Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች ከውጭ የሚበደሩበት አዲሱ ሥርዓት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለትግበራ ካዘጋጃቸውና ማብራሪያ ከሰጠባቸው መመርያዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ በውጭ ምንዛሪ ብድር ማግኘት የሚችሉበት አዲስ ድንጋጌ ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡

በኢትዮጵያ የባንክ ሕግ መሠረት ለዓመታት ሳይፈቀድ ተከልክሎ የቆየ አሠራር ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ባንኮች ከውጭ ብድር በማግኘት ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች መልሰው በብድር እንዲያቀርቡ የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር ታስቦ የወጣ መመርያ መተግበር ይጀምራል፡፡

ስለመመርያው የቀረበው ማብራሪያም ይህንኑ ዓላማ አስረድቷል፡፡ ባንኮች ከውጭ አበዳሪዎች በውጭ ምንዛሪ ተበድረው የውጭ ምንዛሪ ለሚጠይቁና ለተፈቀደላቸው ለደንበኞቻቸው በዚያው በውጭ ምንዛሪ ማበደር እንዲችሉ የሚያስችለው አማራጭ ዘዴ የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡

ይህ መመርያ ከመውጣቱ በፊት ብሔራዊ ባንክ ከቀሩት ባንኮች ጋር እንደመከረበትና ረቂቅ መመርያውም እንዲደርሳቸው መደረጉ ታውቋል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ግን የመጨረሻውና ዋናው መመርያ ወደ ባንኮች ባይደርስም፣ ብሔራዊ ባንክ ግን መመርያውን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ታውቋል፡፡

የመጨረሻው የመመርያው ይዘት ይፋ ባይሆንም በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀውን መመርያ የተመለከቱ የባንክና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት መመርያው አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን ቢያምኑም፣ ጥንቃቄ የሚሻ እንደ ሌሎች ጉዳዮች እንዲሁ በደብዛዛው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በመመርያው ዙሪያ ዘለግ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡ ስለመመርያው አስፈላጊነት ሲናገሩ፣ ‹‹የአገሪቱ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ ብድር መወሰድ የሚከለክለውን ሕግ በማንሳት በውጭ ምንዛሪ ብድር እንዲወስዱ መፈቀዱ ዋና ጠቀሜታው ከተለመዱት የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዘዴዎች ባሻገር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ አማራጮችን ማየት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ የወጣ  መመርያ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በብድር የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ የአቅርቦት ክፍተት ከማስታገስ አንፃር ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ እስካሁን ሲሠራባቸው የቆዩት የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጮች መካከል የወጪ ንግድ፣ የመንግሥት ብድር፣ አልፎ አልፎም በወጪ ንግድ ላይ የተመሠረቱና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ኩባንያዎች ከሚያገኙት ብድር በተጨማሪ ባንኮች በቀጥታ መበደር የሚችሉበት አማራጭ ማምጣቱ ለውጭ ምንዛሪ አቅርቦቶች ችግር መቃለል መመርያው እንዳስፈለገ ይገለጻል፡፡

ይሁን እንጂ የመመርያ አተገባበር ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፤ በዘርፉ ከፍተኛ ክህሎትና ዕውቀት ባላቸውና የምንዛሪ ለውጥ ላይ የሚታዩ እንቅስቃዎችን በሚገባ ተረድተው በሚተነትኑ ባለሙያዎች ዕውቀት ሊተገበር ይገባዋል በማለት ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ ብሔራዊ ባንክ አይነኬ የነበሩ ሕጎችና አሠራሮችን እየፈተሸ ለአገር ጥቅም እንደሚያስገኙ የታመነባቸውን በመለየት እንዲተገበሩ ማድረጉ ያስመሰግነዋል ይላሉ፡፡ ባንኩ አዳዲስ አሠራሮችን ለመተግበር ያለው ፍላጎትና ተነሳሽነትም እየታየ እንደሚገኝ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚታዩ ችግሮች አጋዥ መፍትሔዎችን ለማምጣት፣ አማራጮችን ለማየትና ነባር አሠራሮችን ለመለወጥ ቆራጥ መሆናቸውም የባንኩን አመራሮች አስመስግኗቸዋል፡፡

ሆኖም ከውጭ በብድር እንደሚመጣ የሚታሰበው የውጭ ምንዛሪ ሀብት የሚገኝበት መንገድና አሠራሩ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ሳያሳስቡ አልቀሩም፡፡ ‹‹ባንኮች ዝም ብለው እየተነሱ ይበደራሉ ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም የሚያስቀምጡት መስፈርት ይኖራል፡፡ አበዳሪዎችም ቢሆኑ ዝም ብለው ወለድ ለማግኘት ብለው ብድሩን ይለቃሉ ብዬ አላስብም፤›› በማለት ሐሳባቸውን ለሪፖርተር ያጋሩ አንድ የባንክ ባለሙያ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም እንዲህ ያሉ መመርያዎች ሲወጡና ተግባር ላይ ሲውሉ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው ምክራቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ምንዛሪና ከአገሪቱ የመክፈል አቅም ጋር ሊያያዝ የሚችል በመሆኑ፣ በውጭ ምንዛሪ የተገኘውን ብድር ጊዜው ሲደርስ በውጭ ምንዛሪ መክፈል ካልተቻለ አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል አሳስበዋል፡፡ ባለሙያው እንደሚገልጹት ብሔራዊ ባንክ በረቂቅ መመርያው ላይ ያስቀመጣቸውና ሥጋትን ለመቀነስ የሚያግዙ አንቀፆች ቢካተቱበትም፣ በግልጽ አስተያየታቸውን ለመስጠት ግን የመጨረሻውንና ጸድቆ ለትግበራ የተዘጋጀውን መመርያ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰዋል፡፡

በረቂቅ መመርያው የአደጋ ሥጋት እንዳያስከትሉ በማሰብ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጣቸው ገደቦች ውስጥ በአብነት የተጠቀሰው አበዳሪው ድርጅት ለኢትዮጵያ ባንኮች የሚሰጠው ብድር በስድስት ዓመታት ውስጥ የሚከፈል መሆን አለበት የሚለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሦስቱ ዓመት ክፍያ የማይከፈልበት መሆን አለበት ብሎ ማስቀመጡ አንደኛው የሥጋት መቀነሻ ነጥብ ነው፡፡

ይህን መደንገግ ያስፈለገበት ምክንያት አገሪቱ ያለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት  ሁኔታ ስለሚታወቅ ነው፡፡ የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪም፣ ራሳቸው የውጭ ምንዛሪ የሚያመነጩት ኩባንያዎች ቢሆኑም አምርተውና ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት ለገበያ አቅርበው አለያም ፕሮጀክቶቻችን አጠናቀው የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ሥራዎች ውስጥ በመሰማራት ዕዳቸውን እስኪመልሱ ድረስ ጊዜ ስለሚያስፈልጋቸው፣ የሦስት ዓመት የችሮታ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ በመመርያው መቀመጡ ወደፊት ሊያጋጥም የሚችለውን ሥጋት ሊቀንሰው እንደሚችል ታምኖበት ነው፡፡ ችግሩ ግን በዚህ መልኩ የተቀመጠውን የመመርያውን ድንጋጌ የውጭ አበዳሪዎች ምን ያህል ሊቀበሉት ይችላሉ የሚለው ነው፡፡

አበዳሪው ለሦስት ዓመታት ብድር ሳይከፈለው እንዲቆይ ሲጠየቅ ይህንን  የሚቀበልበት ምክንያት ምንድነው? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ስለሚችል መመርያው በሚፈለገው መንገድ ሊፈጸም የመቻሉ ነገር በሒደት ታይቶ አፈጻጸሙ ላይ ማሻሻያ ማድረግ የሚቻልበት አሠራር ማስቀመጥ ጠቃሚ እንደሚሆን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

ሌላው ጉዳይ ባንኮች በዚህ መንገድ ብድር ከውጭ ሲያመጡ ለብሔራዊ ባንክ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ገዥው ባንክ ባስፈለገውና ባመነበት ጊዜ እንደአስፈላጊነቱ የሚያስቀምጣቸው አሠራሮች ሊኖሩ ይችላሉ በማለት በምሳሌነት ያነሱትም ብድሩ መከፈል በሚጀምርበት ወቅት በምን አግባብና ከየት ሊገኝ በሚል የውጭ ምንዛሪ መከፈል እንዳለበት ብሔራዊ ባንክ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ በመሆኑም የመመርያው አተገባበር በርካታ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዮች እንዳሉበት አብራርተዋል፡፡

‹‹ብድር ተበድረህ ባትከፍል ዕዳው ወደ አገር ዕዳነት የሚተላለፍ በመሆኑ፣ መመርያው በጥንቃቄ መተግበር አለበት፤›› በማለት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት በርካታ የክትትል ሥርዓቶችን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

ሌላኛው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያም የመመርያው አተገባበር ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው በመስማማት፣ ከዚህ ቀደም ለባንኮች ከተላከው ረቂቅ መመርያ በመነሳት እንደሚገልጹት፣ ከውጭ የሚመጣውን ብድር ማግኘት የሚችሉት የውጭ ምንዛሪ አመንጪ የሆኑ ኩባንያዎች እንደሆኑ አውስተው፣ በውጭ ምንዛሪ ተበድረው በውጭ ምንዛሪ ምርቶችና አገልግሎቶቻቸውን በሚያቀርቡት ዘርፎች ላይ ማተኮሩ የተበደሩትን ብድር በውጭ ምንዛሪ ለመመለስ ስለሚያስችል መመርያው ተገቢ ትኩረት እንደሰጠ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና በዚህ መመርያ መሠረት ከውጭ በብድር ከሚገኘው ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ በመተካት ለሚያመርቱ ኩባንያዎች የማሽነሪ ግዥ ቢፈጸምላቸውና ባንኮችም በራሳቸው ሀብት መክፈል የሚችሉበት አሠራር በመመርያው ቢያካትት የተሻለ ውጤት ሊገኝበት እንደሚችል  አስረድተዋል፡፡  

በተወሰነ ደረጃ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በሚመረቱት የሚተኩ ኩባንያዎች ማምረቻ መሣሪያዎች ለማስመጣት ሲያስፈጉ፣ የውጭ ምንዛሪ በወረፋ ከሚጠብቁ ይልቅ ከውጭ በብድር በሚገኘው ገንዘብ ቢስተናገዱ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አክለዋል፡፡

ከመመርያው ጋር በተያያዘ እንደ ሥጋት የታየውና ሊታሰብበት ይገባል የተባለው ሌላው ነጥብ፣ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ተመንን የምታስተዳድረው በከፊል ገበያ መር በሆነ ዘዴ በመሆኑ፣ የምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ እንዴት የብድሩ አከፋፈል በምን መንገድ  ሊስተናገድ ይችላል የሚለው ጉዳይ ግልጽ አለመሆኑ አለመደረጉ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሊመጣ የሚችለውን ሥጋት እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል ከወዲሁ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

ከሦስት ዓመት በኋላ የችሮታ ጊዜው አልቆ የብድር ዕዳው መከፈል በሚጀምርበት ወቅት የወለድ ምጣኔው በምን ስሌትና አግባብ ታስቦ ይከፈላል የሚለውን ማየቱ ተገቢ እንደሆነ ያብራሩት ባለሙያ፣ በዓለም ገበያ የምርቶች ዋጋ መዋዠቅ ከሚያስከትለው ለውጥ ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለው ክፍተት የሚስተናገድበት ሥርዓት ከወዲሁ ታይቶና አሠራሮችም ከወዲሁ ሊዘጋጁ እንደሚገባቸው ተጠይቋል፡፡ ለወጪ ንግድ የሚለው ምርት በዓለም ገበያ ዋጋው ቢቀንስ፣ ተበዳሪው አካል ወይም ላኪው ወገን የተበደረውን የውጭ ምንዛሪ ለመክፈል የሚያበቃ ገቢ ካላገኘ ምን ሊፈጠር ይችላል? በምን አግባብስ ይስተናገዳል የሚለውን የሚመልስ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

የዚህ ዓይነቱ ክፍተት ሊያስከትል የሚችለው ትልቁ ችግር፣ የውጭ ምንዛሪ ዕዳ ወይም ከውጭ የሚገኝ ዕዳ መከፈል በሚጠበቅበት ወቅት ካልተከፈለ፣ መጨረሻው በአገር ላይ ዕዳ መጫን ስለሚሆን፣ መመርያውን ከዚህ አኳያ መቃኘት እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ ጥንቃቄ ካልተደረገበት መመርያው የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለማቃለል ታልሞ የአገር ዕዳ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ባንኮች የውጭ ብድር ማግኘት የሚችሉበት አሠራር እስካሁን ባለመኖሩ ይህንን በቀላሉ ሊላመዱት የሚችሉበት ልምድ አላካበቱም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ይህም ሊታሰበብ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ የባንኩ ገዥ ይናገር (ዶ/ር) ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ አላቸው፡፡ ይህንኑ በመመርያው ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል፡፡

እንደ ይናገር ማብራሪያ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ብድር ለማግኘት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ አለ፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ወይም አበዳሪ ተቋማት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ኩባንያዎች ከማበደር ይልቅ ለባንኮች ማበደሩን ይመርጣሉ በማለት ሞግተዋል፡፡

‹‹የእኛን አገር ኩባንያዎች አቅም የሚያሳይና ደረጃ የሚሰጥ አሠራር ስለሌለና የሒሳብ አያያዛቸውም በዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝና ደረጃ መሠረት ሪፖርት ስለማይቀርብበት የውጭ አበዳሪዎች ለኢትዮጵያ ኩባንያዎች ብድር ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ የተሻለው አማራጭ ከውጭ ብድር ለማግኘትና የሚጠየቀውን መሥፈርት ሊያሟሉ የሚችሉት ባንኮች በመሆናቸው ብድሩ በባንኮች በኩል ይቀርባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የእኛ ባንኮች ምቹ ስለሆኑ ብድሩን በቀላሉ ለማግኘት ይችላሉ፤›› በማለት የባንኮችን ለውጭ ብድር የተሻለ ተመራጭ መሆን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም በመመርያ አተገባበር ዙሪያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለማስቀረት ሥጋቶችንም ለመቀነስ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደሩንና ከሌሎች የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ የሚታዩ ለውጦችን መተንተንና መተንበይ መቻል ከገዥው ባንክ የሚጠበቁ ሥራዎች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ቁጥጥር ማጠንከርና በበቂ ባለሙያዎች መደራጀት ከወዲሁ ባንኩ ዝግጅት ማድረግን ይጠይቃሉ ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ግን ከዚህ መመርያ ጋር በተያያዘ ሊያጋጥም እንደሚችል የሚታሰበውን ችግር አስቀድሞ በመለየትና በመመርያው በማካተት ሥጋት ሊቀንሱ እንደሚችሉ የታመነባቸው አሠራሮች ተቀምጠዋል ይላሉ፡፡ ሥጋትን ይቀንሳሉ የተባሉ አንቀፆች እንደተካተቱበት የተገለጸው መመርያ የሚተገበርበትንና ቁጥጥር የሚደረግበትን ሥርዓት ብሔራዊ ባንክ እንደሚዘረጋ፣ በየጊዜውም ክትትል የሚያደርግበት አሠራር እንደሚኖረው ይናገር (ዶ/ር) ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች