Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለመገናኛ ብዙኃን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለመስጠትና ፍትሐዊ የባለቤትነት ስብጥርን ለመፍጠር የተለመ ፖሊሲ ፀደቀ

ለመገናኛ ብዙኃን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለመስጠትና ፍትሐዊ የባለቤትነት ስብጥርን ለመፍጠር የተለመ ፖሊሲ ፀደቀ

ቀን:

የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሕግ እንዲወጣም ፖሊሲው ወስኗል

ለመገናኛ ብዙኃን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለመስጠት ተደራሽነትና ይዘታቸውን ለማስፋት እንዲሁም በዘርፉ ፍትሐዊ የባለቤትነት ስብጥርን ለማረጋገጥ የተለመ ፖሊሲ ፀደቀ። 

ፖሊሲው ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ታሪክ ውስጥ መንግሥት ያወጣው የመጀመርያው የፖሊሲ ማዕቀፍ ነው። 

ሪፖርተር የፖሊሲ ሰነዱን ማግኘት የቻለ ሲሆን፣ በሰነዱ ከተካተቱት አንኳር ነጥቦች መንግሥት የመናገኛ ብዙኃንን ለማጎልበት የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለመስጠት በግልጽና በዝርዝር የወሰነበት የመጀመርያው የፖሊሲ ማዕቀፍ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። 

‹‹በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሚመራበት ራሱን የቻለ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ባለመኖሩ፣ ዘርፉን በብቃትና በጥራት በማስፋፋት ሁሉንም የኢትዮጵያ ዜጎች የመረጃ ተደራሽ ለማድረግ አልተቻለም፤›› የሚለው የፖሊሲ ሰነዱን አስፈላጊነት የሚገልጸው የመግቢያ ሀተታ፣ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን የሚመሩበትና የሚደገፉበት የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ማዘጋጀት ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ መቀረፁን ያስረዳል። 

ለሕዝብ (ለመንግሥት) መገናኛ ብዙኃን ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር ለንግድና ለማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን የሚደረግ ቀጥተኛ የሆነ የመንግሥት ድጋፍ እስከ ዛሬ አለመኖሩን የፖሊሲ ሰነዱ በግልጽ አስቀምጧል። 

መገናኛ ብዙኃን የዜጎችን አስተሳሰብ በማነጽ ዜጎች በአገር ግንባታ እንዲሳተፉ የሚያደርጉ በመሆናቸው፣ ከማንኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ በተሻለ ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው በመንግሥት መታመኑን በመግለጽ ታሳቢ የተደረጉትን ድጋፍና ማበረታቻዎች ይዘረዝራል። 

የመገናኛ ብዙኃኑን ለመደገፍ ሊወሰዱ ይገባል ተብለው ከተቀመጡት ማበረታቻ ድጋፎች መካከልም  በመገናኛ ብዙኃን መሣሪያዎች ላይ የተጣለውን ከፍተኛ የገቢ ቀረጥ መቀነስ፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ፣ መሥሪያ ቦታ፣ ብድርና የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ዕድል ማመቻቸት ይገኙበታል። 

የመንግሥት ተቋማት ማስታወቂያና ስፖንሰርሽፕ ገቢ በውድድር እንዲከፋፈል ማድረግ ከኢንተርኔት ጋር የተሳሰረ ያልተማከለ ለሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ውጤቶች በሁሉም ቦታ ተደራሽ የሆነ ብሔራዊ የማተሚያ ቤት ማደራጀት፣ የማተሚያ ቤት ወጪንና የመሸጫ ዋጋን መደጎም፣ የኅትመት ግብዓት ወረቀት፣ መሣሪያዎች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ሌሎቹ ማበረታቻዎች ናቸው። 

በቂ ማተሚያ ቤት መቋቋሙንና የግሉ ዘርፍ መሳተፉን ማረጋገጥ፣ አሳታሚዎችም በግልም ይሁን በጋራ የራሳቸው የማተሚያና የማሠራጫ አውታር እንዲኖራቸው መደገፍ፣ ጋዜጣና መጽሔት በፖስታ ቤትና በመሰል ቴክኖሎጂ ታግዞ ማሠራጨት እንዲችሉ መደገፍ እንደሚገባ በፖሊሲ ሰነዱ ተዘርዝሯል። 

በተጨማሪም መገናኛ ብዙኃንን ለማስፋፋት፣ ለመደገፍና ቀጣይነታቸውን ለማረጋገጥ በፋይናንስና በቴክኒክ የሚደገፉበት አሠራር መዘርጋት፣ ለዚህም የድጋፍ ፈንድ በማቋቋም ወይም በሬጉላቶሪ አካሉ በኩል የድጋፍ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ወስኗል። 

አሁን ያለው የንግድ መገናኛ ብዙኃን ባለቤትነትና ስብጥር ፍትሐዊ አለመሆኑን የሚገልጸው የፖሊሲ ሰነዱ፣ ይህንን ጉድለት ለመቅረፍም የንግድ መገናኛ ብዙኃን የባለቤትነት ስብጥር ፍትሐዊና ብዝኃነትን የተላበሰ ማድረግ ይገባል ሲል ወስኗል። 

ብዝኃነትን የተላበሰ ፍትሐዊ የባለቤትነት ስብጥር ያለው የሚዲያ ምኅዳር እንዲፈጠርም ግለሰብን ጨምሮ የንግድ ተቋማት የንግድ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ባለቤት እንዲሆኑ መፍቀድ እንዳለበት ይገልጻል። 

ወደዚህ ለመምጣትም ግልጽ የሆነ ዝርዝር ሕግ በማውጣት የመገናኛ ብዙኃን ባለቤትነት ስብጥርን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን፣ የመገናኛ ብዙኃን የንብረት ቁጥጥር ሕግ አገራዊ ጥቅምን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባቱን፣ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ ሰዎች መያዝን የሚያበረታታ መሆኑን፣ መገናኛ ብዙኃንን የመረጃና የሐሳብ ስብጥርንና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በማበረታታት በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ማስቻልና ማረጋገጥ እንደሚገባም በፖሊሲ ሰነዱ ወስኗል። 

ከዚህ በተጨማሪም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመገናኛ ብዙኃን እንዲሰማሩ እንዲደረግ የወሰነ ቢሆንም፣ ከፍተኛው የባለቤትነት የአክሲዮን ድርሻ ግን በኢትዮጵያውያን ይዞታና ቁጥጥር ሥር እንዲውል አቅጣጫ አስቀምጧል።

ይሁን እንጂ መጠኑ በፖሊሲ ሰነዱ ላይ አልተቀመጠም።  በማኅበራዊ ሚዲያ የሚታየውን የተዛባ የመረጃ ሥርጭት ለመከላከል መንግሥት ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ አገሮች ተሞክሮ በመውሰድና ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማጣጣም አስቻይ የሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሕግ ማውጣት እንደሚገባ አስቀምጧል። 

ይህንንም መሠረት በማድረግ በመደበኛው መገናኛ ብዙኃን ላይ እንደሚደረገው ቁጥጥር ሁሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ባለቤቶች ወይም የሚዲያ ይዘት አሠራጮች ማንነታቸውን በይፋ እንዲገልጹ በሕግ በማስገደድ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ በፖሊሲው ተወስኗል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...