(ቀዳሚው ክፍል)
በሪያድ አብዱል ወኪል
እንደ መግቢያ…
ማኅበራዊ ፍትሕን በኢትዮጵያ ለማስፈን ወጥኖ በንዋይ ወንድማማቾች (The Neway Brothers) መሪነት የተቀጣጠለውና በመነሻ ወሩ ስያሜ ‹‹የታኅሳስ ግርግር›› ተሰኝቶ የተዳፈነው የመገልበጥ መንግሥት ሙከራ ግማሽ ክፍለ ዘመንን ተሻግሯል፡፡ የሙከራውን መክሸፍ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ዛሬም ድረስ ያልጠፋ ሙግት ያለበት ቢሆንም፣ ‹‹ሥዩመ እግዚአብሔር ነኝ›› ይል ለነበረው ሥርዓት በሕዝቦች እኩልነት ላይ ለምትመሠረት ዘመናዊት ኢትዮጵያ ጥርጊያውን ያስመለከተ የማንቂያ ደውል እንደነበር አያከራክርም፡፡
የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ የከተቡት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ስለኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ የለውጥ ወጣኒ ሲጽፉ ‹‹ተራማጅ›› ያሉት ገርማሜ ንዋይ በሥርዓቱ ‹‹ፍርድ ቤት›› ቀርቦ የክርክር ማቆሚያ ንግግሩን ባደረገበት ወቅት፣ ይህንን ውጥን የሚያሳካ ሌላ ማዕበል ሐሳቡን ዕውን እንደሚያደርገው ተንብዮ ነበር፡፡ የገርማሜ ትንቢት ሰመረ፡፡
ኢትዮጵያ ብዙዎችን ያሳተፈና ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!››ን ፍካሬው ያደረገ አብዮት ተካሄደባት፡፡ ይህም ‹‹የለውጥ ተስፋ›› በርቶ ድርግም ሲል ብዙ አልቆየምና ከጄኔራል አማን ሚካኤል አምዶም መገደል ጋር ተስፋው አብሮ መሞት ጀመረ፡፡ አገራችንንም የየወገኑ ደም በየቦታው የሚፈስበት በ‹‹ነፃ ዕርምጃ›› ሳይቀር የኢትዮጵያውያን ሕይወት የተራከሰበት ወታደራዊ ሥርዓት ሲገርፍ፣ ሲያስርና ሲገድል ዓመታትን ኖረባት፡፡ የእኩልነት ጥያቄ በደርጉ በኩል አይመለስም ብለው ያመኑ ሌሎች ደግሞ ለሁለተኛ ዙር አብዮት ምርጫቸውን የትጥቅ ትግል ላይ አድርገው አገራችን ለተራዘመ ጦርነት ተዳርጋለች፡፡ ይህ የወገን ውጊያ (Civil War) በኢሕአዴግ ድል አድራጊነት ሲጠናቀቅም በነበር ቀረ እንጂ፣ ሌላ የነፃነትና የሕዝባዊ አስተዳደር (Democracy) ተስፋ አንሰራርቶ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ለውጦቹ ሁሉ ያመጡት መልካም ነገር አለ፡፡ የፈላጭ ቆራጭ ዘውዳዊው ሥርዓት መውደቅ፣ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ የሃይማኖቶችና የብሔሮች እኩልነት፣ የተሻለ የሐሳብና የንግግር ነፃነት ተጠቃሾች ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ከተነሱበት ዓላማ፣ ለሕዝብ ከገቡት ቃልና ከሕዝቡ ፍላጎት አኳያ ግን ሁሉም የከሸፉ ነበሩ፡፡
በዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ እምነት ኢሕአዴግ የተለየ ምሥጋና ይገባዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ይህንን መመስከር እንደሚያስፈርጅ ሳላውቅ ቀርቼ አይደለም፡፡ እውነት ስለሆነ እንጂ ነው፡፡ በኢትዮጵያችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የብሔሮችና የሃይማኖቶች ነፃነት ከእኩልነት ጋር የተከበረበት፣ የሐሳብና የንግግር ነፃነት ከመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓትና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ጋር ዕውን ሊያደርግ ጀምሮ ነበር፡፡ ወደ ነጥባችን ስንመለስ እነዚያ ተስፋዎችም እንደ ቀዳሚዎቹ ሁሉ አልዘለቁም፡፡ እስርን፣ ማዋከብና ግድያን ደርበው ተመለሱና – ከሸፉ!
እያደር ከተሜነት የወለደው ንቅዘት ሥር ሰደደ፣ በአንድነት ጥላ ሥር ለእኩልነት የታሰበው የብሔሮችና ሃይማኖቶች ነፃነት ለፖለቲካዊ ሥልጣን ማቆያነት ውሎ ለመጣፊያነት ይመነዘር ያዘ፣ የመድበለ ፓርቲውን ሥርዓት በአውራነት (Dominancy) ሥልጣን ላይ የመክረም ፍላጎት አጨናገፈው፡፡ የሐሳብና የንግግር ነፃነትም የወረቀት ላይ ነብር ሆኖ የዜጎች አንደበትና የብዙኃን መገናኛዎች ተሸበቡ፡፡ በአጠቃላይ ስለ ‹‹ሕዝባዊ አስተዳደር›› የነበረን ምልከታ ላይ ቋንቋችን ተለያይቶ ከወታደራዊ ወደ ከፊል ሲቪል የአምባገነን ሥርዓት ተሸጋገርን፡፡ ከዚያስ?!
ምልሰት – ወደ ነበርንበት?!
የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ወትሮም በቋፍ የነበረው ፖለቲካችን አይሆኑ ሆኗል፡፡ የታዋቂዎቻችንን ግድያ በተመለከተ ከመታመን ማማ የወረደውና በምርመራዎቹ ውጤት ረገድ ሕዝብን ማሳመን ያልቻለው፣ መንግሥታችንም ቢሆን ተዓማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷልና ግድያው በገለልተኛ አካል እንዲጣራ መንግሥት ይሁንታውን ሊሰጥ ይገባል፡፡ የወንጀሉ ፈጻሚ ማንም ይሁን ማን ጡረታ ልናስወጣው የተለምንለት ‹‹የሴራ ፖለቲካ›› ተቀፅላ ሆኖ ከፖሊስ፣ ከዓቃቤ ሕግና ከፍርድ ቤት ቀድሞ በባለሥልጣናት የተሰጠውን ድምዳሜም ሆነ ከወንጀሉ የቀጠለውን የአገር ንብረትና የግለሰቦችን ጥሪት የማውደምን ሌላ ወንጀል አለማውገዝ አይቻልም፡፡ ሕግና ሥርዓትን በማስከበርና የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ መካከል ያለውን ልዩነት ያለመረዳት የባለሥልጣናቱ ችግርም እዚሁ ተደማሪ ነው፡፡
የኢትዮጵያችን አገረ መንግሥት ግንባታ ችግር እንደ ነበረበት መቀበል የማይፈልጉ ብዙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የእነዚህ ተቃራኒዎችም በርክተዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነጥብ አንስቼ ልለፍ፡፡ በደርግ ሥርዓት ጅማሮው ብልጭ ቢልም ከኢሕአዴግ ሥልጣን በኋላ በተበየነችው (Restructured) ኢትዮጵያ ላይ ቅሬታቸውን አፍነው የቆዩ፣ ይልቁንም ሚዲያውና ኪነቱ አካባቢ የነበሩ በርካቶች እንደ አዲስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ቢታወቅም በራሱ ችግርነቱ አይታየኝም፡፡
ኢትዮጵያችን ዳግም እንድትበየን የቀደሙት ሥርዓቶች ያነበሯቸው ገፊ ምክንያቶችና ተጨባጭ ሥጋቶችም እንደነበሩ አለማስታወሱ ነው ችግር የሚሆነው፡፡ ብየናው ገና ያላለቀና ማለቅ የሚኖርበት መሆኑን አለመቀበላችን ነው ችግር የሚሆነው፡፡ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንና ከጽሕፈት ቤታቸው ሹማምንት ጀምሮ በተማከለ አስተዳደር ፈላጊዎቹ ባይመሠገንም በነቢብ ያልተማከለ አስተዳደርን መስሎ በገቢር ቀዳሚውን ባስቀጠለው የኢሕአዴግ ሥርዓት ውስጥ በባለሥልጣንነትም ይሁን በአባልነት ቀርቶ በደጋፊነት የተሠለፈው ወገን እንኳን፣ ኢሕአዴግ ለሠራቸው ጥሩ ሥራዎች እንደሚሞገስ ለጥፋቶቹም እንደሚወቀስ እየረሱ ‹‹የጲላጦስን ሚና›› እንውሰድ ማለታቸውና እሱኑ ሲረግሙ መኖርም ሌላው ችግር ነው፡፡ ብዙዎቻችንን በብዙ ካስከፉት ጠቅላይ ሚኒስትራችን መልስ የሚሰጠንን ሐሳብ እንቆንጥር፡፡ ‹‹በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መሠረታዊ መርሆዎችና መብቶች የሚከበሩ ሳይሆኑ የሚደፈጠጡና የሚኮስሱበት፣ መድብለ ፓርቲን የፈቀደ ሕገ መንግሥት እያለ የአውራ ፓርቲ ሕገ መንግሥትን በመገንባት ማንኛውንም መንግሥታዊ ተቋም የአውራ ፓርቲ አጀንዳ ብቻ የሚያስተጋባበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፤›› ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትራችን፡፡
ፖለቲካዊው ተሳልቆ የሚመጣውም እዚህ ነጥብ ላይ ነው፡፡ እንኳንስ ‹‹መደመር›› በተሰኘው ግላዊ መጽሐፍ ኅትመት፣ ትውውቅና ሽያጭ የተገለጠው የላይኛው ሠፈር ቀርቶ በዝቅተኛው እርከን ‹‹የሸገር ዳቦ›› አከፋፋይ ለመሆን የኢሕአዴግ (ብልፅግና) አባል መሆንን አስገዳጅ መሥፈርት ያደረገ መዋቅር ስለመኖሩ አልሰሙ ይሆን?! በአገረ ኢትዮጵያ ‹‹አገዛዝ›› እንጂ ‹‹አመራር›› እንደሌለ ደጋግመው የሚሞግቱት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ሥልጣንና መሪነትን በተመለከተ ቆየት ባለውና “ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?” በተሰኘ ሥራቸው ገዥዎች ሥልጣንን የሙጥኝ የማለታቸውን ምክንያት ጠቃቅሰው ይህንን ከትበው ተመለከትኩ፡፡ ‹‹መሪ…. በሥራው መመሥገን፣ መወቀስና መነቀፍ ይችላል፡፡ እንዲያውም ከነቀፌታም አልፎ ሕዝቡ ሊሽረው ይችላል… መሪን ለመሪነት የሚስለው፣ የሚያበስለውና የሚያሠለጥነው ተቃውሞ ነው፡፡ ዓላማውን ሲስትና ሲታበይ፣ በሥልጣን ሲሰክርና የገባውን ቃል ሲረሳ፣ ከአስተዳዳሪነት ወደ ገዥነት የመለወጥ ምልክቶችን ሲያሳይ ተቃውሞ ካልገጠመው ጭልጥ ብሎ አድራጊ ፈጣሪ እኔ ነኝ ወደ ማለቱ ይደርሳል… ተቃውሞንና ነቀፌታን ለማዳመጥና ከዚያም ራሱን ለማሻሻል የማይችል ሰው ደግሞ ለመሪነት አይበቃም፡፡›› ዘጠናን የተሻገሩት አንጋፋ ፕሮፌሰር ይህንን መመዘኛ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስተዳደር ‹‹ይጠቀሙበት ይሆን ወይ?›› የሚለው ነገር ቢያጠራጥረኝም፣ በኢትዮጵያችንና በኢሕአዴግ ውስጥ ‹‹ለውጥ›› መጥቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ የሥራ ኃላፊነት ከመጡበትና ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በወራት ጊዜ ውስጥ ይህንን የታሪክ ፈተና መውደቅ ስለመጀመራቸው ተስተውሏል፡፡ ከዓመት በፊት በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ስንደግፍ የሚቃወሙና የሚተቿቸውን ሰዎች ሐሳብ የመግለጽ መሠረታዊ መብት እንዳንቃወም ሥጋቴን ገልጬ የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሌላው ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ በ‹‹ሂሳዊ ድጋፍ›› ስም የሚነሱ ወገኖችም አስተዳደሩን የሚተች ምንም ዓይነት ተቃውሞና የተለየ ሐሳብን ለመስማት ያለ መፍቀድ ውስጥ ገብተው ታዝበናል፡፡ ሥልጣን ለያዘው ሁሉ ሲያሸረግዱ ለዘመናት የኖሩት ‹‹የመንግሥት›› የሚባሉቱና የገዥው ሚዲያዎችማ ከቀድሞው ብሰዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ተመሳሳዩን ሐሳብ ‹‹ሥልጣን፣ ባህልና አገዛዝ ፖለቲካና ምርጫ›› ባሉት መጽሐፋቸውም በሰፊው አንስተውታል፡፡ ከያዝነው ርዕሰ ጉዳይ አኳያ ግን ለሕዝባዊው አምባገነንነትን ማዋለድና በሥልጣን መባለግን በባለሥልጣኑ ዙሪያ በሚገኙና ‹‹በሰፊው ሕዝብ›› ገፋፊነትም ሊከሰት እንደሚችል ሲገልጹ፣ ‹‹የሥልጣን ብልግናን በአንድ መልኩ ብቻ -ማለትም በባለጉት ባለሥልጣናት የሚፈጸመውን ብቻ ማየት የለብንም፡፡ የሚያባልጋቸውስ ማን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን… ሕዝቡ የሚያባልግ ካልሆነ ባለሥልጣናት አይባልጉም፣ ለመባልግም ዕድሉን አያገኙም፣ ባለሥልጣን ሲባልግ የተባበረ፣ ያየና ዝም ያለ ሁሉ፣ ሌላው ሲጠቃ፣ ሲበደል፣ መብቱ ሲገፈፍ እየተመለከተ ዝም ያለ ሁሉ በተለያየ ደረጃም ቢሆን ለሥልጣን ብልግና አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የሥልጣን ብልግና ባለበት ሁሉ ሕዝቡ ለዚያ ብልግና የራሱ ድርሻ የሚሆን ኃላፊነት አለበት፡፡ የሥልጣን ብልግና ሊጠፋ የሚችለው ሕዝቡ ለዚህ ጉዳይ ያለበትን ኃላፊነት ሲቀበልና ሲወጣው ነው፡፡››
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይህንኑ የፕሮፌሰሩን መሟገቻ ሲያጠናክሩት፣ ‹‹መሪዎች ከሕዝብ የሚነሳን ወይም ከተመሪዎቻቸው የሚሰነዘርን ተቃውሞና ሐሳብ እንደ አስፈላጊነቱ የሚቀበሉ ካልሆኑ ራሳቸው ሞገደኛ ይሆናሉ ማለት ነው። ይህም መሪነት የሚያስፈልገውን የጋራ ህልም ትቶ የራሱን የመሪውን ህልም ብቻ ይዞ ስለሚጓዝ መሪውን ከመሪነት ወደ ገዥነት ይቀይረዋል፤›› ይላሉ፡፡ እነሆ ሌላው – ተሳልቆ!
አንዳንዶች እንደ ‹‹ዘለፋ›› ቢቆጥሩትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “Walk your talk!” ሲባሉና አስተዳደራቸው የሕዝብን ጥያቄዎች እንዲመልስ ሲጠየቅ፣ የሕዝቡን ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ‹‹ትንንሽ ሐሳቦች›› ብለው በማቃለል በራሳቸው አገላለጽ ‹‹ሞገደኛ›› ሆነዋል፡፡ የራሳቸውን ህልም በመያዝ ወደ ገዥነት ሲንደረደሩ በብዙ ተስፋ አድርገንን ለነበርነው ከዘመኑ ጋር ሲታገል እንደኖረው አቤ ጉበኛ፣ ‹‹ለውጡ የትኛው ነው?›› እያልን በማጠየቅ እንድንቆይ፣ አልያም ብላቴናው ‹‹አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?›› ብሎ እንዳዜመው እንድናዜም የተፈረደብን ይመስላል፡፡
አንዳንድ ጥያቄዎች አሉ…..
ዛሬስ ከአስተዳደር ጅማሮው ወጥቶ ወደ አገዛዝ በገባው የጠቅላይ ሚኒስትራችን መንግሥት ሥር፣ በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር የተጠየቀውና የተጠበቀው ‹‹ለውጥ›› እየመጣ ይሆን?! ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የፖለቲካዊው ፍትሕ›› ዱላ ያረፈባቸው አቶ በረከት ስምዖን በግላጭ ይሉት እንደነበረው የአርባ ዓመታት ‹‹ውጥን›› እንዳላቸው ይፋ አላደረጉም?! ‹‹አሻግራችኋለሁ!›› ተረስቶ ለረዥም ጊዜ የአምባገነንነት ፍላጎት ተመቻችተው አላመቻቹንም?! ሕግጋት የቂም በቀል መወጫ አልሆኑም?! የተቋማት ግንባታ ጥንስስና ተዓማኒነታቸውስ ከወዴት ነው?!
ዛሬ እነሱ ለሚመርቋቸው አገራዊ ፕሮጀክቶች መሠረቱን ያስቀመጠውን የኢሕአዴግን ፖለቲካ በጨለማ ዘመን መመሰላቸው ለእኔ ስህተት ነበር፡፡ ‹‹ከአፍ ሲያመልጥ….›› ሆኖባቸው ‹‹ተፎካካሪ›› ተሰኝተው የሸነገሏቸውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራትን በአደባባይ ሲያብጠለጥሉስ አልተደመጡም?! በእሳቸው አመራር ሥር የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት መዋለድን ጨምሮ ብዙ ተስፋ አጨላሚ ነገሮች አልተስተዋሉም?! ልንሻገረው ነው ያልነው የደምና የመስዋዕትነት ፖለቲካ በአስፈሪ ገጽታውና ‹‹በወታደራዊ ዩኒፎርሙ›› አልተመለሰም?!
ፖለቲካዊውን ተሳልቆ ልድገመው፡፡ ዛሬስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ለሚዲያ ፖለቲካ ፍጆታ ከሚከወኑ የይስሙላ ንግግሮች (Dialogue of the Deaf) የተሻሉና ብዙዎች ፖለቲከኞቻችን የሚነጋገሩበትን የመደማመጥ መድረኮች (National Dialogues) አዘጋጅተው ከቀደመው ችግራችን አዳኑን ወይስ አዲስ ችግር አመጡብን? ተስፋ ያደረግነው ምልክቶቹን ማከም ላይ ሳይሆን ህመሙን ማዳን ላይ እንዲሠራ አልነበርም?! የዳያስፖራውን ፖለቲካ ከብሽሽቅ ለማውጣት አልነበረም?! ዛሬስ ‹‹ባለፉት 27 ዓመታት›› እያልን ያለፈውን ሥርዓት ከመውቀስ (The Blame Game) ተላቀናል?! የእኔ መንገድ ካልሆነ መንገድ የለምን (My Way or No Way) ኢሕአዴጋዊ ትምክህት በቃልም በተግባርም አልተወረሰም?!
ፖለቲካዊውን ተሳልቆ ልሰልሰው፡፡ ‹‹ተፎካካሪ›› ተብለው የተሸነገሉት የተቃውሞ ፖለቲካ ማኅበራት በዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተማከሩና እየተሳተፉ ነው ወይስ ቃሉ ተረስቷል?! የጠላትነት፣ የግብፅና ‹‹የእንቶኔ›› ተላላኪነት ፍረጃ እንደ አዲስ ተጀምሯል፡፡ ከእኛ በሐሳብ የተለዩ በሙሉ የግብፅ ተላላኪና አገርን የማፈራረስ አጀንዳ አራማጆች አድርገናል፡፡ በቃል ደረጃ እንኳ ከ‹‹ትግል›› ያልተላቀቀው ፖለቲካችን ከተዋረዳዊው መተጋገል በተጨማሪ የጎንዮሽ ፍንጣሪንስ አልጨመረም?! በሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ጭንብላችንን የገለጸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ‹‹ድርሰት›› ብለነው የለም?! የታወቁ ዜጎቻችንን ተከታታይ ግድያ ‹‹ድራማ›› አልሰኘነውም?! የሲቪል ፖለቲካስ በአላዋቂነት አልተፈረጀም እንዴ?!
አንድ ስሙን የዘነጋሁት ኢትዮጵያዊ ጠቢብ ‹‹አንዳንድ ጥያቄዎች አሉ በተደጋጋሚ ተጠይቀው እየተመለሱ እንደገና ተደጋግመው የሚጠየቁ!›› እንዲል ወደ ሥልጡንና የሰከነ ሰላማዊ ፖለቲካ እንዳንሻገር ምክንያት ሆኗል ብዬ አምናለሁና ነው ይህንን ሁሉ መጠየቄ፡፡ ኢትዮጵያ በየወቅቱ ተስፋን ታረግዛለች፡፡ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ‹‹ታሪክ ምንድነው?›› ብለው ከመጠየቃቸው በፊት ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› በተሰኙት መጽሐፍ ቀዳሚ ምዕራፍ ሥር እንደጠቀሱት ‹‹መክሸፍ›› ተጣብቶናልና የኢትዮጵያችን የለውጥ ተስፋ አንድም አይወለድም፣ ሁለትም ተወልዶ ብዙ አይቆይም፡፡
ከላይ የጠቀስነው የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ቀዳሚዎቹ ምዕራፎች ሥር የተካተቱና የተጨመቁ ሐሳቦች በራሳቸው ዘርዘር ቢደረጉ ለበርካታ መጻሕፍትና ጥናቶች ግብዓትም መነሻም ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያችን ታሪክ ውስጥ ተከስተዋል ያሏቸውን ዓይነተ ብዙ መከሻሸፎችን አውስተውና የክሽፈቱ ምክንያት ‹‹ተመርምሮ ካልተጠና›› እየከሸፍን የመቀጠላችንን አይቀሬነትም ጠቅሰው ከፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ አንድ ‹‹የሙከራ ሥራ›› ውጪ የተሠራ ጥናት አለመኖሩንም ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹የአገራችን የለውጥ ዕድሎች ለምን ይከሽፋሉ?›› የሚለውን ርዕስ አንስቶ በድፍረት መወያየቱ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ ነን፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ስሜት አልባ ለሆነ ሰው ‹‹ቁም!›› ሲሉ መጽሐፉን ይልቁንም የመቅድሙን ንባብ እንዳያነብ ነፍገው የ‹‹መክሸፍ››ን ምንነት ሲተነትኑ ‹‹መክሸፍ የምለው አንድ የተጀመረ ነገር ሳይጠናቀቅ ወይም ሳይሳካ እንቅፋት ገጥሞት መቀጠል ሳይችል፣ ዓላማው ሲደናቀፍና በፊት ከነበረበት ምንም ያህል ወደፊት ሳይራመድ መቅረቱን ነው፡፡ የዕድገት፣ የመሻሻል፣ የመለወጥ ጉዞ መቋረጥን የሚያመለክት ነው፤›› ይሉታል፡፡
ከውጭ በመንግሥት ተቃዋሚዎች ከውስጥ የለማ ቡድን (Team Lamma) እየተባለ በሚጠራው ስብስብና ብዙ ጊዜ እንዲገለጽ በማይፈለገው በራሱ በኢሕአዴግ ውስጣዊ ትግል የተዋለደው የኢትዮጵያ ‹‹ለውጥ››፣ ከትልሙ ተንሸራትቶ ለግለሰቦች የሥልጣን ጥማት ይልቁንም ‹‹ሰባተኛው ንጉሥነታቸውን›› የምር አድርገው እየወሰዱ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የረዥም ጊዜ አምባገነናዊ ፍላጎት መስከንተሪያነት ሲባል ‹‹ከሽፏል!›› እላለሁ፡፡
‹‹አልወለድም!›› ባዩን አብዮተኛ አቤ ጉበኛ ‹‹አልደመርም!›› ስል ልጥቀሰው፡፡ ብዙ መዘዝ በመዘዘበትና ትንቢቶቹን በገለጸበት በዚህ መጽሐፉ በኩል፣ ‹‹ባለፈው ጊዜ የገቡት ቃል ሁሉ ሌላ ነበር፡፡ የሕዝቡን ጥቅም፣ የሕዝቡን መብትና ነፃነት እናከብራለን…. ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን ተስፋው ሁሉ ተዘንግቶ በህልም እንኳ ያልታሰበ ነገር ሆነ፡፡ ‹ከፊተኛው የኋለኛው ይከፋል!› የተባለው ነገርም ተፈጸመ፤›› ማለቱ ለዚህ ይመስላል፡፡
የሥልጣን ጥያቄን የሚያነውር ሥርዓት?!
ተወደደም ተጠላ ፖለቲካ አንድም የሥልጣን ሁለትም የነፃነት ጥያቄ ስለሆነ ነው “Politics…. above all is a dualistic conflict between Rival groups, a group in power and a group of Opposition forces which would seek replace it.” መባሉ፡፡ እዚህ ጋ አንድ ማሳያ ማንሳቱ አይከፋም፡፡ የኢሕአዴግ የረዥም ጊዜ መሪ ሆነው የዘለቁት አቶ መለስ ዜናዊ፣ የድርጅታቸው ጓዶች አዲስ አበባን ከያዙ በኋላ ዘግየት ብለው ነበር የገቡት፡፡ በጄኔራል ኃይሌ ጥላሁን የተዘጋጀውን ረቂቅ ‹‹ላውንቸር›› ተብሎ በተቀፀለለት ታጋይ በኩል በግንቦት ሃያ ማለዳ ‹‹የዘመናት የሕዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢሕአዴግ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬዲዮ ጣቢያ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል….›› የምትለው የወቅቱ ድል አድራጊነት ንባብ ተሰምታም ቢሆን የቤተ መንግሥቱ ቅፅር ውስጥ የገባ ታጋይ አልነበረም፡፡ አቶ መለስ ይህንን ሲያስተውሉና ታጋዮችን ለምን ቤተ መንግሥቱ ውስጥ እንዳልገቡ ሲጠይቋቸው፣ ‹‹የታገሉት ለሥልጣን ብለው ነው እንዳንባል ፈርተን….›› የሚል አላዋቂ መልስ ይሰጧቸዋል፡፡ በመልሱ የተገረሙት አቶ መለስም ዘመን አይሽሬ ንግግራቸውን፣ ‹‹ታዲያ ለምንድነው የታገልነው?!›› ሲሉ በጥያቄ መልክ አቅርበው እንደነበርም አንብቤያለሁ፡፡ ከዚህ በፊት በጠቀስነውና በአቶ ልደቱ አያሌው ከተጻፈው ‹‹መድሎት፣ በኢትዮጵያ አከራካሪ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሦስተኛ አማራጭነት ሚና›› በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ስለፖለቲካ ባህላችን ከተጠቀሰው እንስበዝ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለገዥው ፓርቲ ሥልጣን ላይ መቆየት ለተቃዋሚዎቹ ደግሞ ሥልጣን ላይ መውጣት ‹‹ዋናው ቁምነገር›› ነውና በአዲስ አበባ ላይ በምርጫ 97 ወቅት ተከስቶ የነበረውን ‹‹የጥምር መንግሥት›› መሆን አጋጣሚ ማሳያ በማድረግ ተግባብቶ የመሥራቱ ነገር እንደማይኖርና ለወደፊትም ይህንን የሚያስችል ብሎም ‹‹ብሔራዊ መግባባት›› ሊፈጠርባቸው የሚገባቸው የታሪክ፣ የፖለቲካና የሕግ፣ እንዲሁም የተቋማትና አገራዊ መለያ ጉዳዮችን አንስተው አቶ ልደቱ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ፣ ‹‹ሲቻል ተከራክሮ መተማመን፣ ሳይቻል ደግሞ በልዩነት ተከባብሮ መኖር ሲቻል ከእኛ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ኃይሎች በደፈናው እያንኳሰስንና እያራከስን ለማየት መሞከር፣ በአገራችን እንዲፈጠር ለምንፈልገው ‹‹ብሔራዊ መግባባት›› የሚያግዘን አይሆንም፤›› ማለታቸውንና ለዚህ የሚያግዝ የብሔራዊ መግባባትና የዕርቅ መድረክ እንዲመቻች ሲጎተጉቱ መቆየታቸውን ማስታወሱም አይከፋም፡፡ በሥልጣን ስስቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ኢሕአዴግ (ብልፅግና) ተቃዋሚዎችን በሥልጣን ፍላጎት የሚተቸው የፖለቲካ ጥያቄ የሥልጣን ጥያቄ መሆኑ ጠፍቶት አይደለም፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የፖለቲካ ጥያቄን በተሳሳተ መንገድ የሚረዳና የሥልጣን ጥያቄን የሚያነውር ሥርዓት ስለገነባን እንጂ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከትናንት እስከ ዛሬ በሚዲያ ከሚቀርቡ የፖሊስ መኮንኖች አንደበትና መግለጫዎች ተቃውሞን ኃጢያት አስመስለው ‹‹ድብቅ ዓላማ ያላቸውና የሥልጣን ጥማታቸውን ለማርካት የሚፈልጉ ኃይሎች….›› የሚሏት አገላለጽ፣ ከሕዝብ ተቃውሞዎች ኋላ እንድትመሽግ የሚደረገው ብዬም አምናለሁ፡፡ በቀጣዩ ክፍል እስከምመለስ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በግንቦት ወር መጀመርያ ላይ ባወጣው መግለጫ ይህንኑ በተመለከተ ባስቀመጠው ሐሳብ እንሰነባበት፡፡ ‹‹ለሥልጣን መሮጥ ምንም ስህተት የለውም፣ ነገር ግን አገርና ሕዝብ ከዚህ ሩጫ ያተርፉ ዘንድ ሥልጣን ለምን? ለማን? ምን ለማድረግ?!….. የሚሉ ጥያቄዎችን በሚገባ መመለስ ያስፈልጋል ብሎ ኢሕአፓ ያምናል፤›› ይላል ኢሕአፓ፡፡ ደርግ ወታደራዊ ሥርዓትን ሲገነባ ኢሕአዴግ ‹‹ዩኒፎርሙን›› ደብቆን ቆይቷል፡፡ የአሁኑስ ሲቪል ነው ወይስ ወታደር?! (ተከታዩ ክፍል ሳምንት ይቀጥላል)
-ሰላም ለእናንተ ይሁን!-
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡