Tuesday, April 16, 2024

በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያሉት የልዩነት ነጥቦች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ላይ ሁለቱ የታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ሥጋት ያዘለ ጥያቄ በማንሳታቸውና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጥቅም ላይ የሚውሉበትን አግባብ የሚገዛ ዓለም አቀፍ ሕግና አሠራር በመኖሩ፣ ኢትዮጵያም ይህንኑ መርህ በመከተል የታችኞቹ አገሮች ሥጋትን ለመቅረፍ መመካከርን መርጣለች።

በዚሁ መሠረትም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ከሚባሉት ግብፅና ሱዳን ጋር ስትደራደር የቆየች ሲሆንአሁንም ያለመታከት እየተደራደረች ትገኛለች።

በአዲስ አበባ፣ በካይሮና በካርቱም እየተዘዋወረ ለዘጠኝ ዓመታት የተደረገው ድርድር2012 ዓ.ም. ደግሞ ወደ ዋሽንግተን ከዚያም ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እያለ ሲዘዋወር ቆይቶ በስተመጨረሻም በአፍሪካ ኅብረት ሥር መፍትሔውን ለማግኘት እየሞከረ ይገኛል።

ላለፋት ዓመታት ሲደረግ በቆየው ድርድር የተስተዋሉት የልዩነት ነጥቦች ባህሪያቸውን የሚለዋውጡከአንድ ጉዳይ ወደ ሌላ የሚዘሉ የነበሩ ቢሆንም ቀላል ያልነበሩ የልዩነት ነጥቦችም መፍትሔ ማግኘታቸው ደግሞ አልቀረም።

ከእነዚህም መካከል አንዱና በዋናነት የሚጠቀሰው የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ከግብፅ የአስዋን ግድብ የውኃ ይዞታ ጋር ተናቦ መከናወን አለበት የሚለው የግብፅ መንግሥት አቋም ይገኝበታል።

ግብፅ ባራመደችው በዚህ አቋም የአስዋን ግድብ የውኃ ይዞታ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ኢትዮጵያ ግድቧን መሙላት የለባትም የሚልና 165 ሜትር በታች ከሆነ ደግሞ በግድቡ ከያዘችው ውኃ መልቀቅ ይኖርባታል የሚል ነበር።

ኢትዮጵያ ይህንን ጥያቄ ከጥንስሱ አንስቶ የተቃወመችው ሲሆንየአስዋን ግድብ የውኃ ይዞታ በምን ምክንያት ወደ 165 ሜትርና ከዚያ በታች ዝቅ እንዳለ ኢትዮጵያ ማወቅ በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ልትስማማበት ይቅርና ልትወያይበት እንኳን እንደሚከብዳት አቋሟን ግልጽ አድርጋለች።

ግብፅ የአስዋን ግድብ የውኃ ይዞታን ከህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላል ጋር ለማገናኘት የፈለገችውአስዋን ግድብን በማስተዳደርና በመቆጣጠር ያላትን ሉዓላዊ መብት ተጠቅማ በግድቡ የተጠራቀመውን የውኃ መጠን ለሁልጊዜ 165 ሜትር ገደማ ላይ እንዲቆይ በማድረግ የህዳሴ ግድቡ ሙሌት ህልም እንዲሆን በግብፅ የተሸረበ ሴራ ሊሆን እንደሚችል በማመን በአቋሟ ፀንታ ጥያቄውን ሳትቀበል ዓመታትን አሳልፋለች።

በዚህ ምክንያታዊ አቋሟ የተነሳም ግብፅ ይህንን የመደራደሪያ ነጥብ ለማንሳት በመገደዷ የተገኘ አንድ መፍትሔ ሆኖ ተመዝግቧል። ከዚህ በተጨማሪ በህዳሴ ግድቡ የሙሌት ሒደት ኢትዮጵያ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንድትለቅ ያቀረበችው የመደራደሪያ ነጥብም፣ በኢትዮጵያና በሱዳን አማራጭ የመደራደሪያ ነጥብ ውስጥ እንዲወድቅ ሆኗል።

በሌላ በኩል የህዳሴ ግድቡ የመጀመርያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትን የተመለከተው የድርድር ነጥብም ኢትዮጵያ ባቀረበችው አማራጭ የተቋጨ ሆኗል። በዚህም መሠረት የመጀመርያው ምዕራፍ የውኃ ሙሌት በሁለት ዓመት የክረምት ወቅቶች እንዲከናወንና በድምሩም 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በግድቡ እንዲያዝ ሦስቱ አገሮች ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ምንም እንኳ በዚህ የሙሌት ምዕራፍ ላይ ስምምነት ቢደርሱም የሙሌት ጅማሮው አጠቃላይ ስምምነት ሳይደረስ መጀመር እንደሌለበት ግብፅና ሱዳን ግፊት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንምበዘንድሮው ክረምት ወደ ግድቡ የመጣው የውኃ መጠን በግድቡ ዲዛይንና የግንባታ ደረጃ ምክንያት በመጀመርያው ምዕራፍ የውኃ ሙሌት የመጀመርያ ዓመት እንደሚያዝ ስምምነት የተደረሰበት 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. ተከናውኖ ተጠናቋል።

ያልተፈቱት የልዩነት ነጥቦች ምንድን ናቸው?

ሦስቱ አገሮች ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ባደረጓቸው በርካታ ድርድሮች ከላይ በተገለጹት የልዩነት ነጥቦች ላይ ስምምነት ቢደረሱምጥቂት የሚባሉ ነገር ግን በፖለቲካዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የጋራ ሀብትን በፍትሐዊነትና ዕኩልነት መጠቀም ጋር የተቆራኙ ወሳኝ የሆኑ የልዩነት ነጥቦች ላይ በርካታ ውይይቶችን ቢያደርጉም ከስምምነት መድረስ አልቻሉም።

እነዚህ የልዩነት ነጥቦች በሁለት የሚከፈሉ ሲሆኑ፣ የግድቡን የውኃ ሙሌትና አስተዳደር የተመለከቱ ቴክኒካዊ ጉዳዮችና የስምምነቱ አፈጻጸምን በተመለከቱ የሕግ ጉዳዮች የተከፈሉ ናቸው።

የቴክኒክ ጉዳዮችን የተመለከቱት የልዩነት ነጥቦችም በተራዘመ ድርቅ ወቅት የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አስተዳደር ምን መሆን አለበት፣ በየቀኑ የሚለቀቀው የውኃ መጠን ልዩነት ስሌትና የኦፕሬሽን ሁኔታዎች ናቸው። 

የሕግ ጉዳዮችን የተመለከቱት የልዩነት ነጥቦች ደግሞ የኢትዮጵያ ወደፊት የዓባይ ውኃ አጠቃቀም እንዴት ይወሰናል፣ የልዩነት ወይም አለመግባባት የሚፈታበት መንገድ ምን መሆን አለበትና የግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን የተመለከቱ የቴክኒክ ሕግና ደንቦችን መከለስ የሚቻልበት የሕግ አግባብ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ ሥነ ሥርዓትን የተመለከቱ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ የውኃ መስና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

የቴክኒክ ጉዳዮችን ከተመለከቱት የልዩነት ነጥቦች መካከል አጨቃጫቂ የሆነው በተራዘመ ድርቅ የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ምን መሆን አለበት የሚለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በተራዘመ ድርቅ ወቅት የሚኖረው የውኃ አስተዳደር የሦስቱም አገሮች ኃላፊነት መሆን አለበት የሚል አቋም ይዛለች። 

ግብፅ በበኩሏ የተራዘመ ድርቅ ለሚለው ሦስት ትርጓሜዎችን የሰጠች ሲሆን፣ እነዚህም ድርቅ፣ የተራዘመ ድርቅና የተራዘመ ደረቃማ ወቅት የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችም ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን ከ40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በታች ሲሆን ተከስተዋል የሚል ትርጓሜ እንዲሰጥ ትሟገታለች።

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ በግድቡ ከያዘችው የውኃ መጠን መልቀቅ አለባት የሚል ክርክር ታነሳለች። ይህ የልዩነት ነጥብ የኢትዮጵያ የወደፊት በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት እንዴት ይወሰናል ከሚለው ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የተራዘመ ድርቅ ሆነ የተራዘመ ደረቅ ወይም በአጠቃላይ የድርቅ ወቅት የሚለው ጉዳይ የሚወሰነው በተፈጥሯዊ የድርቅ አመላካች የአየር ንብረት ሁኔታዎች ሳይሆን፣ ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን ላይ የሚመሠረት በመሆኑ ነው። 

በሌላ አነጋገር ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን (ማለትም 31 እና 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ) ከሆነ የድርቅ አመላካች ሲሆኑ፣ ይኸው መጠን ለተከታታይ ዓመት ከቀጠለ ደግሞ የተራዘመ ድርቅን አመላካች ይሆናል። 

ነገር ግን ወደ ግድቡ የሚመጣ የውኃ መጠን የድርቅ ወቅት አመላካች ይሆናል ወደ ተባለው የውኃ መጠን ዝቅ ያለው በምን ምክንያት ነው የሚለው ነጥብ ደግሞ ከወደፊት የኢትዮጵያ የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ጋር በቀጥታ ይገናኛል። 

ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ተፈጥሯዊ በሆነ የዝናብ እጥረት ምክንያት ነው ወይስ ከግድቡ በላይ በሚገኘው የዓባይ ተፋሰስ ላይ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ልማቶችን በማካሄዷ፣ በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ላይ ሦስቱ አገሮች መግባባት ያልቻሉበት ግዙፍ የልዩነት ነጥብ እንደሆነም መረጃው ያመለክታል። የወደፊት የውኃ አጠቃቀም ጉዳይ የሚከሰተውም እዚህ ጋር ነው። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን የድርቅ ወይም የድርቅ ወቅት አመላካች መጠን ወይም ከዚያ በታች የሆነው በተፈጥሯዊ የዝናብ እጥረት የተነሳ እንደሆነ ግዴታውን ለመቀበል እንደምትችል፣ ነገር ግን የተገለጸው ሁኔታ የተከሰተው ከግድቡ በላይ በሚገኘው የዓባይ ተፋሰስ ላይ ወደፊት በምታካሂደው ልማት ምክንያት ከሆነ ለግድቡ ሙሌት ተብለው በተቀመጡት አኃዞች እንደማትገደድ ገልጻለች። 

የዚህ ምክንያቱም በላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ላይ ወደፊት በምታካሂደው ተጨማሪ ልማት ምክንያት የግድቡ ሙሌትን የሚያደናቀፍ አልያም ኃይል የማመንጨት አቅሙ ላይ አሉታዊ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ነው። 

በተጨማሪም ግድቡ የውኃ ሙሌት ወይም ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳይቀንስ ሲባል፣ በላይኛው የዓባይ ውኃ ላይ ወደፊት ልማት እንዳታካሂድ የሚያስር ስለሚሆን ነው። 

ይህ ደግሞ በዓባይ ውኃ ላይ ለዘመናት የቆየውን የግብፅን በብቸኝነት የመጠቀም ኢፍትሐዊ አካሄድ የሚያስቀጥልና የአሁኑንም ሆነ የመጪውን የኢትዮጵያ ትውልድ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት የሚያሳጣ ነው የሚል አቋም በመያዝ በዚህ ጉዳይ ላይ ፈጽሞ ልትስማማ እንደማትችልና ዓለም አቀፍ ሕጎችንና መርህን በመከተል በታችኞቹ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መንገድ መብቷን ተግባራዊ እንደምታደርግ አስረግጣ አስታውቃለች። 

በመሆኑም ግብፅና ሱዳን ይህ ጥያቄ እንዲመለስ ከፈለጉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ አጠቃላይ የውኃ ክፍፍል ስምምነት መምጣት እንደሚገባቸው፣ ይህንን ለመወሰንም አሥሩ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ተደራድረው ወደተስማሙበትና እ.ኤ.አ. በ2010 በኡጋንዳ ወደ ተፈረመው ስምምነት መመለስ እንደሚገባ ኢትዮጵያ አቋም ይዛለች። 

ሌሎቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ይህንን ስምምነት በወቅቱ ተቀብለው ሲፈርሙ ግብፅና ሱዳን ግን ስምምነቱን ሳይቀበሉ ረግጠው መውጣታቸው ይታወሳል። ግብፅና ሱዳን ይህንን ስምምነት ላለመቀበል ምክንያት የሆናቸው አንድ አንቀጽ ሲሆን፣ ይህም የረዥም ጊዜ የውኃ ድርሻቸው የማይቀንስ ስለመሆኑ ዋስትና አይሰጥም በሚል ተቃውሞ ነው። 

አሁን እየተደረገ በሚገኘው ህዳሴ ግድቡን በተመለከተው ድርድር ላይ እየተሟገቱ የሚገኘውም ይህንኑ የረዥም ጊዜ የውኃ ድርሻ መጠን ለማስከበር በመሆኑ ልዩነቱ ሊጠብ አልቻለም። አገሮቹ ሰሞኑንም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የተጀመረውን ድርድር በመቀጠል ዕልባት ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል። 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -