Tuesday, March 5, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች ሀብት 88 ቢሊዮን ብር መሆኑን መንግሥት የቀጠረው ኩባንያ አመለከተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የስኳር ፋብሪካዎቹ የባንክ ዕዳ ወለድን ሳይጨምር 155 ቢሊዮን ብር በላይ ነው

መንግሥት ስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዘዋወር የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል የሁሉም ፋብሪካዎች አጠቃላይ ሀብት ግመታን እንዲያከናውን የተቀጠረው የእንግሊዙ ቡከር ቴት የተባለው ኩባንያ ሥራውን አጠናቆ ለመንግሥት ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ የፋብሪካዎቹ አጠቃላይ ሀብትና ንብረት 88 ቢሊዮን ብር መገመቱን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አመለከተ። 

ሪፖርተር ያገኘው የሰነድ ማስረጃ እንደሚገልጸው የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ የስኳር ፋብሪካዎቹን አጠቃላይ ሀብት በተናጥል ቆጥሮ እንዲገምት የተቀጠረው ቡከር ቴት የተባለው ኩባንያ፣ ሥራውን አጠናቆ የሀብት ግመታ ሪፖርቱን ለገንዘብ ሚኒስቴር አስረክቧል። 

ኩባንያው ስኳር በማምረት ላይ የሚገኙትን ነባር ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም በግንባታና በከፊል የማምረት ሒደት ላይ የሚገኙትን 13 የመንግሥት ስኳር ፋብሪካዎች ሀብትና ንብረት ቆጥሮ የፋብሪካዎቹን የሀብት ግምት በተናጥል ለመንግሥት ማቅረቡን መረጃው ያሳያል። 

በዚህም መሠረት የ13ቱም ፋብሪካዎች አጠቃላይ ድምር ሀብት 88 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ሪፖርተር ከመረጃው ለመረዳት ችሏል። 

ኩባንያው የሀብት ግመታውን ሲያከናውን ታሳቢ ያደረጋቸው መረጃዎች ላይ መንግሥት ቅሬታ እንዳቀረበና ከግምት ያልገቡ መረጃዎች እንዲካተቱ ማመልከቱን መረጃው ያስረዳል። በዚህም ምክንያት የሀብት ግመታው ላይ የተሟላ መግባባት ተደርሶ ኩባንያው ሥራውን እንዳላስረከበ ለማወቅ ተችሏል። 

መንግሥት የሀብት ግመታውን ላከናወነው የእንግሊዙ ኩባንያ ቡከር ቴት የሀብት ግመታው ታሳቢ ሊያደርጋቸው ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች በመጥቀስ በዚሁ መሠረት ማስተካከያ እንዲደረግለት በጽሑፍ አስተያየቱን እንደላከ መረጃው ያመለክታል። ታሳቢ ሊደረጉ እንደሚገባቸውና በዚሁ መሠረት ማስተካከያ ከተጠየቀባቸው ጉዳዮች መካከል የሀብት ግመታው ኢትዮጵያ ለስኳር ልማት ኢንዱስትሪ ያላትን ተፈጥራዊ ዕምቅ ሀብት፣ ለሸንኮራ አገዳ ልማት በጣም ተስማሚ የሆነ መሬት፣ ውኃ፣ የአየር ንብረት፣ የሸንኮራ ምርታማነት እንዲሁም የሸንኮራ የስኳር ይዘት መጠን መካተት እንደሚገባ የሚገልጽ ነጥብ ይገኝበታል። 

ኩባንያው የሀብት ግመታውን ሲያከናውን ከላይ የተጠቀሰውን ለስኳር ኢንዱስትሪ ልማት ተስማሚ ሁኔታ አመላክቶ ከግምት ከማስገባት ይልቅ ትኩረት ያደረገው በፋብሪካዎች ወቅታዊ አቋም ላይ ብቻ መሆኑ የኢንዱስትሪውን ትክክለኛ ገጽታ ለኢንቨስተሮች የሚያሳይ አለመሆኑን በጽሑፍ ለኩባንያው አስታውቋል። 

በሌላ በኩል ኩባንያው የሀብት ግመታውን ሲሠራ ስኳር ፋብሪካዎቹ ወይም ፕሮጀክቶቹ ለውጭ ገበያ ምቹ መሆናቸውን ለማመልከት ከወደብ ያላቸውን ርቀትና ቅርበት ከግምት አለማስገባቱ፣ የሀብት ግመታው የማይዳሰስ ሀብት (Good Will) ከግምት ያስገባበት ሁኔታ አለመኖሩን በመጥቀስ ማስተካከያ እንዲደረግበት መንግሥት በጽሑፍ ጠይቋል። 

በተጨማሪም የሀብት ግመታው በፋብሪካው ይዞታነት ሥር ያለውን ዋነኛ ሀብት (መሬትን) ያካተተ ሆኖ አለመዘጋጀቱ ተገቢ ባለመሆኑ ማስተካከያ የተጠየቀበት ሌላው ነጥብ ነው። የአገር ውስጥ የስኳር ምርት ዓመታዊ ፍላጎት ከአሥር ዓመት በኋላ አንድ ሚሊዮን ቶን ሊደርስ እንደሚችል ሆኖ በኩባንያው የተሰጠው ግምት ከነባራዊ ዕውነታው በእጅጉ ያነሰና ግፋ ቢል በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚደረስበት መጠን በመሆኑ፣ እንዲስተካከሉ ጥያቄ ከቀረበባቸው ከላይ የተገለጹትና ሌሎች ነጥቦች መካከል ተካቶ ለኩባንያው መላኩን ለማወቅ ተችሏል። በእንግሊዙ ኩባንያ የተከናወነው የሀብት ግመታ የፋብሪካዎቹን የባንክ ዕዳ የተካተተበት አለመሆኑን ሪፖርተር ለማረጋገጥ ችሏል። 

ይሁን እንጂ ፋብሪካዎቹ ያለባቸውን የባንክ ዕዳ በተመለከተ ሪፖርተር ተጨማሪ መረጃ ያገኘ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የ13ቱም ፋብሪካዎች የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች አጠቃላይ ዕዳ ወለድን ሳይጨምር እ.ኤ.አ. በ2019 መጨረሻ ላይ 144 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑንና ይህ የዕዳ መጠን አሁን ላይ በውጭ ምንዛሪ ጭማሪ ምክንያት ብቻ 155 ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ከመረጃው መረዳት ይቻላል። 

እስከ 2019 መጨረሻ ወር ድረስ የሁሉም ፋብሪካዎች አጠቃላይ የአገር ውስጥ የብድር ዕዳ 81.6 ቢሊዮን ብር እንደሆነ፣ ይህም ወለድን እንደማያካትት መረጃው ያመለክታል። 

በተመሳሳይ ወቅት የነበረው የሁሉም ፋብሪካዎች የውጭ ብድር ቀሪ ዕዳ 2.1 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ይህም ወለድን እንደማይጨምር መረጃው ያመለክታል።  በወቅቱ በነበረው የውጭ ምንዛሪ ተመን መሠረት የውጭ ብድር ዕዳው 62.4 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን በመገመት አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር ዕዳው 144 ቢሊዮን ብር እንደሆነ መረጃው ያመለክታል። 

ነገር ግን የውጭ ብድር ዕዳው አሁን ባለው ኦፊሳላዊ የምንዛሪ ተመን ስሌት መሠረት ከ67 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን መገንዘብ ይቻላል። 

በአጠቃላይ መንግሥት ሁሉንም ፋብሪካዎች ለመሸጥ በያዘው ዕቅድ ቢሳካለት እንኳን የሚገኘው ገቢ ፋብሪካዎቹ ያለባቸውን የብድር ዕዳ ግማሹን መመለስ እንደማይችል አኃዞቹ ያስረዳሉ። 

የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪና የስኳር ፋብሪካዎቹ የፕራይቬታይዜሽን ሒደትን የሚመሩት ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ የሀብት ግመታውን የሠራው የእንግሊዙ ድርጅት የዓለም ባንክ አካል በሆነው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) በኩል የተቀጠረ መሆኑን ገልጸው፣ የስኳር ፋብሪካዎቹ የፕራይቬታይዜሽን ሒደት ጊዜ ሊወስድ የቻለው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው መሆኑን አመልክተዋል። 

ኩባንያው የሀብት ግመታውን አጠናቆ ለመንግሥት ያቀረበ መሆኑን የተናገሩት አማካሪው፣ በግመታ ሒደቱ ላይም ሆነ የመጀመርያ ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ መስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በርካታ ምክክሮች መደረጋቸውን ገልጸዋል። 

ኩባንያው ያቀረበውን የሀብት ግምት አኃዞች ከመግለጽ የተቆጠቡት አማካሪው ብሩክ (ዶ/ር)፣ ስኳር ፋብሪካዎቹ በተገመተው የሀብት መጠን ይሸጣሉ ማለት እንዳልሆነና ይህ የሚወሰነው ገበያው በሚሰጠው ዋጋ መሆኑን አመልክተዋል። 

ገበያው የሚሰጠውን ዋጋ የሚወስነው ደግሞ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ የገበያ ሁኔታዎች መሆኑን፣ ከእነዚህም መካከል የአገር ውስጥና ኢትዮጵያ ባለችበት አካባቢ ያለው የስኳር አቅርቦት እጥረት ወይም ከፍተኛ የምርት ፍላጎት አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል። 

ለዓብነትም በኬንያ ብቻ በዓመት የ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የስኳር ምርት ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል። በመንግሥት እጅ ከሚገኙት ፋብሪካዎች መካከል አሥሩ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲሸጡ መንግሥት መወሰኑንም አማካሪው ገልጸዋል። 

ስኳር ፋብሪካዎቹ ያለባቸው የባንክ ዕዳ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ቢሸጡ ዕዳቸውን መመለስ ይችሉ እንደሆነ የተጠየቁት ብሩክ (ዶ/ር)፣ በሽያጩ ከሚገኘው ሀብት ይልቅ ከሽያጭ በኋላ በሚኖረው ዕድል ላይ ከፍተኛ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። 

ከውጭ የሚገባውን የስኳር ምርት በማስቀረት የዶላር ወጪን መታደግ አንዱ ፋይዳ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በአካባቢው ያለው የስኳር ምርት እጥረት ደግሞ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢን እንደሚያስገኝ ገልጸዋል። 

በኦሞ ተፋሰስ ውስጥ ከሚገነቡት ፋብሪካዎች ከአንዱ ብቻ 25 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት እንደሚቻል፣ አንድ የስኳር ፋብሪካ ብቻውን የሚቀጥረው በሺዎች የሚቆጠር የሰው ኃይል ትልቅ የኢኮኖሚ አማራጭ መሆኑን በመጥቀስ ከሽያጭ በኋላ በሚኖረው ዕድል ላይ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። 

ፋብሪካዎቹን ወደ ግል ለማዘዋመር ከሚቀሩ ሒደቶች መካከል ለእያንዳንዱ ፋብሪካ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ማከናወን፣ የሸንኮራ አገዳ አብቃዮች የሚያቀርቡት አገዳ ዋጋና የስኳር ዋጋ ትመና ሥርዓትን ማበጀት የመሳሰሉት እንደሚቀሩ ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ሰፋ ያለ የፕራይቬታይዜሽን ዕቅድ በመያዝ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህ ዕቅድ ውስጥ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙት 13ቱም ስኳር ፋብሪካዎች በሽያጭ ወደ ግል ባለሀብቶች እንዲዘዋወሩ ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል። 

ከስኳር ፋብሪካዎቹ በመቀጠል የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግና የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትን በብቸኝነት እያቀረበ የሚገኘውን ግዙፉን ኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻ (ባለቤትነት) በሽያጭ ለግል ባለሀብቶች ለማስተላለፍ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። 

የኢንዱስትሪ ዞኖችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊልና በሙሉ በሽያጭ ለግሉ ዘርፍ ማስተላለፍም በመንግሥት የፕራይቬታይዜሽን ዕቅድ የተካተቱ ናቸው። 

በዚህ የፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራም በቀዳሚነት ወደ ግል እንዲዘዋወሩ የተወሰነባቸው የመንግሥት ስኳር ፋብሪካዎች ቢሆኑም፣ አማካሪው በገለጿቸው ምክንያቶች የተነሳ በተቀመጠው ፍጥነት መሄድ አልቻለም። 

ቅድሚያ እንዲሸጡ ከተባሉት የመንግሥት ስኳር ፋብሪካዎች ይልቅ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት የማድረጉ ሒደት ወደ ተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ተሸጋግሯል። 

በዚህም ለሁለት የግል የቴሌኮም ኩባንያዎች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ወጥቶ 12 የተመረጡ ድርጅቶች በውድድር ሒደት ላይ ይገኛሉ። የስኳር ፋብሪካዎቹ የሽያጭ ሒደት ቢጓተትም መንግሥት ያልተጠናቀቁ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታን በማጠናቀቅና በማምረት ላይ የሚገኙትንም የማምረት አቅም የማጎልበት እንቅስቃሴ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል እየተደረገ ነው።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች