ከ800 ቢሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ወጪ የሚጠይቅ የአሥር ዓመት የኤሌክትሪክ ልማት ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ ወደ ተግባራ ሊገባ መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አመለከተ።
በኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ይኸው የኤሌክትሪክ ኃይል ልማትና አቅርቦት ማስተር ፕላን (ፍኖተ ካርታ) ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን መረጃው የሚጠቁም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወደ 19 ሺሕ ሜጋ ዋት ለማሳደግ የታለመ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ በገጠራማ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለውን 16 በመቶ የሚሆን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሽፋን ወደ 56 በመቶ ለማሳደግ የታለመ መሆኑንም ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 4,300 ሜጋ ዋት ገደማ ሲሆን፣ የአገሪቱ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ደግሞ በየዓመቱ በ20 በመቶ በመጨመር ላይ በመሆኑ ማስተር ፕላኑ ይህንን የኃይል ፍላጎት ለመመለስ ታሳቢ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል።
ይህንን ለማሳካት በተዘጋጀው ማስተር ፕላን ውስጥ አዳዲስ የኤሌክትሪክ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ትልቅ ድርሻ የተሰጣቸው ሲሆን፣ የእነዚህም ወጪ ከ431 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተገምቷል።
በዚህ ውስጥ የፀሐይና የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች በገጠራማ ቦታዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማድረስ በዋናነት ታሳቢ መደረጋቸውን መረጃው ያመለክታል።
በፀሐይና በንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶችን የተመለከተ ራሱን የቻለ ማስተር ፕላን ከጥቂት ዓመታት በፊት በቻይና ኩባንያ ተጠንቶ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ለአጠቃላይ ማስተር ፕላኑ ግብአት ሆኗል።
በዚህም መሠረት ከሁለቱ የኃይል አማራጮች ስምንት ሺሕ ሜጋ ዋት ገደማ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በዕቅድ መያዙን መረጃው ያመለክታል። በዚህ ኢንቨስትመንትም በውኃ ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አሁን ከሚገኝበት 90 በመቶ ወደ 70 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተወጥኗል።
በአሥር ዓመት ማስተር ፕላኑ ከታቀደው 800 ቢሊዮን ብር የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ውስጥ፣ 106 ቢሊዮን ብር የሚወጣው የተጀመረው በግንባታ ሒደት ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። የተቀረው ወጪ ደግሞ ለኃይል ማስተላለፊያና ማሰራጫ መስመር ግንባታዎች እንደሚውል ታውቋል።
በተጨማሪም ማስተር ፕላኑ ለጎረቤት አገሮች ኤክስፖርት እየተደረገ ያለውን የኃይል ሽያጭ አሁን ካለበት ከ300 እስከ 400 ሜጋ ዋት የኃይል ሽያጭ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለመጨመር አልሟል።
በዚህም መሠረት ወደ ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት በመጭው 2013 ዓ.ም. መሸጥ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንና በሁለቱ አገሮች በተደረሰው ስምምነት መሠረት 400 ሜጋ ዋት ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ እንደሚጀመር ለማወቅ ተችሏል።
በተጨማሪም ወደ ጂቡቲ ሁለተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ በመጨመር የኃይል አቅርቦቱን ለማሳደግ የታሰበ ሲሆን፣ የሁለተኛው ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ የታቀደው በዲቼቶ በኩል እንደሆነም መረጃው ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት እየተመረተ ከሚገኘው 4,300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 324 ሜጋ ዋት የሚሆነው ከንፋስ ኃይል የሚገኝ ሲሆን፣ የተቀረው ከሞላ ጎደል ከውኃ ኃይል እንደሚገኝ መረጃው ያመለክታል።