Tuesday, July 23, 2024

ያልጠራው የብልፅግና ውህድ አደረጃጀት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ካከናወኗቸው አበይት ተግባራት መካከል፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግ) ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲነት የመለወጡ ውሳኔ ተጠቃሽ ነው፡፡

ኢሕአዴግን አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ የማድረግ እንቅስቃሴ በበርካታ የግንባሩ ጉባዔዎች ላይ ሲነሳ ሲጣል የሰነበተ ጉዳይ የነበረ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን መምጣት ለዚህ ሲነሳ ሲጣል ለሰነበተ አጀንዳ መቋጫ አበጅቶለታል፡፡

ግንባሩን ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲነት የመለወጥ ሒደት በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረ አጀንዳ ቢሆንም፣ ‹‹ጊዜው ገና ነው›› በሚል ጥቅል ምክንያት ውህደቱ ሳይሳካ ለረዥም ዓመታት ሲንከባለል መጥቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ከሆኑ በኋላ በተረደረገው የሐዋሳው ጉባዔ ላይም ይህ ጉዳይ ተነስቶ ጉዳዩን በሳይንሳዊ መንገድ የሚያጠና ኮሚቴ እንዲቋቋምና ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብ ተወስኖ እንደነበረ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሀል ሲዋልል የሰነበተው ኢሕአዴግን የማዋሃድ ሒደት መቋጫ ያገኘው ባለፈው ዓመት የብልፅግና ፓርቲ ሲመሠረት ነበር፡፡ በወቅቱ የግንባሩ ሦስት ፓርቲዎች ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በስተቀር፣ ራሳቸውን አክስመው የአዲሱ ውህድ ፓርቲ መመሥረትን ዕውን እንዲሆን በመወሰን የአዲሱን አገራዊ ፓርቲ ምሥረታ ሒደት ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግረውታል፡፡

ከእነዚህ ሦስት የቀድሞው ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ‹‹አጋር›› ተብለው የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል፣ የሐረሪ፣ የአፋር እንዲሁም የሶማሌ ክልልን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ፓርቲዎችም ራሳቸውን አክስመው አዲሱ አገራዊ ፓርቲ ብልፅግናን ተቀላቅለዋል፡፡

የግንባሩ ‹‹አጋር›› ሆነው የዘለቁት ፓርቲዎች በውሳኔ ሰጪነት ድርሻ ያልነበራቸው መሆኑን በመጥቀስ፣ የብልፅግና አካሄድ ሁሉንም እኩል በመመልከት የአገሪቱን የፓርቲ ፖለቲካ ባህል እንደ አዲስ ይቃኘዋል በሚል በርካቶች ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡ በሌላ በኩል እንዲሁ ደግሞ ፓርቲው አሃዳዊ ሥርዓትን ሊያሰፍን ነው በሚል በተቃውሞ የሚከሱትም ነበሩ፡፡

የውህዱን ፓርቲ ምሥረታ አክርረው ከተቃወሙ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ የኢሕአዴግ መሥራች የሆነው ሕወሓት አንዱ ሲሆን፣ ‹‹አሃዳዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረግ ጥረት ነው›› ከሚለው ክሱ በተጨማሪ፣ ኢሕአዴግን ወደ ውህድ ፓርቲነት የመቀየሪያ ጊዜው ገና ነው የሚል መከራከሪያም ሲያቀርብ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ሕወሓት ብልፅግና እንደ ፓርቲ ሳይሆን እንደ አንድ የተለየ ዓላማ እንዳለው ‹‹ቡድን›› እንደሚቆጥረው በተደጋጋሚ ከሚያወጣቸው መግለጫዎች መታዘብ ይቻላል፡፡

ከሕወሓትና ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በተጨማሪ የብልፅግና ፓርቲ መመሥረት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ የቅርብ ጓዶችም ቢሆን ትችት ተሰንዝሮበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በተለይ ባለፈው ሳምንት ከመከላከያ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው የተነሱት የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ ስለ ብልፅግና ፓርቲ ለቪኦኤ ኦሮሚኛ አገልግሎት የሰጡት አስተያየት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆድና ጀርባ እንዳረጋቸው ይገልጻሉ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የተመሠረተ ሰሞን በርካቶች ሲያነሱት የነበረው የድርጅቱ አወቃቀርና ቁመና ጉዳይ፣ በዚህ ሰሞንም እንደ አዲስ የመወያያ አጀንዳ ሆኗል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ሲመሠረት በመሥራችነት ፓርቲውን የተቀላቀሉት ድርጅቶች በሙሉ የቀደመ ማንነታቸውን በማክሰም የነበረ ሲሆን፣ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ አልያም ደግሞ የአፋር ወይም የሶማሌ በሚል አደረጃጀት ሳይሆን አንድ ወጥ የሆነ አገራዊ ፓርቲ መመሥረታቸውን ይፋ አድርገው ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም አገሪቱ ውስጥ ከነበረው የብሔር ማንነትን ከተከተለ የፓርቲ ፖለቲካ አወቃቀር በተለየ መልኩ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ፓርቲውን መቀላቀል ይቻላል ማለቱ፣ ለአገሪቱ አዲስ የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ሊያስተዋውቅ ይችላል በሚል በርካቶች የሚጠብቁት ፓርቲ ነበር፡፡

ሆኖም ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተከሰቱት ክስተቶች የፓርቲው ድርጅታዊ ቁመናና አወቃቀር ላይ ከመጀመርያው ጀምሮ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ደግመው እንዲያንሰራሩ በር ከፍቷል፡፡

የፓርቲውን አደረጃጀትና አወቃቀር በተመለከተ ጥያቄዎቹ ዳግም ሊነሱ የቻሉት ደግሞ፣ በተለይ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ በሦስት አባላቱ ላይ የወሰደው የማገድ ዕርምጃ ነው፡፡

እዚህ ላይ የኦሮሚያ ብልፅግና ወይም የአንድ ክልል ብልፅግና የሚባል ከሆነ ወጥና አገራዊ ፓርቲነቱ ከምን ላይ ነው? በማለት የሚጠይቁ አሉ፡፡ ለዚህም መከራከሪያነት የሚያነሱት ነጥብ ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የፓርቲው አባል በሚፈጽመው ጥፋት ልክ የሚወሰድበትን የዕርምጃ እርከኖች በማንሳት ነው፡፡

ከዚህ አንፃር አንድ አባል ከመታገዱ በፊት ተግሳፅ፣ የቃል ማስጠንቀቂያ፣ እንዲሁም የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል የሚለውን አንቀጽ በመጥቀስ ሲሆን፣ ይህም ሊሆን ቢገባውም አቶ ለማ ላይ የተወሰደው የእግድ ዕርምጃ እነዚህን የፓርቲውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት አለመሟላቱንም ይጠይቃሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ለማ ላይ ዕርምጃ መውሰድ ያለበት የኦሮሚያ ብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ነው ወይስ አጠቃላይ የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ? በሚል የሚጠይቁ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ የራስ የሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴ ካለው እንዲሁም ሌሎቹም እንዲሁ የሚኖራቸው ከሆነ ከቀደመው የኢሕአዴግ አደረጃጀት የሚለየው በምንድነው? በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ብልፅግና የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ እንደሚኖረው የተገለጸውን በማስታወስ ነው፡፡  

ከዚህ አንፃር የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተጠቀሰውን የፓርቲውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ሥልጣን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር ነው፡፡ በዚህም መሠረት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለፓርቲው ጉባዔ መሆኑን በመጥቀስና የፓርቲው ጉባዔ ደግሞ የፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አካል መሆኑን በማውሳት፣ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ብልፅግና የተወሰደው ዕርምጃ ከፓርቲው አደረጃጀት ጋር እንደሚቃረን ይጠቅሳሉ፡፡ ብልፅግና አጋር የሚሰኙትን ፓርቲዎች ከማካተቱ በስተቀር፣ ከኢሕአዴግ አደረጃጀት የተለየ እንዳልሆነና አዲስ ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ነው በማለት እየተቹት ይገኛሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በባህር ዳር መከናወኑን በማንሳት፣ የፓርቲው አደረጃጀት አሁንም ከዚህ ቀደም የነበረውን የክልል ፓርቲዎችን አደረጃጀት የተከተለ ነው በማለት የተለየ ነገር አለመኖሩን በማውሳት ግራ መጋባታቸውን የሚገልጹ አልጠፉም፡፡

ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑትና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ መምህር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እንዲህ ያሉ ግራ መጋባቶች አያስገርማቸውም፡፡

ግራ መጋባቶቹ ለምን እንደማያስገርማቸው ሲያብራሩ ደግሞ፣ ከመጀመርያው አንስቶ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ስለአዲሱ ፓርቲ አመሠራረትና አወቃቀር ጠለቅና ዘለግ ያለ ውይይት በተለያዩ ደረጃ አለማድረጋቸውን ነው፡፡ ‹‹ምንም እንኳን ኢሕአዴግን ማዋሃድና አንድ ወጥ ፓርቲ የመመሥረት ጉዳይ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ሲነሳ የቆየ ቢሆንም፣ በተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ ጉዳዩ ዕልባት ሳይበጅለት ሰንብቷል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መምጣት በኋላ ያለው የተለየ ነገር እሳቸው ጉዳዩን በፍጥነት መቋጨታቸው ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የፓርቲው ካድሬዎች ጉዳዩን ለመረዳት፣ ለመተንተንና ለማብራራት በቂ ጊዜ አልነበራቸውም፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግን ‹‹ብልፅግና ፓርቲ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትንና የፓርቲ አደረጃጀትን ከቀድሞው ኢሕአዴግ መውረሱን ወደ ጎን ልናደርገው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፤›› በማለት አክለው፣ ‹‹ይህም ደግሞ እየተካሄደ ካለው አጠቃላይ ተሃድሶ ጋር ራሱን እንዲያሳልፍ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወቅታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ ጡዘትም የብልፅግና ፓርቲን መሠረታዊያን ለማስረፅ ፈታኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ምሁሩ ገለጻ ከሆነ፣ ስለ ብፅግና ፓርቲ መሠረታዊያን በሰፊው ለመነጋገርም ሆነ ሐሳቡን በአመራሩ አማካይነት ሕዝብ ውስጥ ለማስረጽ ቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫን ተከትሎ የሚኖረው የፖለቲካ ምኅዳር ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አንፃር በርካታ የዘርፉ ምሁራንና ተዋንያን እንደሚገልጹት፣ ብልፅግና ፓርቲ ቀጣዩን ጠቅላላ ምርጫ ካሸነፈ ሐሳቡን ለማስረፅና የተዳከመውን የክልልና የፌዴራል መንግሥት ግንኙነትንን ለማረቅ ዓይነተኛ ሚና ከመጫወቱም በላይ፣ በአገሪቱ የፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ላይ አወንታዊ አሻራውን እንደሚያሳርፍ ይጠቅሳሉ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ መመሥረትን ተከትሎ ሲነሱ የነበሩ የተለያዩ ሙገሳዎችም ሆነ ወቀሳዎች መቋጫ የሚያገኙት የሚመስለው፣ በኮቪድ 19 ሳቢያ የተራዘመው ጠቅላላ ምርጫ ተከናውኖ አሸናፊው ከለየለት በኋላ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች የሚገልጹት ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት መጪው ምርጫ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ሥልጣን ለማምጣት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በአገሪቱ አዲስ የፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋትና የብልፅግናን መሠረታዊ ባህሪያት ለመረዳት የሚያገለግል ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚሆን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ አሁን ላይ የሚታዩትን የአደረጃጀት የአወቃቀር ትችቶች ቀረፎ መሠረታዊ ባህሪያቱን ያሳያል ወይስ አሁን ባለበት ሁኔታ ይቀጥላል? እንዲሁም ደግሞ በአገሪቱ ታሪክ አዲስ የሆነ የፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ይዘረጋል የሚሉት ጥያቄዎች ለመመለስ መጪውን ምርጫ ወሳኝ ይሆናል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -