Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ መያዝ በሕግ እንደሚያስቀጣ ተደነገገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኮች ከውጭ መደበር ሊፈቀድላቸው ነው

በብር ኖቶች ላይ መጻፍ ሊያስቀጣ ነው

ግለሰቦችና ተቋማት በጥሬ ገንዘብ በእጃቸው መያዝ የሚችሉት መጠን ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳይሆን የሚደነግግ መመርያ ተግባራዊ መደረግ ጀመረ፡፡ ከዚህ ገንዘብ በላይ ይዘው በሚገኙ ላይ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አምስት የተለያዩ አዲስ መመርያዎችን ሥራ ላይ ለማዋል መዘጋጀቱን አስመልክቶ የባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ ማክሰኞ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ከዛሬ ጀምሮ ይተገበራል የተባለው መመርያ ግለሰቦችና ተቋማት በጥሬ ገንዘብ ከባንኮች ውጭ መያዝ እንዲችሉ የሚፈቅድላቸው መጠን ላይ ገደብ ተቀምጧል፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት በመኖሪያ ቤታቸው ወይም በተቋማቸው ውስጥ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ መያዝ አይችሉም ተብሏል፡፡ ከዚህ ገንዘብ መጠን በላይ ይዞ የተገኘም በሕግ እንደሚጠየቅ ገዥው አስታውቀዋል፡፡

እንደ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ ይህንን ገደብ ማስቀመጥ ያስፈለገው ግለሰቦችና ድርጅቶች በቤትና በመሥሪያ ቤቶቻቸው ውስጥ በርካታ ጥሬ ገንዘብ ስለሚያስቀምጡ የመጠን ገደብ ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ከባንኮች ውጭ ያለገደብ የሚከማቸው ገንዘብ ለሕገወጥ ተግባራት ማስፈጸሚያነት ሊውል የሚችለበት ሰፊ ዕድል በመኖሩ፣ ከግብር መሰወርና ከማጭበርበር ጋር በተያያዘ ምክንያትም ከባንኮች ውጭ ሊቀመጥ ስለሚችል፣ መጠኑ ላይ ገደብ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ገንዘብ በኢኮኖሚ ውስጥ መዘዋወርና ወደ ባንክ ሥርዓት ውስጥ መግባት አለበት ያሉት የባንኩ ገዥ፣ እንዲህ ያለውን ሕጋዊ ሥርዓት ለማዳበር መመርያው አስፈልጓል፡፡ አላግባብ የተቀመጠ ገንዘብ ለብልሽት ስለሚደረግም ጭምር መመርያው እንዲህ ያለውን ብክነት ለማስቀረት እንደሚያግዝ ተብራርቷል፡፡

በመሆኑም ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንኮች ውጪ በቤት ውስጥ ወይም በሌላ ቦታ ማስቀመጥ የተከለከለ መሆኑ ታውቆ ኅብረተሰቡ መመርያውን እንዲያከብር የብሔራዊ ባንክ ገዥው ጠይቀዋል፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለሥራና ለተለያዩ ጉዳዮች ጥሬ መጠቀም የሚፈልጉ ከዚህ በኋላ በቤት ወይም በድርጅት ውስት ማስቀመጥ የሚችሉት 1.5 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ተብሏል፡፡ ‹‹የሥራቸው ባህሪ አስገድዷቸው ወይም ይህንን ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ሁኔታ ነው፤›› ይህን ያህል ገንዘብ መያዝ የሚቻለው ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ በመሆኑም ሁሉም ግለሰብና ድርጅት ገንዘቡን በባንክ ማንቀሳቀስ አለበት ብለዋል፡፡  

ከተገለጸው ገንዘብ በላይ በቤት ውስጥ ወይም በሌላ ቦታ ይዞ መገኘት፣ በሕግ የተከለከለና ሕገወጥ ተግባር እንደሆነ ያሳሰቡት ገዥው፣ ይህንን መመርያ አለማክበር በሕግ እንደሚያስቀጣ አሳስበዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው በገለጹት መሠረት አምስት አዳዲስ መመርያዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም ባንኮች በውጭ ምንዛሪ እንዳይበደሩ የሚከለክለው ሕግ መነሳቱን የሚጠቅሰው አንደኛው መመርያ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ባንኮች  ከውጭ አበዳሪዎች እንዲበደሩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ምንጮችን ለማስፋት ታሳቦ የወጣ መመርያ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ከተለመዱት የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መንገዶች በተጨማሪ፣ ሌሎች አማራጮችን በመመልከት ባንኮች ከውጭ እንዲበደሩ ማስቻል  አንደኛው አማራጭ ተደርጓል፡፡ ባንኮች ከውጭ መበደር እንዳይችሉ ክልከላ ተደርጎባቸው የቆየበት ምክንያት የተለያየ እንደነበር ያስታወሱት፣ ይናገር (ዶ/ር)፣ ከነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ ይህ ክልከላ እንዲነሳ ማድረጉ ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት ተፈጻሚ ይደረጋል ብለዋል ነው፡፡

ለክልከላው መነሳት በምክንያትነት የተጠቀሰው አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃላል የሚያስችል አመራጭ ሆኖ በመታሰቡ ነው፡፡ መመርያው ሲተገበር፣ የግሉ ዘርፍ በተለይም የፋብሪካ ባለቤቶችና ሌሎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት በሙሉ አቅማቸው ማምረት ያልቻሉ ተቋማት አማራጭ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚችሉበት ነው፡፡ ስለዚህ ባንኮች ከውጭ እንዲበደሩ የሚያስችለው አሠራር ለምንዛሪ እጥረት መቀረፍ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ሳይፈታ ለዓመታት የመቆየቱ ዋነኛ ምክንያት የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ እንደሆነ የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ ችግሩን ለማቃለል የወጪ ንግድን ማሳደግ ዋናው ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  

ከወጪ ንግድ ባሻገር፣ ከውጭ ሐዋላ ገቢ፣ ከዕርዳታና ብድር፣ ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትና ከሌሎችም ምንጮች የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ ሲሆን፣ እንዲህ ያሉት የተለመዱ ዘዴዎች እንዳሉ ሆነው፣ ተጨማሪ ምንጮችን ለማየት እየተሠራ እንደሆነ፣ ከእነዚህ ሥራዎች አንዱም ባንኮች በውጭ ምንዛሪ የሚበደሩበትን አሠራር የሚፈቅደው መመርያ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ ይህ በመፈቀዱ ዳያስፖራው በብዙ መንገድ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ከውጭ ምንጮች መበደር በሚፈልጉበት ወቅት የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያስችል ገዥው ጠቁመዋል፡፡ በምሳሌ ሲያስረዱም ‹‹በእኛ አገር ኩባንያዎች የሚለኩበት ወይም የመበደር አቅማቸው የሚመዘንበት ሥርዓት ስለሌለ፣ ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓትና ሪፖርት ስለሌላቸው የውጭ አበዳሪዎች ለኢትዮጵያ ኩባንያዎች ብድር ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡ ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ የውጭ ብድርን በባንኮች በኩል እንዲያገኙ ለማድረግ ያሰበ መመርያ ነው፤›› ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ ከውጭ ምንጮች የሚገኘውን ብድር ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የተሻለው አማራጭ፣ በኢትዮጵያ ባንኮች በኩል በውጭ ምንዛሪ ብድር እንዲያገኙ ማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ግንኙነት ስላላቸውና ከዓለም ሥርዓት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው፣ ዓለምአቀፍ የሒሳብ ሪፖርት ደረጃና የታወቀ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት መከተል በመጀመራቸውና የውጭ አበዳሪዎች የሚፈልጋቸውን መሥፈርቶች በአብዛኛው የሚያሟሉ በመሆናቸው ክልከላውን ማስነሳት  እንዳስፈለገ ተጠቅሷል፡፡

በመሆኑም ባንኮች ከውጭ አበዳሪዎች የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙና ያገኙትንም ለኢትዮጵያውያን በተለይም የውጭ ምንዛሪ በሚያስፈልጋቸው ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች እንዲያቀርቡ የሚያግዝ መመርያ እንደሆነ ይናገር (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡  በውጭ አበዳሪና በኢትዮጵያ ኩባንያ መካከል የኢትዮጵያ ባንኮች እየተሳተፉ ብድሩን ከውጭ በማምጣት ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ድንጋጌዎችን መመሪያው እንዳሰፈረ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ከውጭ በሚመጣው ብድር ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ የባንኮች ብድር የመመለስ አቅም እንደሚታይ ተገልጾ፣ ብሔራዊ ባንክም ብድሩ ሲመጣ ከፍተኛ ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ መመርያውን ለማስተግበር ባንኮችን እንደሚገመግም ያመለከቱት ይናገር (ዶ/ር)፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሥጋቶች ወይም አደጋዎች ካሉ በክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንደሚለዩ ለዚህም አሠራር እንደሚዘረጋ፣ ባንኮችም በኃላፊነት እንዲሠሩ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

ሌላኛው መመርያ የግብይት ሥርዓቱን የተመለከተ ነበር፡፡ በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተውን ግብይት፣ በሰፊው በሚንቀሳቀሱ የቴክኖሎጂ ክፍያ ዘዴዎች መተካት የሚቻልበትና ከባንክ ውጭ የሆኑ ኩባንያዎች በኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ በሰፊው የሚሳተፉበትን አሠራር የሚፈቅደው መመርያ ነው፡፡

የኤሌክትሮኒክ ክፍያዎች በባንኮች ሲተገበር እንደቆየ የገለጹት ገዥው፣ በወጣው አዲስ መመርያ መሠረት ከባንክ ውጭ ያሉ ተቋማት ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓቶችን በማስተዳደር እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ድንጋጌ ነው፡፡

እንደ ኤትኤምና ፖዝ ማሽኖችን ማንቀሳቀስ የሚችሉት ባንኮች ብቻ ነበሩ፡፡ አገልግሎቱም ለባንኮች ብቻ የተፈቀደ ነበር፡፡ በአዲሱ መመርያ ግን ሌሎች ኩባንያዎች በኤትኤም፣ በፖስ፣ በስዊች ኦፕሬተርነትና በመሳሰሉት የክፍያ ሥርዓቶች ላይ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ወስደው እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡

የዲጂታልና የኤሌክትሮኒክ ክፍያዎችን በስፋት ተግባራዊ ለማድረግ ባንኮች ውጭ ያሉ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ማድረግ የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት ለማዘመን  አስተዋጽኦ ያበርክታል ተብሏል፡፡ ኢስዊች፣ ኤትኤም፣ ፖዝና ጌትዌይ በተባሉት አገልግሎቶች ላይ በኦፕሬተርነት መሳተፍ የሚፈልጉ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ለአገልግሎቱ የወጡትን መሥፈርቶች አሟልተው ፈቃድ ሲያገኙ መሳተፍ ይችላሉ፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ዜጎችም እንዲሳተፉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል ቢሆንም በአጠቃቀም ችግሮች ምክንያት ከአገልግሎት ጊዜው ቀድሞ የሚበላሸውን በርካታ ገንዘብ የሚመለከት መመርያም ተዘጋጅቷል፡፡ የብር ኖቶችና ሳንቲሞች ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው በውጭ ምንዛሪ ቢታተሙም፣ በአጠቃቀምና አያያዝ ጉድለት ሳቢያ እየተበላሹ ነው፡፡ ሆን ብለው የብር ኖቶችንና ሳንቲሞችን የሚያበላሹትን የሚቆጣጠር መመርያ መጥቷል፡፡ ‹‹በብር ኖቶች ላይ ጽሑፍ ይጽፋል፡፡ ይቀደዳል፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ ከፍተኛ የአያያዝ ችግር አለ፡፡ ይህ በመሆኑ ብር ቶሎ ቶሎ እየተበላሸ ነው፤›› ያሉት ገዥው፣ በዚህም ምክንያት የቆይታ ዕድሜው እያጠረ ከኦኮኖሚ ውጭ የሚደረግበት አጋጣሚ እየበዛ በመምጣቱና መልሶ ለመተካት ከፍተኛ ወጪ እየጠየቀ በመሆኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ ከአሁን በኋላ በብር ኖቶች ላይ መጻፍና ሌሎች ጉዳቶችን ማድረስ በሕግ ያስጠይቃል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች