ከጥቂት ወራት በፊት የፖሊሲ ማሻሻያ የተደረገበትና ሌሎችም ወቅታዊ አጋጣሚዎች ያገዙት የወርቅ የወጪ ንግድ፣ በመጠንና በገቢ እየጨመረ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ በዚህም በአንድ ወር ብቻ 72 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘ የወርቅ ምርት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መቅረቡ ታውቋል፡፡ በሌሎች ዘርፎችም ተመሳሳይ ማሻሻያ ለማድረግ ጥናት መጀመሩ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሎ የነበረው የወርቅ የወጪ ንግድ ከጥቂት ወራት ወዲህ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው መጠን እየጨመረ መምጣቱን ለዚህም የፖሊሲ ለውጡ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ይህ በመሆኑም በሐምሌ ወር ብቻ ከ72 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጣ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ሊቀርብ ችሏል፡፡ ባንኩ በሚከተለው የወርቅ ግዥ መመርያ ላይ ማሻሻያ ከተደረገ ወዲህ በወር በአማካይ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ወርቅ መቅረብ እንደጀመረ ተገልጿል፡፡
ወርኃዊ የወርቅ አቅርቦት ዕድገቱ እየጨመረ በመምጣቱ በሐምሌ 2012 ዓ.ም. 72 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ወርቅ ማስገኘቱ በዋጋም በመጠንም ጭማሪ ለማሳየቱ መገለጫ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በኋላም ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ አመላካች እንቅስቃሴ እየታየ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከወርቅ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በታች ብቻ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህን ያስታወሰው ባንኩ፣ በወርቅ መመርያ መሻሻል ሳቢያ የተገኘው ለውጥና ውጤት ከፍተኛ መሻሻል ያስገኘ በመሆኑ በሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ጥናት መካሄዱን ብሔራዊ ባንክ ይገልጻል፡፡
በዓመት እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ይገኝበት የነበረው የወርቅ ወጪ ንግድ፣ እንደ ሌሎች ምርቶች ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመምጣት ላይ ነበር፡፡ ባንኩ ባካሄዳቸው ጥናቶች መሠረት በጎረቤት አገሮች ውስጥ ኮንትሮባንዲስቶች በምን ያህል ዋጋ ገዝተው በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጡ ለመረዳት እንደቻለ ጠቅሶ፣ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚያዋስኑ ድንበሮች አካባቢም ሰፊ ጥናት በማካሄድና በሌሎች አገሮች ውስጥ ያለውን አሠራር ግምት ውስጥ በማስገባት ወርቅ የሚገዛባትን ዋጋ እንዳሻሻለ፣ የዚህ ውጤቱ አሁን እየታየ እንደመጣ ተብራርቷል፡፡
የዋጋ ማሻሻያ በማድረግ የግዥ ሥርዓት የሚፈጸምበት መመርያ ከወጣ በኋላ በየወሩ ከ30 ሚሊዮን ዶላር ጀምሮ፣ ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር በኋላም 60 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ እያሳየ በአሁኑ ወቅትም ወርኃዊ የወርቅ ንግድ ገቢ ወደ 72 ሚሊዮን ዶላር አሻቅቧል፡፡ ‹‹አሠራር በማሻሻላችን የመጣ ውጤት በመሆኑ በሌሎች የወጪ ምርቶችም ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ ለመውሰድ ጥናቶች እየተጠኑ ነው፤›› በማለት ይናገር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የግብርና ምርቶች በሕጋዊ መንገድ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበትን መንገድ የሚያመቻቹና የሚያቀላጥፉ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆናቸው፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከእስካሁነ በተሻለ መጠን እንደሚያድግ እየተጠበቀ ነው፡፡ በቅርቡ ለውጭ በሚቀርበው
የቡና ግብይት ላይ ዝቅተኛውን የዋጋ ደረጃ የሚወስን መመሪያ፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሲያወጣ፣ ዋናውን የዋጋ ቀመርና ስሌት የሚያከናውነው ብሔራዊ ባንክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመመርያው መሠረት ብሔራዊ ባንክ ከሚወስነው የመሸጫ ዋጋ በታች ቡና ወደ ውጭ መላክ አይቻልም፡፡