በእስጢፋኖስ ስሜ
ተጭኖን የነበረ ቋንቋና ባህል ነበረ (አለ) አሽቀንጥረን መጣል አለብን በሚል ዘመኑን በማይመጥን በጃጀ ትርክት ላይ መሠረቱን ያደረገ ፖለቲካና የዚሁ መንታ ወንድም የሆነው፣ ‹‹ተረኛ›› ወይም ‹‹ተረኛው›› ባህልና ቋንቋውን በኃይል ሊጭንብ ነው በሚል ፍርኃት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካን ከሚፀየፉ ሰዎች መካከል ዋነኛው ነኝ፡፡
ምክንያቱም በውስጡ ያለው አመክንዮ ሳይሆን እኛና እነሱ፣ ጥላቻና ፍርኃት፣ ቂምና በቀል ስለሆነና ከመጠፋፋት ውጪ አንዱንም አሸናፊ የማያደርግ ርዕዮት በመሆኑ ነው፡፡
በእንዲህ ዓይነት የተንጋደደ ትርክት ላይ መሠረቱን ያደረገ የፖለቲካ አካሄድ አዕምሮን አደንዝዞ ስሜትን ደግሞ ያጦዛል፡፡ ያልተደረገን ነገር እንደ ተደረገ የተደረገን ነገር ላይ ጨምሮና አጋኖ፣ ትንሸ እውነትን ከብዙ ውሸት ጋር ደባልቆና ሸቅጦ የፖለቲካ ሜዳውን የሐሳብ ትግል የሚደረግበት ሳይሆን፣ በስሜት የሚጋለብበት ሰለሚያደርግ አይመቸኝም፡፡
አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ ይባላል፡፡ ሰውዬው ከጎረቤቱ ጋር ትንሽ ግጭት ይገባና ሊከሰው ፈልጎ የክስ ጽሑፉን እንዲከትብለት ወደ ፍርድ ቤት አካባቢ ወዳለ በዚህ አግልግሎት ወደ ተሰማራ ግለሰብ ጎራ ይላል፡፡ ከጎረቤቴ ጋር በትንሹ ተጋጭተን ነበር ብዙ ጉዳት አላደረሰብኝም፡፡ እኔም እንደዚያው ምንም እንኳ ለክስ የሚያደርስ ባይሆንም ተናድጄበታለሁ ልከሰው እፈልጋለሁና ጻፍልኝ አለው፡፡ አገልግሎት ሰጪውም ትንሽ ጊዜ ወስዶ ስሜት በሚነካ ቃላትና በተጋነነ ሁኔታ የጻፈውን የክሱን ጽሑፍ አነበበለት፡፡ ከሳሹም ስቅስቅ ብሎ ካለቀስ በኋላ፣ ‹‹ለካስ ይህን ያህል ተበድዬ ኖሯል›› አለ ይባላል፡፡
ከጎረቤቱ ጋር በነበረው ፀብ ያላለቀሰው ሰው ከጎረበቱ ጋር የነበረውን ፀብ በጻፈለት ሰው አምርሮ አለቀሰ፡፡ ለእኔ ‹‹ተጭኖብን›› ነበር ‹‹ሊጫንብ›› ነው የሚባለው ፖለቲካ ከዚህ ታረክ ፈፅሞ አይለይብኝም፡፡ የተጫነህ ወይም ሊጫንብህ ያለ ቋንቋና ባህል አለ በማለት ስሜትን እየኮረኮሩ ማስለቀስ የዕውቀት ፖለቲካ ሳይሆን የቁማር ፖለቲካ ነው፡፡ ቁማር ደግሞ የበይና የተበይ ጨዋታ ነው፡፡
ሲጀመር የእኛ ብቻ ቋንቋ ነው፡፡ የእኛ ብቻ ባህል ነው የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁሉም ሲሰጥና ሲቀበል፣ ሲያወርስና ሲወርስ ነው ዛሬ ላይ የደረሰው፡፡ አማራ ከኦሮሞው የወረሰውና ያወረሰው አለ፡፡ ኦሮሞው ለአማራው ያቀበለውናና የተቀበለው አለ፡፡ የእኔ ብቻ ነው የሚባል ነገር በ21ኛው ክፍለ ዘመን አይሠራም፡፡
መቼውንም ቀናው ነገር የማይታየው ሰው ‹‹ይህች አገር የኦሮሞና የአማራ ብቻ ነች እንዴ?›› የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ እኔ ያነሳሁት ስለአንድ ሐሳብ ነው፡፡ ‹‹ተጫነብን››፣ ‹‹ሊጫንብን›› ስለሚባለው፡፡ ሰለዚህ ሐሳቡን ለሁሉም ይሆናል ብሎ ለመውሰድ ቅንነትን ይጠይቃል፡፡
ወደ ሐሳቤ ስመለስ ጥላቻ ካልሆነ በቀር ወይም ጥላቻችንን ቀለል ባለ ቃል ‹‹ተጫነብኝ››፣ ‹‹ሊጫንብኝ›› ነው በሚል ለመግለጽ ካልሆነ በቀር ውስጡ ሌላ ቁም ነገር (ሚስጥር) የለውም፡፡ በፈረንጅ አፍ እየተናገረ የአገሩን ቋንቋ ተጫነብኝ ቢል ጥላቻ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡ ወንድሜ! ‹‹የፈረንጁ›› ቋንቋ ተጭኖብህ ነው?
ሁላችንም እንግሊዝኛ ቋንቋን በትምህርት ቤት ስንማር ለምን ጥያቄ አልፈጠረብንም? ማለቴ ለምን ተጫነብን አላልንም? ከሌላው ዓለም ጋራ በቀላሉ ለመግባባት ይጠቅመናል በማለት አይደለ እንዴ?
ታዲያ ከአገር ልጅ ጋር ለመግባባት የሚጠቅምህን ቋንቋ ተጫነብኝና ሊጫንብኝ ነው የምትለው ፈሊጥ አይገባኝም፡፡
ግዴለም ወንድሜ በሌላ ቃላት አታሽሞንሙነው፣ እንዲህ የሚያደርግ ጥላቻ ነው፡፡ በእውነት ሐሳብህ ይህ ከሆነ በውስጥህ ጥላቻ አለ፣ በጥለቻ ምች ተመተሃል፡፡
ሰለዚህ አማርኛን መናገር መጥላት ተግባቦትን መጥላት ነው፡፡ አፋን ኦሮሞንም ለማወቅ አለመፈለግና አለመናገር ተግባቦትን መጥላት ነው፡፡ እንዲሁም ሌሎችን ቋንቋዎች፡፡
ዛሬ ላይ እንግሊዝኛ ቋንቋ የማን ቋንቋ ነው? የማን አገርና የማንስ ብሔር ቋንቋ ነው? ቋንቋና ባህልን ከአንድ ብሔር ጋር ብቻ መስፋትና ለፖለቲካ መጠቀም መጥበብ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡