Friday, May 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ለመሆኑ ሊያ ካሳና ሊያ ታደሰ ማንና ማን ናቸው? ሁለቱን ሊያዎች ከተፀውኦ ስማቸው በስተቀር የሚያገናኛቸው ነገር ይኖር ይሆን? እንግዲህ እኔ ያለኝን ግርድፍ መረጃና በዚያ ላይ ተመሥርቶ የተቀረፀውን ምልከታዬን በአጭሩ ላቅርብላችሁና የራሳችሁን ደግሞ በራሳችሁ አክሉበት፡፡ ያችኛዋ ሊያ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አፈ ቀላጤ፣ ወይም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ናት፡፡

ይህችኛዋ ሊያ ደግሞ ማታ ማታ ‘ጤና ይስጥልኝ’ እያለች ወደየቴሌቪዥን መስኮቶቻችን ከፈገግታ ጋር ብቅ ስትል የምናውቃትና የቤተሰብ ብርቅዬ ወዳጅ ያህል የለመድናት የአገራችን የጤና ሚኒስትር ናት፡፡

የሰዎችን ተፈጥሯዊ ተመሳስሎሽና ተቃርኖ በጥሞና መታዘብ ምንኛ ያስደምማል ጎበዝ? እዚያ ማዶ ያለችው ሊያ ካሳ፣ ዓይኗን በጨው አጥባ መላ አገሪቱን ጨምሮ በክልሉ ውስጥ እንደሰደድ እሳት እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ በሽታ ለመከላከልና የወረርሽኙን አስከፊነት ለማኅበረሰቡ ይበልጥ ለማስገንዘብ እንዲያመች የልዩ ኃይሉን ሠራዊት ከታጠቀው ብሬን ጋር በአደባባይ ማሠለፍና በፉከራና በሽለላ የታጀበ ወታደራዊ ትርዒት ማሳየት ያለውን ጠቀሜታ ልታስረዳን የባጥ የቆጡን ትቀባጥራለች፡፡

- Advertisement -

እዚህ ማዶ ያለችው ሊያ ታደሰ ደግሞ፣ ውድ ወገኖቿ በአደገኛው ቫይረስ እንዳንጠቃባት ጭንቅ ጥብብ እያለች አስቀድመው በተጎዱባትና ይህችን ዓለም በሞት በተሰናበቱ ዜጎች ሕልፈተ ሕይወት ልቧ በመሪር ሐዘን እየተሰበረና እንባዋ እያቀረረ አካላዊ ርቀታችንን ጠብቀን እንድንቀመጥም ሆነ እንድንንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን አፍና አፍንጫዎቻችንን በማስክ እንድንሸፍን በየምሽቱ ያለመታከት አጥብቃ ትመክረናለች፣ ታስጠነቅቀናለችም፡፡ ምግባረ ብልሹነት አብዝቶ የተጣባት የምትመስለው የሊያ ካሳ ሐሰተኛና ይሉኝታ ቢስ መግለጫ እዝነ ህሊናን ክፉኛ ይበክላል፣ ያቆሽሻልም፡፡ ፍፁም ትህትናና የተሟላ ሥነ ምግባር የዘወትር ገንዘቧ ከሆነው ከሊያ ታደሰ ጥዑም አንደበት ግን የማር ወለላ ያለማቋረጥ ይፈሳል፡፡

እንደ መታደል ሆኖ ይህችኛዋ ሊያ ምሽቱን እየጠበቀች ወደየመኖሪያ ቤቶቻችን ብቅ ባለች ቁጥር የምትጠቀምባቸው ቃላት ምጥንና በወጉ የተመረጡ ናቸው፡፡ የዚያ ማዶዋ ሊያ ግን እንደ አንድ የሕዝብ ግንኙነት የበላይ ሹም መሽቶ በነጋ ቁጥር ድንገት ወደ ሚዲያ እየወጣች ባልተገራ አንደበቷ በመረጃ ስም የምትለቃቸው ፍሬ ፈርስኪ ወሬዎች ደረቅና በቀላሉ ተላምጠው የማይልሙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ሊያ ካሳ የእህልና ውኃ ነገር ሆኖባት “ሳትዋጋ ንገሥ ቢሉት ግድ ተዋግቼ” በማለት በወገኖቹ ላይ ጦር ለሚሰብቀውና ጠብመንጃ ለሚወለውለው ቡድን አድራ ዕድሜውን ለማራዘም ከጠዋት እስከማታ አንዳች መታከት ሳይታይባት እንደ ቁራ ስትጮህ እንከታተላታለን፡፡

ባለፈው ሐምሌ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በመቐለ፣ በማይጨው፣ በሁመራና በአላማጣ ከተሞች የተካሄደውን የጠብ አጫሪነት ትዕይንተ ሕዝብ ፀባይ አስመልክቶ ሴቲዮዋ ለመገናኛ ብዙኃን የሰጠችው የተዛባ መግለጫ የዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ የትግራይ ክልል ፀጥታ ቢሮ ራሱ “ሰላማችንን ለመጠበቅ ያለንን ዝግጁነት ያሳያል” ሲል ነበር ያንኑ ግዙፍ የታጣቂዎች ሠልፍ በተቃራኒው ተኩራርቶ በድረ ገጹ ላይ አሥፍሮት የተመለከትነው፡፡

ዶ/ር ሊያ ግን በኮቪድ 19 ምክንያት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳሰበው መሠረት ምርጫው እንዲራዘምና ለሕዝቡ ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥብቅና ትቆማለች፣ እማኝነቷንም በአደባባይ ለመግለጽ አልተሸማቀቀችም፡፡

ወ/ሮ ሊያ ካሳ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሰላም ውለን ማደራችን ራሱ ክፉኛ እየከነከናት የጦርነት ነጋሪት የሚጎሰምባቸውን የሕወሓት ተከታታይና የማያባሩ ድንፋታዎች ተቀብላ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በየዕለቱ እያስተጋባች ሥጋታችንን የበለጠ ታንረዋለች፡፡

ዶ/ር ሊያ ታደሰ ግን ምን ጊዜም ቢሆን ከመዘናጋት ተቆጥበን ራሳችንንና ቤተሰቦቻችንን ከወረርሽኙ ጥቃት እንድንከላከል በየደቂቃው እየወተወተች በሕይወት የመቀጠል ተስፋችንን ታለመልመዋለች፡፡

ወገኖቼ ምን አለፋችሁ?

ከተፀውኦ ስማቸውና ከፆታቸው በስተቀር እነዚህን ሁለት ቱባ እንስቶች የሚያመሳስላቸው ሳይሆን የሚያለያያቸው ባህሪ እንደሚያመዝን በቀላሉ ለመገንዘብ አያዳግተንም፡፡ ለነገሩ ‘የእናት ሆድ ዥንጉርጉር’ ሆኖ ነው እንጂ የዳር አገሯም ሆነች የመሀል አገሯ ሊያዎች ሁለቱም ከዋክብት እህቶቼ የትግራይ ማህፀን ፍሬዎች ናቸው መባልን በጭምጭምታም ቢሆን ሰምቻለሁ፡፡

አጃይብ ነው እኮ ዘመዶቼ!!!

(በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ፣ ከባህር ዳር)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ