹‹አፓርታይድ›› የሚመስል ነውረኛ ድርጊት ፈጽመው የፈራረሱ አገሮችም አሉ፡፡ ‹‹ብልህ ከሌሎች ስህተት ሲማር ሞኝ ግን ከራሱም አይማርም›› እንዲሉ፣ አገር የሚያፈርስና የሚበታትን የፌዴራል ሥርዓት ቅርፅና ይዘት ላይ ሙጭጭ ያሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊያንን በእኩልነትና በነፃነት የሚያስተናግድ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለመገንባት የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የፈረንሣይና የመሳሰሉ የተሳካላቸውን አገሮች ምሳሌዎች በማቅረብ የሚያሳስቡ አሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ዩጎዝላቪያ ዓይነት የቁልቁለት መንገድ ካልያዝን የሚሉ ናቸው አገር እያመሱ ያሉት፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ተወደደም ተጠላ አሀዳዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ምንም ዓይነት አመቺ ሁኔታ የለም፡፡ አለ ብለው የሚከራከሩ ካሉም እነሱ ከዘመኑ ጋር እየተራመዱ አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊያን ሥልጡን በሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እየተማሩና እየተዳኙ፣ ከአካባቢያቸው እስከ መላ አገሪቱ በነፃነት እየተንቀሳሱና እየሠሩ፣ ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብቶቻቸው እየተከበሩ፣ ወዘተ በጋራ የሚያኖራቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያዳግታቸው ምንም ነገር የለም የሚባለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለዘመናት አብረው በፍቅር፣ በመተሳሰብና በአርቆ አስተዋይነት መኖራቸው ምስክር ነው፡፡

  በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የብልፅግና ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ኢትዮጵያውያንን በእኩልነትና በነፃነት ሊያኖር የሚያስችል ሥርዓት ግንባታ ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በፓርቲዎች መካከል ይስተዋል የነበረው የተበላሸ ግንኙነት በፍጥነት ታርሞና ተስተካክሎ፣ ለሰጥቶ መቀበል መርህ የሚያስገዛ ዘመናዊ ግንኙነት መመሥረት ይኖርበታል፡፡ ገዥው ፓርቲ እንዳሻው የሚፈነጭበትና ግለሰባዊ ተክለ ሰብዕና ላይ የሚተኮርበት ኋላቀር የፖለቲካ ባህል መቀየር አለበት፡፡ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ጠያቂ የሌለበት ይመስል እንዳሻው ሥልጣኑን ሲባልግበት፣ ለሥልጣን የሚፎካከረው ደግሞ ምኅዳሩ ተዘጋግቶበት ሳይወድ በግድ ሴራና አሻጥር ውስጥ የሚገባበት ብልሹ አሠራር መወገድ ይኖርበታል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የአምባገነኖችና የከሰሩ ፖለቲከኞች መናኸሪያ ሆኖ የቆየውና አሁንም ከዚያ አባዜው መላቀቅ ያልቻለው፣ ለሥልጡን የፖለቲካ መስተጋብር የተሰጠው አክብሮት በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ነው፡፡ በአጋጣሚ የተገኘን ሥልጣን መከታ በማድረግ አንደበታቸውን መግራት ከማይችሉ እንጭጭ ፖለቲከኞች ጀምሮ፣ ዕድሜ ልካቸውን ካለፉት ስህተቶቻቸው መማር የማይፈልጉ ጎምቱዎች ድረስ እርማት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለሁሉም የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር እነሱ ባላቸው ቁመና መሠረት እንደማትገነባ ሊረዱ ይገባል፡፡

  ብልሆች ፖለቲካን በጥበብ ሲዘውሩት ሙቀቱ ወይም ቅዝቃዜው ለሰስና ነፈስ እያለ ይሰማ ይሆናል እንጂ፣ እንደ በረሃ ንዳድ ወይም እንደ ደጋ ውርጭ አቅል እያሳተ ለአደጋ አያጋልጥም፡፡  በሌላ በኩል ፖለቲካን ድንገት ዘው ብለው የገቡበት ወይም ከማን አንሼ በማለት የሚላላጡበት ደግሞ፣ ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው የባህር ማዕበልና የሰደድ እሳት እየሆነ ያገኘውን ሁሉ ያናውፃል ወይም ይለበልባል፡፡ የዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጠ ሚስጥሩ የገባቸው ስክነትንና ብልኃትን ስንቃቸው ሲያደርጉ፣ አርቆ ማየት የተሳናቸው ግን የስህተት አረንቋ ውስጥ ይዳክራሉ፡፡ ከበርካታ ዓመታት ውጣ ውረዶች በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለው እጅግ በጣም ጥቂት የሚባሉ ፖለቲከኞች ብስለት ሲሆን፣ እጅግ በጣም ብዙ የሚባሉት ግን አድሮ ቃሪያ እየሆኑ ነው፡፡ ብልሆቹ እንደ ወቅቱ ሁኔታ ረቀቅና ለዘብ እያሉ ምክንያታዊነትን ሲያሳዩ፣ ለዚህ ያልታደሉት ግን ስሜታቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው ችግር ይፈጥራሉ፡፡ ብልሆቹ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሲጠቀሙበት፣ እነዚያ ግን ለእንዲህ ዓይነቱ ዕይታም ሆነ ምልከታ ባዕድ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚፈልጉት ግን በእኩልነትና በነፃነት የሚያኖራቸውን ሥርዓት የሚያዋልዱላቸውን ፖለቲከኞች እንደሆነ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡

  እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚፈለገው ፖለቲካን ከኮረንቲ ጋር እያነፃፀሩ ከሚሸሹት ጀምሮ፣ ፖለቲካን ከቁማር ጋር እያስተሳሰሩ የሴረኞች መጫወቻ ካርድ ለማድረግ እስከሚፈልጉ ድረስ የማያግባቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ ነገር ግን ፖለቲካን በሠለጠነ መንገድ ሥራ ላይ በማዋል ለአገር ግንባታ የሚጠቀሙበት እንዳሉ ሁሉ፣ ጽንፈኛ ሆነው አገርን ለአደጋ በማጋለጥ የሕዝብን ሕይወት ማመሰቃቀል የሚፈልጉ መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ እርግጥ ነው ፖለቲካ በመርህ መመራት ቢኖርበትም፣ ለሥልጣን በሚደረግ ፉክክር ሴረኝነት መኖሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካን የሴራ መቆመሪያ በማድረግ ብቻ ለግጭትና ለውድመት ማመቻቸት፣ አገርን ለመገንባት ሳይሆን ለማፍረስ አመቺ መደላድል ይፈጥራል፡፡ ይሁንና ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ ፖለቲከኞች ፖለቲካን ለልዩነትና ለክፍፍል አይጠቀሙበትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት፣ ለጋራ ዕድገት ራዕይና ፍላጎት የሌላቸው ፖለቲከኞች በመበራከታቸው ነው፡፡ ለእኩልነትና ለነፃነት የሚተጉ ኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞች በተቻለ መጠን ከፋፋይና በታኝ አስተሳሰቦችን በማሸነፍ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የምትመች አገር ግንባታ ላይ ቢያተኩሩ ይመረጣል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሪቱ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት በመሆኑ ሊከበር ይገባዋል፡፡ በስሙ መነገድና መቆመር፣ ማንነቱንና እምነቱን እየታከኩ ንፁኃንን መግደልም ሆነ ንብረት ማውደም አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡

  ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መታገል ያለባቸው በእኩልነትና በነፃነት የሚያኖራቸው ሥርዓት እንዲገነባ ነው፡፡ እርስ በርስ እየለያየና እየከፋፈለ የሚያባላቸው የፖለቲካ ሥርዓት አይጠቅማቸውም፡፡ ይህንን በክፋትና በሸፍጥ የተሞላ ሥርዓት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሴረኞች ሕዝቡን በብሔር፣ በእምነት፣ በባህልና በመሳሰሉት ልዩነቶች እየከፋፈሉ የሚያባሉት ሥልጣኑ ላይ ተደላድለው በመቀመጥ ለዘረፋ እንዲመቻቸው ብቻ ነው፡፡ ሕፃናት ምግብ አጥተው በረሃብ የሚሞቱባት፣ በርካታ ሚሊዮን ወጣቶች በሥራ ዕጦት ቁም ስቅላቸውን የሚያዩባት፣ በቀን አንዴ ለመብላት መከራ የሚታይባት፣ ጥቂቶች ተመራርጠው ከብር አልፈው ሚሊዮን ዶላሮችና ዩሮዎች የሚቆጥሩባት የመከራ አገር እንድትኖር የሚጥሩ ጽንፈኞችን በሐሳብ መታገል የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ልጆቿ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ጤናማና ንፁህ መኖሪያ፣ ተመጣጣኝ ምግብ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና የመሳሰሉት የሚቋደሱባት አገር መሆን ትችላለች፡፡ ዴሞክራት ልጆቿ ለአገር አንድነት በኅብረት ሲነሱ ጽንፈኞች ይከስማሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙሉ ትኩረታቸውን ዴሞክራሲያዊት አገር ግንባታ ላይ ሲያደርጉና ውጤቱም መታየት ሲጀምር፣ ለሥልጣን ሲሉ ግጭትና ውድመት የሚያቀነቅኑ ኃይሎች ፋይዳ ቢስ ይሆናሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚኖሩበት ሥርዓት መገንባት አለበት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ዕርምጃ መራመድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፋይዳ የለውምና!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...