Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየመከላከያ ሚኒስትሩ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው አልተነሱም

የመከላከያ ሚኒስትሩ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው አልተነሱም

ቀን:

ሪፖርተር በነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ሕትመቱና በድረ ገጹ የፖለቲካ አምድ ሥር ‹‹የመከላከያ ሚኒስትሩ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው መነሳታቸው ታወቀ›› በሚል ርዕስ መረጃን ማውጣቱ ይታወቃል፡፡

በዮሐንስ አንበርብር አዘጋጅነት የቀረበው ይህ ጽሑፍ የሚከተሉትን የተሳሳቱና ፍጹም ሐሰት የሆኑ መረጃዎችን አቅርቧል፡፡

1ኛ. ‹‹የኦሮሚያ ክልልን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ከአባልነታቸው መነሳታቸው ተጠቆመ›› ብሏል፡፡

2ኛ. ‹‹ክልሉን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ለማ መገርሳና ሌሎቹ ሁለት አባላት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነት እንዲነሱ የተወሰነው ጨፌ ኦሮሚያ ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ላይ እንደሆነም የሪፖርተር መረጃ ያመለክታል፤›› ብሏል፡፡

3ኛ. ‹‹አቶ ለማን ጨምሮ ሦስቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ተጓድለዋል በሚል ምክንያት ጨፌው ሌሎች አባላትን በመምረጥ እንዲተኩ ማድረጉን መረጃዎቹ አመልክተዋል፤›› በማለት የሐሰት መረጃን አሠራጭቷል፡፡

4ኛ. ‹‹…አቶ ለማን ተክተው የተመረጡትም በአሁኑ ወቅት የብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ኃላፊና በጨፌ ኦሮሚያ የክልሉ መንግሥት ተጠሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው፤›› የሚሉ መረጃዎችን ለንባብ አብቅቷል፡፡

ስለሆነም ሪፖርተር በቅድሚያ በሰጠው የተሳሳተ መረጃ አንባቢያንን ይቅርታ በመጠየቅና የእነዚህን መረጃዎች ምንጭ ማንነት በመግለጽ የሚከተሉትን ማስተካከያዎች በሪፖርተር ጋዜጣና በድረ ገጹ ፊት ለፊት ገጽ ላይ እንዲወጣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጨፌ ኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት በጥብቅ ያሳስባል፡፡

ሀ. ‹‹የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በመወከል አሁንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነት ያልተነሱ መሆናቸውን እናረጋግጣለን፡፡

ለ. ክልሉን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ብቻ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ጠይባ ሀሰንና ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) ቀድሞውንም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል አልነበሩም፡፡ ስለዚህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ያልነበሩ ሰዎችን ከአባልነት ተነሱ ብሎ መዘገብ ትልቅ ስህተት በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፡፡

ሐ. ከዚህም ሌላ ሦስቱ የሥራ ኃላፊዎች እንዲነሱ የተወሰነው ጨፌ ኦሮሚያ ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ላይ እንደሆነ የተገለጸውም በጣም የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ ምክንያቱም ጨፌው ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ጉባዔው በሥራና በትምህርት ምክንያት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ላይ መሳተፍ ባልቻሉ በተከበሩ አቶ ሙክታር ከድር፣ በተከበሩ አምባሳደር እሸቱ ደሴና በተከበሩ አቶ በከር ሻሌ ምትክ ነው፡፡ የጽሑፉ አዘጋጅ ይህንን በአግባቡ ጠይቆና አጣርቶ መረጃን ለአንባቢው መስጠት ሲችል በመላ ምትና የሕዝቡን ስሜት ሊኮረኩርልኝ ይችላል በሚል የተሳሳተ ግምት እንዲህ ዓይነት መረጃን በግድየለሽነት ማውጣቱ ትልቅ ስህተት ሆኖ አግኝቶታል፡፡

መ. በተጨማሪም ጨፌው የማስመሰልና የሐሰት ሥራን እየሠራ እንዳለ በማስመሰል ‹‹አቶ ለማን ጨምሮ ሦስቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ተጓድለዋል በሚል ምክንያት ጨፌው ሌሎች አባላትን በመምረጥ እንዲተኩ ማደረጉን መረጃዎቹ አመልክተዋል፤›› በማለት ጋዜጣው የጨፌውን ክብር በሚነካ ሁኔታ የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡

ሠ. በመጨረሻም የጋዜጣው ጸሐፊ የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳን ተክተው የተመረጡት የተከበሩ አቶ ፍቃዱ ተሰማ መሆናቸውን ያለ ምንም ተጨባጭ መረጃ በድፍረት መግለጹን ተመልክተናል፡፡ ችግሩን ይበልጥ ያከበደው ደግሞ ይህ የተሳሳተ መረጃ በሪፖርተር ጋዜጣና በድረ ገጹ ብቻ ተሠራጭቶ ያበቃ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህንን በስህተት የተሞላ መረጃ በርካታ የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች በምንጭነት ተጠቅመው ማሠራጨታቸው ነው፡፡

በመሆኑም ሪፖርተር ይህ ማሳሰቢያ እንደደረሰው ከላይ የተገለጸውን  ስህተት አስመልክቶ በይፋ ይቅርታ በመጠየቅና ጽሑፉን በጋዜጣውና በድረ ገጹ ላይ በማውጣት ዕርማት እንዲያደርግ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

(ሰማን አባ ጎጃም አባ ገሮ፣ የጨፌ ኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ)

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...