Friday, September 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ቤቶች ኮርፖሬሽን በሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ 510 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ሊገነባ ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአሥር ዓመታት ውስጥ 4.2 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል

  ላለፉት 44 ዓመታት በተለያዩ አደረጃጀቶችና ስያሜዎች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ግንባታቸው በ2013 ዓ.ም. የሚጀመሩ 510 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን በሦስት ቢሊዮን ብር ለማስገንባት የኮንትራት ውል ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ተፈራረመ፡፡

  አዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተሻለ ጥራት፣ በቅናሽ ወጪና በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል የተባለውን ዘመናዊ የሕንፃ ግንባታ ኮርፖሬሽኑ ውል የፈረመው ኦቪድ ኮንስትራክሽን (Ovid Constriction) ከሚባል አገር በቀል ተቋራጭ ጋር ሲሆን፣ ግንባታውም በ18 ወራት እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል፡፡

  ኮንትራቱን የተፈራረሙት የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማልና የኦቪድ ኮንስትራክሽን (Ovid Constriction) ማኔጂንግ ዳይሬከተር አቶ ዮናስ ታደሰ በሸራተን አዲስ ሲሆን፣ በዕለቱ ቤቶቹ ይገነባሉ በተባሉበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ ከሮባ ዳቦ ቤት ሁለት መቶ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና ‹‹ገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር›› ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ወ/ሮ ደሚቱ አምቢሳ፣ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)፣ አቶ ረሻድ ከማልና ሌሎች የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ ተወካዮች የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

  የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ እንደገለጹት፣ ግንባታው ከፍተኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በከፍተኛ ጥራት፣ በአጭር ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነባ ነው፡፡

  በአዲሱ ቴክኖሎጂ የሚገነቡት 510 ቤቶችን የያዙ 16 ባለ አሥር ፎቅ ሕንፃዎች ሲሆኑ፣ ተቋራጩ በ18 ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለኮርፖሬሽኑ እንደሚያስረክብ ተናግረዋል፡፡ በሦስት ሔክታር ላይ የሚሠሩት ሕንፃዎች ባለ አምስት፣ ባለ አራትና ባለ ሦስት መኝታ ቤቶች ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ ቤቶቹ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ከመሆናቸው በተጨማሪ የዕለት ከዕለት ኑሮአቸው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችንና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ተቋማትን አረንጓዴ ቦታዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችንና መዝናኛ ቦታዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  ሕንፃዎቹ የሚገነቡት አልሙኒየም ፎርምዎርክ (Aluminum Formwork) በሚባል ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ የሚመጣውም ከደቡብ ኮሪያ ኩም ካንግ ካይንድ (Kumkan Kind)  ከሚባል ኩባንያ ሲሆን፣ የቤቶቹን ዲዛይን የሠራው ደግሞ የህንድ ኩባንያ መሆኑን አቶ ረሻድ ተናግረዋል፡፡

  የኮንትራቱን ፊርማ የፈጸሙት የኦቪድ ሕንፃ ግንባታ ተቋራጭ (Ovid Constriction) ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ታደሰ ስለ ኩባንያውና ግንባታው እንደገለጹት፣ የድርጅታቸው ራዕይ ልማት ነው፡፡ ለዚህም ነው በቤት ልማት ዘርፍ የተሰማራው፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ቀዳሚ ኩባንያ መሆኑንና ተገጣጣሚ ግድግዳ (ማግኔዢየም ቦርድ) ሥራ በስፋት መሥራቱ በምሳሌነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል፡፡ አሁን ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት የኮንትራት ውል በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚያደርጉት አዲስ ቴክኖሎጂ አልሙኒየም ፎርምወርክ የሚባል ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ የቤት እጥረትን ለመቅረፍ ተመራጭና ልዩ ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቴክኖሎጂው የደቡብ ኮሪያው ኩምካንግ ካይንድ ኩባንያ ሲሆን፣ እሳቸው የሚመሩት ተቋራጭ ደግሞ የዚህ ኩባንያ ሰርቲፋይድ ፓርትነር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቴክኖሎጂው ከ1979 ዓ.ም. ጀምሮ በዓለም ላይ ብዙ የተሠራበትና ተመራጭ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን ላይ በአፍሪካ አገሮች በስፋት እየተዋወቀና በኬንያ፣ በጋናና በአልጄሪያ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑንም አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው የምርት ችግር የሌለበትና የራሱ ሰባት ማምረቻ ፋብሪካዎች ያሉት መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በአፍሪካ ሲተገበር የቆየውን አዲስ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል መፈጸማቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ድርጅታቸው የሚገነባውን ‹‹ገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር›› ፕሮጀክትን ዲዛይን የሠራው የ21 ዓመታት ልምድ ያለው የህንድ ኩባንያ መሆኑንና እሱም ኩባንያ የኩም ካንግ ካይንድ ኩባንያ ሰርቲፋይድ ፓርትነር መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

  የመሠረት ድንጋይ ካስቀመጡት አንዷ የነበሩት የሚኒስትሮች ካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ አምቢሳ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ መንግሥት ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ መተግበር ከሚጀምርባቸው የአሥር ዓመታት መሪ ዕቅዶች መካከል ትኩረት ሰጥቶ ከሚያስፈጽማቸው የትኩረት መስኮችና የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ የከተማ ልማት ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ በመሪ ዕቅዱ እንደተመለከተው በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት 4.2 ሚሊዮን ቤቶች ይገነባሉ፡፡ በከተሞች የመኖሪያ ቤቶች አቅርቦትን ማሻሻል ማለት ነዋሪዎች የተረጋጋ ሕይወትን እንዲመሩ፣ ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆና በቀን ተቀን ሥራቸው ውጤታማና ምርታማ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት ከ400 ሺሕ በላይ ቤቶችን በመገንባት ለዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቁመው፣ በከተማው የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በቤት ፍላጎትና አቅርቦት የሚታየው ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ነዋሪው ለከፍተኛ የቤት ኪራይ መዳረጉንም ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በሚገጥማቸው የመኖሪያ ቤት ችግር ምክንያት ሥራቸውን በተረጋጋ መንፈስ ለመሥራት እንደሚቸገሩም አክለዋል፡፡ በመሆኑም በከተሞች የመኖሪያ ቤቶችን እጥረት ለመቅረፍ የተቀረፁ አገራዊ ፕሮግራሞችን የማስፈጸም ኃላፊነት የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን መሆኑን ጠቁመው፣ ያሉበትን ችግሮች ጭምር በመፍታትና የሪፎርም ሥራዎችን በመሥራት የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት ጥረት በማድረግ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑንንም ተናግረዋል፡፡

  የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ደግሞ እንደተናገሩት፣ በቤት ልማት ላይ መረባረብ ካልተቻለ አሁን ያለው የቤት ልማት ዕድገት፣ የቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ማመጣጠን አይቻልም፡፡ በመሆኑም መንግሥት አዲስ ስትራቴጂ መቅረፁን ተናግረዋል፡፡ የቤት ልማት ከፍተኛ ፋይናንስ ስለሚጠይቅ መንግሥት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ማምጣትና አዳዲስ ፖሊሲዎችን ከማስቀመጥ ባለፈ የሚሠሩ ሥራዎችን ኮኦርዲኔት ማድረግ ላይ ብቻ በማተኮርና ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸው ዜጎች ብቻ ቤት በማቅረብ ላይ እንዲወስን መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ የግል ዘርፉ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በተለይ በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ የቤት ልማትን በማፋጠን አቅርቦቱ መስተካከል እንዳለበት መንግሥት ማመኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 4.2 ሚሊዮን ቤቶችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ይህ ማለት ግን የሕዝባቸው ብዛት በ5.4 በመቶ እያደጉ ላሉ ከተሞች በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ ይፋ የተደረገውን ቴክኖሎጂ ዓይነት ሌሎችንም አዋጭነታቸውን በመፈተሽ መጠቀም ወይም ወደ ሥራ መግባት አለባቸው፡፡ አዋጭነታቸውን ዓይቶ ማስገባት እንጂ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ እንደማያወጣ አድርጎ መግፋት ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

  የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ደግሞ እንደተናገሩት፣ ተቋማቸው በአደረጃጀት የተደገፈ ተስማሚ  ቴክኖሎጂዎችንና የአሠራር ፈጠራዎችን የመፈተሽ፣ የመመርመርና ከአገራዊ ሁኔታዎች ጋር ተስማሚ ሆነው የሚበለፅጉበትንና አጠቃላይ አገር አቀፍ የልማት ሥራዎችን ተደራሽ የሚያደረጉበትን አሠራሮች በመቀመር፣ በሀብት፣ በቅልጥፍናና በጉልበትን ጨምሮ ቆጣቢ ሥራዎችን ለመሥራት የተዘጋጀ የአመራርና የድጋፍ አሰጣጥ ከባቢ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች የማቅረብ ጅማሮ ሊበረታታ የሚገባው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንና አገር በቀሉ ኦቪድ ኮንስትራክሽን ከደቡብ ኮሪያውና ከህንዱ ኩባንያዎች ጋር በመሆን የሚተገብሩት የገርጂ ዘመናዊ መኖሪያ መንደር ፈጣን የግንባታ ዘይቤ በኢትዮጵያ አማራጭ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ጉልህ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

  ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከሚያስገኘው ጥቅም በተጨማሪ፣ በግንባታው ወቅት በሥራው በቀጥታ ተሳታፊ ለሚሆኑ በ7,500 ሰዎችና ከሳይት ውጭ ለሆኑ 500 ሰዎች በድምሩ ለ8,000 ባለሙያዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ረሻድ ገልጸዋል፡፡

  በቴክኖሎጂ ሽግግር ከሚገኘው ጠቀሜታ በተጨማሪ ለ50 ቴክኒሻኖች በቴክኖሎጂ ገጠማ የሙያ ሰርተፍኬት እንዲያገኙ እንደሚደረግም አክለዋል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተርስ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉና የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በግንባታ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለመጻፍ ለሚፈልጉ 20 ተማሪዎች የጥናት ወጪያቸውን ሙሉ በሙሉ እንደሚሸፈንላቸውም አቶ ረሻድ ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በሚካሄድበት አካባቢ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙና መኖሪያ ቤት ለሌላቸው 50 የወረዳው ነዋሪዎች አንድ የጋራ መኖሪያ ሕንፃ በመገንባት በነፃ እንደሚያበረክትም (ተቋራጩ) ገልጸዋል፡፡

  የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አሁን የሚጠራበትን ስያሜ ያገኘው በ2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ ላለፉት 28 ዓታት ግንባታ አቋርጦ እንደነበር አቶ ረሻድ ገልጸዋል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 398/2009 እና በደንብ ቁጥር 427/2010 ባሳለፈው ውሳኔ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ግብዓቶች አቅራቢ ይባል የነበረውን ድርጅት በመቀላቀል በተጠቀሰው ስያሜ የልማት ድርጅት ሆኖ መደራጀቱን አክለዋል፡፡

  ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ የአገር ግንባታና ከድህነት የመውጣት ሪፎርም መነሻ በማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንና ተልዕኮውን ለማስፈጸም በሚያስችል ደረጃ ማስተካከያ ማድረጉን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ብቃት ያላቸውን አመራሮችና ባለሙያዎችን ወደ ተቋሙ ማስገባቱንም ተናግረዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዓመታዊ ገቢ በ2009 ዓ.ም. 308 ሚሊዮን ብር የነበረ ቢሆንም፣ በ2012 ዓ.ም. 2.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለኮሮና መከላከያ አገራዊ ጥሪ አሥር ሚሊዮን ብር፣ ለሜቄዶንያ አምስት ሚሊዮን ብርና በኮሮና ምክንያት ለደንበኞቹ የአራት ወራት 50 በመቶ ኪራይ በመቀነስ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ማኅበራዊ ግዴታውን መወጣቱንም አስረድተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ማዕከላዊ ቦታዎች በስምንት ሳይቶች 13 ብሎኮች እስከ አሥር ፎቅ ከፍታ ያላቸው ዘመናዊና ምቹ የመኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ቤቶችን እየገነባ መሆኑንና በ2013 በጀት ዓመትም ከፍታቸው እስከ 21 ፎቅ የሚደርሱ ሕንፃዎችን ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት መጨረሱንም አክለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ተቆጥረው የተለዩ 18,456 ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ 11,861 መኖሪያና 6,595 የንግድ ድርጅቶች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ አጠቃላይ የኮርፖሬሽኑ ሀብት ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች