Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያደፈጡ ሸፍጦች  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከሲቪክ ማኅበራት አመራሮችና ከተቋማቱ ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይታቸው ወቅትም በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር፡፡

ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ አብዛኞቹ በወቅታዊ የአገር ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አዳዲስ መረጃዎችን ያሰሙበትና ለብዙዎቹ ጥያቄዎችም የተፍታታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያና ምላሽ ውስጥ መንግሥት ከወቅቱ ችግሮች አኳያ በሕግ በማስከበር ረገድ እያከናወነ ስላለው እንቅስቃሴ ምላሽ ሲሰጡ እግረ መንገዳቸውን በአንዳንዶች የሚፈጸሙ ሸፍጦችን ጠቃቅሰዋል፡፡ በተለይም ከህዳሴው ግድብ ጋር የተገናኘ ከጠቀሱት ውስጥ አንዱ ተግባር በተለየ እንድመለከተው አድርጎኛል፡፡

ይኸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሳታፊዎቹ ስለ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመጎብኘት ያቀረቡትን ጥያቄ ሲመልሱ አስታከው የጠቀሱት አንድ ነጥብ ነው፡፡ ነገሩ በቅርቡ ከሲሚንቶ ግብይት ጋር ተያይዞ ከተፈጠረው የአቅርቦት ክፍተት ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ከፍ ብሎ ሲታይ ግን የህዳሴውን ግድብ ከማስተጓጎል ጋር ትስስር ያለው ሸፍጥ ተሠርቶ እንደነበር የሚያመለክት አንደምታ ያለው ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከሞላ ጎደል እንዲህ የሚል ነበር፡፡ ‹‹…ስለ ፕሮጀክቱ ብዙ ሰው የሚመስለው ዲፕሎማሲያችን ላይ ጫና የተፈጠረ፣ የዓለም ባንክ እንደዚህ አደረገ የሚል ነው፡፡ ያለፍንበት ጣጣ ጊዜው አልፎ የሚነገር ነው፡፡ ደርባ ሲሚንቶ ላይ የሚደረገው ጥቃት ዋናው ጉዳይ የህዳሴው ግድብ ለማስተጓጎል ነው፡፡ ደርባ ላይ ሰው ሞተ ነው የምትሉት እንጂ ለምን ሞተ የሚል ሰው የለም፡፡ ደርባ ላይ አስተዳደር አይደለም፡፡ ምርት ሥራ ላይ ይህ የሆነው፡፡ ምርቱ እንዲቋረጥ የተደረገ ሥራ አለ፡፡ ምርቱ ከተቋረጠ ግድቡ [የግንባታ ሥራ] ስለማይሞላ ማለት ነው፡፡ ይኼ አሁንም ይቀጥላል፡፡ ይህ እንዲፈጠር የተገዙ ሰዎች እንዳሉ ዓመቱን ሙሉ ስንናገር ነበር፡፡ ግን ፖለቲካዊ ስለሚሆን ሰው አይጠብቀውም…›› የሚል ንግግር አሰምተዋል፡፡

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ካቀረቧቸው ማብራሪያዎች ውስጥ ይህንን ነጥብ ለይቼ ማውጣት የወደድኩት፣ የአገራችን የግብይት ሥርዓት እንዲህ ያለ ሸፍጥ የሚፈጸምበት፣ አገር የሚሸጥበት መሆኑን ለማሳየት ይጠቅማል ብዬ በማሰቤ ነው፡፡ እንደምናስታውሰው የሲሚንቶ ገበያ ዝብርቅርቁ ወጥቶ ግራ ተጋብቶ ሰንብቷል፡፡

 ችግሩን ለመቅረፍ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ላይ ታች ሲል ከርሟል፡፡ እንዲህ ባለ ምክንያት ገበያው መበረዙንና ችግር መፈጠሩን ግን ብዙዎቻችን አናውቅም፡፡ ነገሮች በደንብ ከተመረመሩ እንዲህ ያሉ አስከፊ ተግባራት ገበያን መበረዝ ብቻም ሳይሆን፣ የአገር ጥቅም በምን መንገድ እንደሚጎዱ ያሳየናል፡፡ ገበያ የሚያዛቡ አካላት ሚናቸው እስከምን እንደሚዘልቅ ለመገንዘብ የሚያስችል አጋጣሚ ነው፡፡ ልንማርበት የሚገባን ይመስለኛል፡፡ የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረትና የገበያውን መመሰቃቀል በመረዳት ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ግብይቱ በተለየ መንገድ እንዲከናወን እስከመወሰን የደሰረው በወቅቱ ገበያው ውስጥ በተፈጠረው አስገራሚና ሆን ተብሎ በተፈጠረ ችግር ነበር፡፡ በወቅቱ የችግሩ መንስዔ ባይገልጽም ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መረዳት የተቻለው ግን በደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ በተፈጠረ ሸፍጥ ሳቢያ የምርት መስተጓጎል በማጋጠሙ እንደሆነ ልንገነዘብ ችለናል፡፡ ደርባ ሲሚንቶ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፋብሪካ ነው፡፡  

 ችግሩ እንዴት እንደተፈታ ባይነገረንም ሲሚንቶ ፋብሪካው ውስጥ የተፈጠረው ችግር ያመጣው የአቅርቦት እጥረት ግን ለህዳሴው ግድብም ሊተርፍ ችሏል፡፡  በፋብሪካው ውስጥ ተፈጠረ የተባለው ምርትን የማስተጓጎል ሸፍጥ ዋነኛ ጉዳይ ተደርጎ የተወሰደው የታላቁ ህዳሴ ግድብን የግንባታ ሒደት ለማደነቃቀፍ ታሳቢ ያደረገ ነበር ቢባልም ችግሩ ከዚህም ከፍ ብሎ አጠቃላይ በአገሪቱ የሲሚንቶ ግብይት ላይ ጭምር አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህ ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይብዛም ይነስም በሌሎች የግንባታ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ በግብይት ሥርዓትም ሆነ በአጠቃላይ ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደር ተፈልጎ የተደረገው ሙከራ ግን ለመንግሥት ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዲህ ያለው ነገር ነገም ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋልና እንዲህ ያለው አመለካከት ካለ ደግሞ ቀድሞ መዘጋጀትና ተመሳሳይ ድርጊቶች አይፈጠር የተቋማትም የመንግሥትም በአጠቃላይ ኃላፊነት ይጠይቃል ማለት ነው፡፡

ለተንኮል የማያሸልቡ አዕምሮዎች በተመሳሳይ በሌሎች ተቋሞችና በአጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን ሊበርዙ በሚችሉ ፅዩፍ የተግባራቸው ላለመሰማራታቸው እርግጠኛ መሆን እንደማይችል ተገንዝቦ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይነግረናል፡፡ ነገሩን ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የበኩሉን ማበርከት ይኖርበታል፡፡

ስለዚህ ይህ የማንቂያ ደውል መሆኑን ተረድቶ በሌሎች ተመሳሳይ የምርትና የአገልግሎት ተቋማት ውስጥ አጠቃላይ ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም አገልግሎቶችን እንዳይታጎሉ የሚያስችል ጥንቃቄ እንዲደረግ በሲሚንቶ ፋብሪካው ሆነ የተባለው ነገር ማስተማሪያ ይሁን፡፡

አሁንም የገዛ ወገኖቹ የሚገለገሉበትን ተቋም ላይ እሳት ለመለኮስ ያልተገራ ጥንቃቄ ላይ ወላጅ እናቱ አምጣ የወለደችበትን የጤና ተቋም ለማጋየት ያልተመለሰ አካል ባለበት አገር የተቋማትን ሥራ ለማስተጓጎል በገንዘብ የሚገዙ ጥቂቶች እዚህም እዚያ አይጠፋምና ተቋማትም ሠራተኞቻቸውን በአግባቡ መቆጣጠር በሥነ ምግባር የተላበሰ መልኩ ማነፅን ይጠይቃል፡፡

ሁሌም አገርንና ሕዝብን የሚያሳምሙ ፅዩፍ ተግባራት የሚፈጸምበት በጥቂቶች ስለመሆኑ ግልጽ ነውና እነዚህን ነቅሶ የማውጣቱ ሥራም ቸል መባል የሌለበት ነው፡፡ በደርባ ሲሚንቶ የተሞከረውን ሸፍጥ በሌላ መልኩ ካየነው ደግሞ የንግድ ተቋማት የግብይት ሒደታቸውንና አጠቃላይ አሠራራቸውን በሚገባ መፈተሽ ይጠይቃቸዋል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ ግን በአገራችን ውስጥ በግብይት ሥርዓት ውስጥ ችግር ሲፈጠር አንድ ምክንያት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ ምንም በሌለበት ሁኔታ ገበያው እሳት ሲሆን ችግሩ የውጭ ምንዛሪ ስለጠፋ ወይም ምርት ስለሌለ ብቻ ማሳበብ የሌለብን መሆኑን ነው፡፡

እንደተባለውም ችግሮቻችን የበዙ ናቸውና ገበያውን ለመረበሽ የሚፈጸሙ ሌሎች ተግባራቶች መኖራቸውን በማወቅ የመንግሥት የቁጥጥርና የክትትል ሥልትም ከጊዜው ጋር መራመድ ይኖርበታል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት