ከድስሳ ዓመት በፊት በሮም ኦሊምፒክ በማራቶን የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳሊያ ላጠለቀው ፋና ወጊው አበበ ቢቂላ የዕውቅና ፕሮግራም እያዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ ዝግጅቱ ከሜልቦርን እስከ ሪዮ ዲጂኔሮ ኦሊምፒክ የተሳተፉና ውጤታማ አትሌቶችና ሙያተኞች የሚታወሱበት እንደሚሆንም ገልጿል፡፡
በማራቶን ሁለት ተከታታይ ኦሊምፒያዶች ቀዳሚዎቹን የወርቅ ሜዳሊዎች ለአገሩና ለራሱ በማስመዝገብ ለጥቁር ሕዝቦች በተለይም ለአፍሪካውያውን የድል ተምሳሌት ተደርጎ በታሪክ የሚዘከረው አበበ ቢቂላ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስና ለዘርፉ ሙያተኞች የሠራው ገድል የትውልድ ኩራት መሆኑ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ ዓለም አቀፉን ወረርሽኝ ከግምት በማስገባት እስከ ጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ለሮምና ቶኪዮ ኦሊምፒክ ባለድሉን አበበ ቢቂላን በልዩ ሁኔታ ለመዘከር ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡
ዝግጅቱን አስመልክቶ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሜልቦርን እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ የነበራቸው አትሌቶችና (በሕይወት የሌሉ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት) በሕይወት የሚገኙ አትሌቶች ይዘከራሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በሻምበል አበበ ቢቂላ ስም የተዘጋጀው ነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) ለሴት አትሌቶችና አሠልጣኞች ይፋ ይደረጋል፡፡