Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በኮሮና የተዘጋው የቱሪዝም ዘርፍ ሊከፈት ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የተዘጋውን የቱሪዝም ገበያ ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ታወቀ፡፡

  በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአገሪቱ ኤርፖርቶች ያልተዘጉ ቢሆንም፣ የቱሪስት መዳረሻዎች ተዘግተው ከርመዋል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጣሉ የጉዞ ክልከላዎች ምክንያት የቱሪዝሙ ገበያ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል፡፡

  ጥቂት ሆቴሎች ለለይቶ ማቆያነት እያገለገሉ ቢሆንም፣ አብዛኛው ሆቴሎች ተዘግተው ገሚሱ ዕድሳት ላይ ናቸው፡፡ በርካታ ሠራተኞች ያሏቸው ሆቴሎች ክፉኛ የተጎዱ ሲሆን፣ የአስጎብኚ ድርጅቶች ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ሆቴሎች ከባንኮች ለክፉ ቀን የሚሆን ብድር እያገኙ ሲሆን፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ግን የገንዘብ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ከነሠራተኞቻቸው ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለይም በየክልሉ የሚገኙ አስጎብኚዎች ከነቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል፡፡

  የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ የተዘጋውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማንቀሳቀስ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በር ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡

  ዓለም አቀፍ ትራቭል ኤንድ ቱሪዝም ካውንስል ያወጣውን የጉዞ ፕሮቶኮል በመቀበል፣ ሊደረጉ የሚገባቸውን የጤና ጥንቃቄዎች ላይ ዝግጅት እየተረገደ እንደሆነ አቶ ስለሺ ገልጸዋል፡፡ ፕሮቶኮሉ በጉዞ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጋላጭነት የሚቀነስ እንደሆነ ታውቋል፡፡

  ቱሪዝም ኢትዮጵያ የጉዞ ፕሮቶኮል አዘጋጅቶ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚመራው ቦርድ በቅርቡ አፅድቋል፡፡ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሆቴሎች፣ ክልሎችና አስጎብኚ ድርጅቶችን በማስተባበር በቱሪስት መዳረሻዎች አስፈላጊው የፀረ ተዋስያን ርጭት እንዲካሄድ፣ ሳኒታይዘር አቅርቦት እንዲኖርና መታጠቢያ ቤቶች እንዲገነቡ በመሥራት ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

  የተዘጋጀው የጉዞ ፕሮቶኮል ለቱሪስቶች ከኤርፖርት ጀምሮ በመኪኖች፣ በሆቴሎችና በቱሪስት መስዕቦች ሊደረጉ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች ይዘረዝራል፡፡

  የቱሪስት መኪኖች በግማሽ አቅማቸው እንዲጭኑ፣ አስጎብኚዎች እንደ ሳንታይዘር ማስክና ጓንት ያሉ መከላከያዎች ይዘው እንዲጓዙ ያዛል፡፡ የጉዞ ፕሮቶኮሉ ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደተዘጋጀ አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡

  ‹‹እንደ ላሊበላና ጎንደር ያሉ ዋና ታሪካዊ መስዕቦቻችን መታጠቢያ ቤት የላቸውም፡፡ የብሔራዊ ሙዚየሙ መታጠቢያ ቤት ንፁህ አይደለም፡፡ ዩኒቲ ፓርክ ደረጃቸውን የጠበቁ መታጠቢያ ቤቶች አሉት፡፡ በክልሎች በሚገኙ የቱሪስት መስዕቦች መታጠቢያ ቤቶች መገንባት አለብን፤›› ያሉት አቶ ስለሺ፣ ከክልሎች ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ ውይይት እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡

  የቱሪስት መዳረሻዎቹ ገቢ ሲያስገቡ የነበሩ በመሆኑ ክልሎች መታጠቢያ ቤቶች ሊገነቡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቢያንስ ተንቀሳቃሽ መታጠቢያ ቤቶች ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ ሳኒታይዘር ሊቀርብ ይገባል፡፡ ቱሪስቶች ከገንዘብ ንክኪ እንዲኖራቸው የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መቀነስ ያስፈልጋል፤›› ያሉት አቶ ስለሺ፣ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ብቻውን ሊወጣ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ አክለውም ቱሪዝም ኢትዮጵያ በሐረር ከተማ ሞዴል ጣቢያ እንደሚገነባ ተናግረዋል፡፡ የሐረር ሞዴል ጣቢያው የፀረ ተዋስያን መርጫ ማሽን፣ መታጠቢያ ቤት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡

  ቱሪዝም ኢትዮጵያ በጢያ፣ ብሔራዊ ሙዝየምና ሐረር የፀረ ተዋስያን ርጭት አከናውኗል፡፡ በቅድሚያ የአገር ውስጥ ቱሪዝሙን ማንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ስለሺ፣ በቀን በርካታ ጎብኚዎች የሚያስተናግዱት ብሔራዊ ሙዝየምና ዩኒቲ ፓርክን አስፈላጊው ጥንቃቄ በማድርግ መክፈት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

  የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አንድነት ፈለቀ ማኅበሩ የጉዞ ፕሮቶኮሉን ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱን ገልጸው፣ ፕሮቶኮሉን ከማዘጋጀት ባለፈ ሊተገበሩ የሚገባቸው ዝግጅቶችን መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ከ250 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ከዓለም አቀፍ አስጎብኚ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ቱሪስቶችን ለመሳብ ዝግጁ መሆኑን የጠቀሱት አንድነት፣ መንግሥት አገሪቱን ለቱሪስቶች መክፈቱን ይፋ እስከሚያደርግ እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ማስተዋወቁ ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ በፕሮቶኮሉ የተዘረዘሩት ጉዳዮች መሬት ላይ ወርደው በተግባር ሊሠሩ ይገባል፡፡ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች ሊስተካከሉ ይገባል፤›› ያሉት አንድነት፣ ፕሮቶኮሉ እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረግ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሥልጠና ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

  ቱሪዝም ኢትዮጵያ የማስተዋወቂያ ቪዲዮዎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በማኅበራዊ ትስስር ቅስቀሳ እንደሚካሄድ፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አማካይነት ኢትዮጵያ በሯን ለቱሪስቶች መክፈቷን የሚገልጹ መረጃዎች እንደሚሠራጩ አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ በሚካሄደው የአምባሳደሮች ስብሰባ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በራችንን የምንከፍትበት ቀን በቅርቡ ማሳወቅ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

  አስፈላጊው ዝግጅት ከተጠናቀቀ የተዘጉ የቱሪስት መስዕቦች ከኅዳር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍተው ጎብኚዎችን ማስተናገድ እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች