የሜንሽን ፎር ሜንሽን መሥራች ነፍስ ኄር ካርል ሄንዝ (ዶ/ር)፣ እ.ኤ.አ. በ1981 በድርቅ ተፈናቅለው በምሥራቅ ኢትዮጵያ በባቢሌ ወረዳ በካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እንዳይጎዱ መልሶ ከማቋቋም ጀምሮ የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎች በመሥራት ይታወቃሉ፡፡ በርካታ ዜጎችን በመታደግ በጎ ተግባራቸውን ለዓለም ያሳዩት ዶ/ር ካርል ሄንዝ ለ35 ዓመታት የሚታይ ሥራ አበርክተዋል፡፡ ይህ አበርክቷቸው ሕያው እንዲሆን የዶክተር ካርል ሄንዝ መታሰቢያ በጎ አድራጎት ድርጅት ተቋቁሟል፡፡ ድርጅቱን ያቋቋመችው ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለአሥር ዓመታት በዓለም አቀፍ የጎዳና ሩጫና የማራቶን ውድድሮች ተወዳዳሪ የነበረችው ዓለም አሸብር ነች፡፡ ዓለም በ10 ኪሎ ሜትር፣ በግማሽ ማራቶንና ማራቶን በተለያዩ አገሮች በመወዳደር በአሸናፊነት የተወጣችባቸውና ተሸላሚ የሆነችባቸው ቁጥር ቀላል አይደሉም፡፡ ስለ በጎ አድራጎት ድርጅቱ እንቅስቃሴ የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ዓለም አሸብርን ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯታል፡፡
ሪፖርተር፡– የዶ/ር ካርል ሄንዝ መታሰቢያ በጎ አድራጎት ድርጅት መቼ ተመሠረተ?
አትሌት ዓለም፡- በጎ አድራጎት ድርጅቱ በሲቪል ማኅበራት ድርጅት ኤጀንሲ ተመዝግቦ ሕጋዊነት አግኝቶ ከተመሠረተ አምስት ወራት ሆኖታል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ላለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮ ካርል አትሌቲክስ ክለብ በሚል ስም፣ በእኔ መሥራችነት በአትሌቲክስ ዙሪያ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ኅብረተሰቡ የሚገጥሙትን ችግሮች ለመቅረፍና የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት አልሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡– ካርል ሄንዝ መታሰቢያ በጎ አድራጎት ድርጅት ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ምን ላይ ነው?
አትሌት ዓለም፡– በኢትዮጵያ በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍች ላይ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ዶ/ር ካርል የሠሯቸውን ሥራዎች በማስታወስና የሳቸውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማበርከትም መንገድ ላይ እንገኛለን፡፡ የሕክምና አገልግሎት ችግር በሆነባቸው ቦታዎች ላይ ሆስፒታሎችንና ጤና ጣቢያዎችን እንዲሁም በገጠራማ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና የትምህርት ተደራሽነት እንዲስፋፋ ለማድረግ ዕቅዶች ይዘናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በኢትዮጵያ የንፁህ ውኃ አቅርቦት በሌለባቸው አካባቢዎች ላይ ንፁህ ውኃ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ አሳዳጊ የሌላቸውንም ሕፃናት በመሰብሰብና በማሳደግ ከዚያም አልፎ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በበጎ አድራጎት ድርጅቱ ውስጥ ምን ያክል ሰዎች ይረዳሉ? ምን ዓይነት ድጋፍስ ታደርጋላችሁ?
አትሌት ዓለም፡– በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታዎች ላይ በመዘዋወር የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት እንቅስቃሴዎች ጀምረናል፡፡ ለ300 ታዳጊ ሕፃናትና ሴት አትሌቶችም ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ድጋፎችን አድርገናል፡፡ አቅም ለሌላቸው ጀማሪ አትሌቶች የስፖርት ትጥቅ አበርክተናል፡፡ ዶክተር ካርል የጀመሯቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በመደገፍና በማጠናከር ጉልህ ሚናዎችን እየተጫወትን ነው፡፡ ወደፊትም በርካታ የተቸገሩ ሕፃናትና ወጣቶችን ለመርዳት ከማኅበረሰቡ ጋር እጅና ጓንት ሆነን ለመሥራትና ኃላፊነታችንንም ለመወጣት የተለያዩ አቅጣጫዎችን ዘርግተናል፡፡ ይህም በትንሹም ቢሆን ችግሩን ለመቅረፍ ያስችለናል፡፡ ካልተባበርን የችግሩ አሳሳቢነት ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡-ድርጅቱ እየሠራ ያለው በክልሎች ላይ ነው ወይስ በአዲስ አበባ?
አትሌት ዓለም፡– ማኅበረሰቡ ውስጥ ጠልቆ በመግባትና የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታዎች ላይ በመንቀሳቀስ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት አልመን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይህንንም ለመሥራት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማደራጀት፣ ማኅበረሰቡን ተደራሽ ለማድረግ ኤስኤምኤስ ቁጥር 7,330 በይፋ በማስጀመር ሁሉም ሰው የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎችን በመሥራት ለተቸገሩ ሰዎች ድጋፍ እንዲውልም በጎ ጅምሮች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡– ሌላ የገንዘብ ድጋፍ ከየት ታገኛላችሁ?
አትሌት ዓለም፡– በአሁኑ ሰዓት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተለያዩ ሥራዎች ባለመሥራታችን የገንዘብ ችግር አጋጥሞናል፡፡ ከዚህ ቀደምም ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ አላገኘንም፡፡ በራሴ በኩል እየተሯሯጥኩ በማመጣው ገንዘብ ድጋፍ ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ማኅበረሰቡ እንዲያግዘኝና እንዲተባበረኝ እየጣርኩ ነው፡፡ የካርል መታሰቢያን ለማስቀጠል ሁሉም ሰው በመተባበር የበኩሉን መወጣት ይገባዋል
ሪፖርተር፡– ይህ የመታሰቢያ በጎ አድራጎት ድርጅት በቀጣይ ምን ለመሥራት አስቧል?
አትሌት ዓለም፡– ገጠራማ አካባቢዎች በመሄድ ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችንና የንፁህ ውኃ አቅርቦትን በመገንባት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ሥራዎችን ጀምረናል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንም ለማቋቋም ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ እንዲሁም የአትሌቲክስ ስፖርትን በማስፋፋት የተለያዩ ውድድሮችን በማዘጋጀት በውድድሩ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ ወጣቶችን በመመልመል ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትና የተሻለ ውጤት ያላቸው ወጣቶች ውጭ አገር ድረስ ሄደው እንዲወዳደሩ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ከሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በምን ዓይነት መልኩ እየሠራችሁ ነው?
አትሌት ዓለም፡– በአሁኑ ወቅት ከማንኛውም የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር እየሠራን አይደለም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በጎ አድራጎቱ በቅርብ ጊዜ የተጀመረ በመሆኑ ነው፡፡ ወደፊት ግን ከማኅበረሰቡና ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር የምንሠራ ይሆናል፡፡ በተለይም ካርል የሠሯቸውን ሥራዎች አጠንክረን የምንቀጥል ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ወጣቶቹ ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ የካርልን ውለታ በማሰብ ሰዎች የኔነት ስሜት በውስጣቸው ኖሮ ይህን የመታሰቢያ ድርጅት በገንዘብም ሆነ በጉልበት በመደገፍ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግም እየተሠራ ነው፡፡ በሳቸው ሥር አድገው ለቁም ነገር የበቁ ሰዎችን ወደዚህ ማዕከል በማምጣት በጎ ሥራዎችን እንዲሠሩ እየተደረገ ነው፡፡ ለበርካታ ኢትዮጵያውያንም ሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመሥራት ሁኔታዎችን አመቻችተናል፡፡
ሪፖርተር፡– የበጎ አድራጎት ድርጅታችሁ ምን ላይ ይገኛል?
አትሌት ዓለም፡– ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሥራዎችን እየሠራ አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላም የተለያዩ ስፖንሰሮችን በመፈለግ ያለብንን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ እስካሁንም እየሠራን የነበረው በራሳችን ተነሳሽነት ነው፡፡ አሁን ግን ማኅበረሰቡን ባማከለ መልኩ እንዲሆንና ሁሉም ሰው በበጎ አድራጎቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን መንገዶችን አመቻችተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በስፖርት ዘርፍ ያላችሁ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አትሌት ዓለም፡- ላለፉት አምስት ዓመታት በካርል ስም ለዓመታዊ ዝክራቸው የሩጫ ውድድሮች በማዘጋጀትና አሸናፊ አትሌቶችን በመሸለም ለቀጣይ ውድድሮች ተነሳሽነት እንዲኖራቸው አስችለናል፡፡ ስፖንሰር በማፈላለግ አቅም ለሌላቸው ታዳጊዎችና ወጣት አትሌቶች ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በውድድር እንዲሳተፉ ዕድል ፈጥረናል፡፡ በቀጣይም አትሌቲክሱ የበለጠ እንዲያድግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ጋር ለመሥራት ዕቅዶችን ይዘናል፡፡