ኢትዮጵያውያን ወደ ሀብት ሊቀይሯቸው የሚችሏቸው በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ቢኖሯቸውም፣ እምብዛም ከሀብቱ ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ በየዘመኑ የገጠሙ ፖለቲካዊ አለመግባባቶች የሚያስነሱት ግጭት እንቅፋት ከሆኑት ይጠቀሳል፡፡ ይህም በየጊዜው ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው ካለው ጀምሮ በአገር ደረጃ ከሚገኘው ሀብት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ፣ በተለያዩ ባለሙያዎች የተሠሩ ጥናቶችና ምክረ ሐሳቦች በሚፈለገው ደረጃ ከመሬት እንዳይወርዱ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ወደ ተግባር የወረዱትም ቢሆኑ ሊያስገኙ የሚችሉትን ያህል ጥቅም አላበረከቱም፡፡
የዕውቀት ክፍተት፣ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም የመሠረተ ልማት ችግር ኢትዮጵያ ያሏት የተፈጥሮ ሀብቶች በመንግሥት በኩል ነጥሮ አለመታወቅና ወደ ጥቅም አለመቀየር፣ የየአካባቢውን ሕዝብ አለማስተባበርና ተጠቃሚ አለማድረግ የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡
እነዚህም ኢትዮጵያ ከለገሰችው ገበታ ሙሉ የተፈጥሮ ሀብት ሕዝቡ እንዳይቋደስ አድርገዋል፡፡ ይህን መቀየርና ኅብረተሰቡንም አገርንም ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሸገር ፕሮጀክት፣ የአንድነት ፓርክንና የእንጦጦ ፓርክን ከማስዋብ ለጥቀው በአማራ ክልል ጣና ሐይቅ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚገኘውን ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ የሚገኘውን ወንጪ ሐይቅና በደቡብ ክልል ኮንታ የሚገኘውን ኮይሻ የማልማት ውጥን ይፋ አድርገዋል፡፡
የሸገር ፕሮጀክቶችን ወደ ክልሎች ለማስፋፋት፣ ሁሉም ከኢትዮጵያ ሀብቶች ተቋዳሽ የሚሆንበትን ዕድል ለማመቻቸት ያለመውና ‹‹ገበታ ለአገር›› የተሰኘውን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግም በኢትዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት ጥናቶች ተደርገዋል፡፡
ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባገኘነው መረጃ መሠረት፣ ለአሁኑ በገበታ ለአገር የተመረጡት ሦስቱ ሥፍራዎች፣ በቀጣይ አሥር ዓመት በቱሪዝም ልማት ለማልማት መሪ ዕቅድ ከተያዙት 59 ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡
በገበታ ለአገር የሚተገበሩት ሦስቱ ፕሮጀክቶች መንግሥት ከያዛቸው መደበኛ የመሠረተ ልማት ግንባታ የማይካተቱ ሲሆን፣ የመንግሥት በጀት ሳይመደብላቸው ራሳቸውን ችለው የሚሠሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሳውቀዋል፡፡
የፕሮጀክቶቹን የመጀመርያ ዙር ዕውን ለማድረግ ከአገር ውስጥ ሦስት ቢሊዮን ብር ከልማት ተቋማትና ከኅብረተሰቡ ሦስት ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብም ሥራ ተጀምሯል፡፡
ጥቅምት 2013 ዓ.ም. አጋማሽ አካባቢ ባለሀብቶች የሚሳተፉበት የአሥር ሚሊዮንና አምስት ሚሊዮን ብር እራት የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገበታ ለአገር ፕሮጀክት ላይ አሻራውን ያሳርፍ ዘንድም በኢትዮ ቴሌኮም አጭር የጽሑፍ መልዕክት ቁጥር 333 ይፋ ሆኖ ሥራ ተጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሥፍራዎቹ ድረስ በመሄድና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማወያየት ወደ ምድር ሊያወርዷቸው ያሰቧቸው ፕሮጀክቶች የሚከወኑባቸው ሥፍራዎች እንዴት ይገለጻሉ?
ጎርጎራ
ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከጣና ሐይቅ ደቡባዊ ጫፍ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ የተለያዩ ሥፍራዎች ተሠርተው የነበሩ አብያተ መንግሥታትን ማዕከል በማድረግ ብቅ ካሉት ከተሞv አንዷ የጎርጎራ ከተማ ናት፡፡ በአካባቢው የሚገኙትን ታሪካዊ ሥፍራዎች ለመጎብኘት ተስማሚ የመነሻ ወይም የማረፊያ ሰፈርም ናት፡፡ ጎርጎራ በአካባቢው ያሉ አብያተክርስቲያናትንና ገዳማትን ለመጎብኘትም አመቺ ሥፍራ ናት፡፡
ከጎንደር 64 ኪሎ ሜትር ርቀት ከጎርጎራ ወደብ መዝናኛ ክበብ በአጥር ብቻ የተለየችውና በጣና ሐይቅ ዳርቻ የምትገኘው ደብረ ሲና ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ዐምደ ፅዮን ዘመነ መንግሥት አባ ኢስ ዲሮስ በሚባሉ ባህታዊ እንደተሠራች የቤተ ክርስቲያኗ ካህናት ያስረዳሉ፡፡
የቤተ ክርስቲያኗ መቅደስ ዙሪያ እጅግ በሚያስደንቅ የግድግዳ ላይ ሥዕል ያጌጠ መሆኑን ጎብኚዎች ይመሰክራሉ፡፡ ሥዕሉ የተሠራው በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ ያሠሩትም የአፄ ፋሲል እህት ወ/ሮ መለኮታዊት ናቸው ይባላል፡፡
በ1970ዎቹ በወቅቱ የባህል ሚኒስቴር ባለሙያዎች አማካይነት ሳይንሳዊ የቅርስ ጥገናና እድሳት መርህን በተከተለ መንገድ በተደረጉት የእድሳት ዕርምጃዎችና አሁንም በሚደረገው የባለሙያዎች ክትትል ቤተ ክርስቲያኗና ሥዕሎች ጥንታዊ ገጽታዎቻቸውን እንደጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ድጓና ጥንታዊ የብራና መጽሐፍት የቤተ ክርስቲያኗ ቅርሶች ናቸው፡፡
ደብረ ሲና ማርያም ከጎርጎራ ወደብ መዝናኛ ጋር ሰፊ ቁርኝት ስላላት በበርካታ ቱሪስቶች እየተጎበኘች ያለች ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም፣ ትኩረት የምትሻ መሆኗን ከዚህ ቀደም ሪፖርተር በዘገባው አስታውቋል፡፡
ከጎንደር ከተማ 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የጎርጎራ አካባቢ ከሚገኙ ጥንታዊ ገዳማት መካከል ሌላው የማን እንደ አባ አንድነት ገዳም ነው፡፡ ይህ ገዳም በ1326 ዓ.ም. በቀዳማይ አምደጽዮን ልጅ በፃዲቁ አቡነ አሳይ ዘመን እንደተሠራ ይነገራል፡፡
ወደዚሁ ጥንታዊ ገዳም ለመሄድ ከጎርጎራ በእግር 50 ደቂቃ፣ በጀልባ 25 ደቂቃ፣ በመኪና ደግሞ 30 ደቂቃ ይወስዳል፡፡ ማራኪ ውብና አስደሳች የሆነ 150 ሄክታር የሚሸፍን የተፈጥሮ ደን የያዘም ነው፡፡
በተንጣለለው የጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የተመሠረተው ይህ ገዳም ስያሜውን ያገኘው፣ አባ አሳይ ተዓምራዊ በሆነ ጥበቡ ሰፊ ድንጋይ እንደ ጀልባ በመጠቀም በጣና ላይ ይመላለሱ ስለነበር ገዳሙም ማን እንደ አባ እንደተሰኘ አባቶች ያስረዳሉ፡፡
ከጎርጎራ ወደብ የአንድ ሰዓት የጀልባ ጉዞ በኋላ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሠራው የአፄ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ይገኛል፡፡ በቅርብ ርቀት ደግሞ አፄ ላሊበላ አስጀምረውት ነበር የሚባለው የስላሴ ዋሻና አፄ ሠይፈ አርዕድ ያሠሯቸው ሁለት አድባራት ፍርስራሽ ይገኛሉ፡፡ የስላሴ ዋሻ በርካታ በሮችና ክፍሎv ያሉት ሲሆን፣ ውስጥ ለውስጥ ረዥም ርቀት ያስኬዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ የአፄ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ወደ ሚገኝበት ሥፍራ ለመጓዝ ሌላው አማራጭ ከጎርጎራ ወደ ጎንደር በሚወስደው መንገድ የአበርጀ መንደርን ደቡባዊ አቅጣጫ ይዞ በአጃግራ ሚካኤል ጥቂት ርቀት መጓዝ ነው፡፡
በጎርጎራ አቅራቢያ የሚገኘው ሌላው የቅርብ ዘመን የታሪክ አሻራ የአርባ አምስት ደቂቃ የእግር ጉዞ ርቀት ላይ በተለምዶ ‹‹የሞሶሎኒë ተራራ» ተብሎ በሚጠራው ከፍተኛ አምባ ላይ የሚገኘው የሞሶሎኒ ሐውልት ነው፡፡ ከዚህ ስፍራ ሆኖ የጣና ሐይቅና አካባቢውን መመልከት ይቻላል፡፡ ሥፍራው ጣሊያኖች ካምፕ ሠርተው አርፈውበት ነበር፡፡ በዘመኑ የነበረው ሐውልት እስከ ዛሬ እንደቆመ ይታያል፡፡ ሃምሳ ሜትር ርዝመትም አለው፡፡
ከጣና ሐይቅ ደቡባዊ ጫፍ ከባህር ዳር ወደ ሰሜናዊው ጫፍ ለሚደረገው ረዥም የውኃ ላይ ጉዞ የወደብ አገልግሎትም አለ፡፡ ከወደቡ ጋር ተያይዞ በደርግ ዘመን የተገነባውና የወቅቱ ባለሥልጣናት ይዝናኑበት የነበረው ጎርጎራ ሆቴል አሁን ንብረትነቱ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ሲሆን፣ ለጎብኚዎች የመኝታ ክፍሎችና የምግብ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም እንደነገሩን፣ ጎርጎራ የቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ ቢቆይም፣ ማስገኘት የሚችለውን ያህል ገቢ አላመጣም፡፡
ባህር ዳርና ጎንደርን የሚያገናኘውና ከጣና ሐይቅ ዳርቻ የሚገኘው ጎርጎራ ከተማን ለማልማት የተነደፈው ፕሮጀክትም፣ አካባቢውን ተጠቃሚ ለማድረግ ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
ጎርጎራ የተመረጠበት ምክንያት ከተማው ባህር ዳርና ጎንደርን ስለሚያገናኝ፣ ለሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቅርብ በመሆኑ፣ ከባህር ዳር ተነስቶ በየብስም በጣና ሐይቅም (በውኃ) አድርጎ ጎርጎራ መግባት መቻሉ በአጠቃላይም የሰሜን ቱሪዝም ማዕከል በመሆኑ ነው፡፡
ማራኪ መልክዓ ምድርና የተፈጥሮ ዛፎች ገዳማትንና ሌሎች መስህቦች ያሉበትን ጣና ሐይቅ አይቶና በውኃ ላይ ተጉዞ ጎርጎራ መግባት ሲቻል፣ ከጎርጎራ 60 ኪሎ ሜትር በመኪና ተጉዞ ደግሞ ጎንደር ይገባል፡፡ አቶ መልካሙ እንደሚሉትም ይህን አካባቢ ማልማት በርካታ የቱሪዝም ሥፍራዎችን በአንዴ ለመድረስና ከሀብቶቹ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል፡፡
‹‹በማንኛውም ጊዜ ሊጎበኝ የሚችልና እግረ መንገድ በርካታ መስህቦችን፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን፣ ጥንታዊ ገዳማትንና ደሴቶችን ለመጎብኘት ስትራቴጂክ ሥፍራ የሆነው ጎርጎራ፣ በፕሮጀክት ከመያዙ አስቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሥፍራውን ጎብኝተዋል፣ የአካቢውን ማኅበረሰብም አነጋግረዋል›› ያሉት አቶ መልካሙ፣ ሳቢና አስደማሚ በሆነው በዚሁ ሥፍራ የቱሪዝም መስህቦችን በማልማት የአካባቢውን ማኅበረሰብና አገርን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ወንጪ ሐይቅ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በገበታ ለአገር በመጀመርያው ዙር ካስቀመጧቸው ፕሮጀክቶች ወንጪ ሐይቅ ይገኝበታል፡፡ ጎብኚዎች ወደ ሥፍራው ቢያቀኑም፣ ያለውን የተፈጥሮ መስህብ ያህል ጥቅም ያልሰጠው ወንጪ ሐይቅ በተፈጥሯዊ መስህብ የተዋበ አስደማሚ ሥፍራ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በወንጪ ወረዳ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ፣ ከአዲስ አበባ በምዕራብ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በወሊሶና አምቦ መሀል የከተመ ውብ ሥፍራ ነው፡፡
ተፈጥሯዊ መስህብ የተላበሰው ወንጪ ሐይቅ ከባህር ጠለል በላይ 2800 ሜትር ከፍታ ላይ መገኘቱ ለየት ያደርገዋል፡፡ ተራራ ላይ የነገሰውና በእሳተ ገሞራ የተፈጠረው ወንጪ ሐይቅ፣ በተፈጥሮና አገር በቀል በሆነ ደን የተከበበ ሥፍራም ነው፡፡
በኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ በተቀመጠው እሳተ ገሞራ ሥፍራ ላይ የሚገኘው ሐይቁ እስከ ጥልቀቱ 400 ሜትር ሊዘልቅ እንደሚችል የሚያመላክት ጥናት ሲኖር፣ በሥፍራው ሁለት ደሴቶችም ይገኛሉ፡፡ የቅዱስ ቂርቆስ ገዳምም በአንዱ ደሴት ሲገኝ፣ ከገዳሙ ለመድረስ በውኃው ላይ ማቋረጥ ግድ ይላል፡፡
የሐይቁ አካባቢ ፍልውኃና ፏፏቴ መገለጫዎቹ ሲሆኑ፣ ንፁህ ውኃ ኩልል የሚልበትም ነው፡፡ ብርቅዬዎቹን ጨምሮ የተለያዩ ዐዕዋፋት የነገሱበትም ነው፡፡
በአገር በቀል ዛፎች በተደነነው አካባቢ በሚገኘው ደሴት በመካከለኛው ዘመን የተገደመው ቅዱስ ቂርቆስ ይገኛል፡፡ የዱር እንስሳቱን ጨምሮ ውብና ማራኪ በሆነው ወንጪ ሐይቅ የሚከናወነው የወንጪ ፕሮጀክት በመሠረተ ልማት ጉድለት ምክንያት በርካታ ጎብኚዎችን መሳብ ላልቻለው አካባቢ ቀን የሚያወጣ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ አስተባባሪ አቶ አህመድ መሐመድ፣ በውኃና መሬት አቀማመጡ ለየት ያለውና ቱሪስትን የመሳብ ኃይል ያለው ወንጪ ሐይቅና አካባቢው በቱሪስት ቢጎበኝም ያልለማ አካባቢ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ለአካባቢው የታሰበው ዘላቂ ልማት አድቬንቸር ቱሪዝምን ጨምሮ ሌሎች የቱሪስት መስህቦች ሊከናወኑበት የሚችልም ነው፡፡
ወንጪ የቱሪዝም ፍሰቱን ፍትሐዊ ለማድረግ የሚያግዝ ሥፍራ ነው የሚሉት አቶ አህመድ፣ ኅብረተሰቡን አስተሳስሮ በሚተገበረው የወንጪው ገበታ ለአገር ፕሮጀክት የአካባቢው ነዋሪና ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡
ከወሊሶ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኘውን ወንጪ ሐይቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወንዙ ድረስ ወርደው መጎብኘታቸውንና የአካባቢውን ነዋሪ ማነጋገራቸውን ያስታወሱት አቶ አህመድ፣ ፕሮጀክቱ ቱሪዝሙን ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ጋር አስተሳስሮ ለመሄድ ያስችላል ብለዋል፡፡
ኮይሻ
ከሐዋሳ በ282 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ ደግሞ በሻሸመኔ አድርገዉ በወላይታ ሶዶ የሚጓዙ ከሆነ 455 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ በጅማ መንገድ ሲጓዙ ደግሞ በ479 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚያገኙት የደቡብ ክልል የዳዉሮ ዞን በርካታ ፍል ዉሃዎች ፏፏቴዎች ትክል ድንጋዮች የተፈጥሮ ዋሻዎች ጥንታዊ ቤተ መንግስቶችና አበያተ ክርስቲያናት እና ሌሎችም መስህቦች የቢገኙበት ነው፡፡
ኮይሻ በዳውሮ ውስጥ በኮንታ ልዩ ወረዳና በወሎ ወረዳ መካከል ከሚገኘው የኦሞ ወንዝ አካባቢ ይገኛል፡፡ ኮይሻ የኮንታ ልዩ ወረዳና የወሎ መዋሰኛ ልዩ ቀበሌ ነች፡፡ አካባቢው ሰንሰለታማ ተራሮች ያሉበት የቱሪስት መስህብ መሆኑን የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አዳነ ፀጋዬ ነግረውናል፡፡
በአካባቢው ኦሞ ወንዝ የሚገኝበት ሲሆን 2160 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የኃይል ማመንጫ ግድብ እየተገነባ ነው፡፡ ኮይሻ ሰንሰለታማውን ተራራ ተከትሎ የሚገኘውን ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ ሥፍራም ነው፡፡
በጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ ዝርያዉ እየተመናመነ የመጣዉ የአፍሪካ የዝሆን ዝርያን ጨምሮ ጎሽ ከርከሮ ሳላ አጋዘንና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ በደን ሽፋኑ ጉልህ ሲሆን ለዚህም እንደሌሎቹ የኢትዮጵ ፓርኮች በውስጡ የሰዎች ሰፈራም ሆነ እርሻ አለመኖሩ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አቶ አዳነ ይናገራሉ፡፡
በፓርኩ ዉስጥ ጥቅጥቅ ደኖችን የሚያቋርጡ በርካታ ወንዞች ሲኖሩ፣ ዝግና የፓርኩን ክፍል ለሁለት የከፈለ ወንዝ ነዉ፡፡ በፓርኩ ዉስጥ ሃይቆችም ይገኛሉ፡፡
ኮይሻ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ ሥፍራ ከመሆኑም ባሻገር፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ግድብ እየተሠራ ያለበት ሥፍራ ነው፡፡
ከፓርኩ በስተምሥራቅ በዳውሮና በወላይታ መካከል የጊቤ ሦስት ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቆች ሲኖሩ፣ ከወላይታ ወሰን ተያይዘው ያሉት ሰው ሠራሽ ሐይቆች የፕሮጀክቱ አካል ናቸው፡፡ ከወላይታ በኩል ሲገባ በዳውሮ ዞን የተለያዩ መስህቦች አሉ፡፡ የሃላላ ካብ፣ የሶሎ ተፈጥሮ ደን እና የተለያዩ መስህቦች ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ከጨበራ ጩርጩራ ፓርክ በደቡብ ወሰን የሚገኘውን ኮይሻን አይቶና ተሻግሮ ወሎ ይገኛል፡፡ ወሎ ተይዞ ወደ ጂንካ የሚወስድ መንገድ (ደቡብ ኦሞ) አለ፡፡ ፕሮጀክቱ ይህንን በአጠቃላይ አልምቶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ዲዛይን በጨበራ ጩርጩራ የሚገኙ እንስሳትና ዐዕዋፋት እንዳይረበሹ መመገቢያና መራቢያ ቦታቸው እንዳይነካ ጥንቃቄ ተደርጎ መሠራቱን አቶ አዳነ ገልጸው፣ ዲዛይኑ ሲሠራ የአካባቢና አየር ንብረት ባለሙያዎች የፓርክ ባለሙያዎችና ሌሎችም ተሳትፈው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በፓርኩ ውስጥ የሚሠራው መንገድ የፓርክ ደረጃን በጠበቀ መልኩ የፍጥነት ገደብ፣ የመንቀሳቀሻ ሰዓትና ሌሎችም ተካተው የሚሠሩ ይሆናል፡፡ ፕሮጀክቱ እንስሳቱን በማይነካና በማይረብሽ መልኩ የሚከናወን ነው፡፡
እንደ ሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች የሰው ሰፈራና እርሻ በሌለበት ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ አገር በቀል የሆኑትን ጨምሮ በርካታ የዛፍ ዓይነቶች የሚገኙበት ደን፣ የትላልቅ አጥቢ እንስሳት፣ የስድስት ሐይቆች መገኛና የሞቃታማና ቀዝቃዛ ፏፏቴዎች መዝናኛም ነው፡፡
አቶ አዳነ እንደነገሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአካባቢውን ማኅበረሰብ አወያይተዋል፣ ፓርኩን ጎብኝተዋል፣ ሥፍራውን አይተዋል፡፡ የኮይሻው የገበታ ለአገር ፕሮጀክትም በሥፍራው የሚገኙ አምስት አካባቢዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
የገበታ ለአገር የመጀመርያው ዙር ፕሮጀክት ያቀፋቸው እነዚህ ሥፍራዎች ማኅበረሰብ አቀፍ ዘላቂ ልማትን ዕውን ለማድረግ የተወጠኑ ናቸው፡፡ ከተጠኑትና በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ ይሆናሉ ከተባሉት 59 የቱሪዝም ሀብት ፕሮጀክቶች የሚካተቱት ሦስቱ ፕሮጀክቶች፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይፋ የተደረጉት እሑድ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግም 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡