ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ‹‹የመከላከያ ሚኒስትሩ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው መነሳታቸው ታወቀ›› በሚል ርዕስ ያወጣነው ዘገባ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ መሆኑን የሪፖርተር ጋዜጣ የዝግጅት ክፍል እየገለጸ፣ አንባቢያንንና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤትን ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በመወከል አሁንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል መሆናቸውን የክልሉ ምክር ቤት የገለጸልን ሲሆን፣ ዘገባውን በዚሁ መሠረት ማረማችንን ለአንባቢያን በትህትና እናስታውቃለን፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ጉባዔው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ሆነው እንዲተኩ አቶ ፈቃዱ ተሰማ፣ አቶ ሳዳት ነሻና አቶ አብዱል ሐኪምን የመረጠ ቢሆንም፣ እነዚህ አባላት በትምህርት ምክንያት የተጓደሉ ሦስት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን እንዲተኩ መሆኑን ጨፌው አስታውቋል። በትምህርት ምክንያት በተጓደሉትና እንዲተኩ የተወሰነባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነትም አቶ ሙክታር ከድር፣ አቶ እሸቱ ደሴና አቶ በከር ሻሌ መሆናቸውን ጨፌው ካደረሰን መረጃ ለመረዳት ችለናል። ጨፌው ለሪፖርተር የላከውን ደብዳቤ ሙሉ ይዘት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ::