ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ሱዳን መዲና ካርቱም በመገኘት፣ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ በመከሩበት ወቅት የተናገሩት፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያሰመሩበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚነሱ ማናቸውም ዓይነት ጉዳዮች በሁለትዮሽ ውይይት እንደሚፈቱም ተናግረዋል። ኢትዮጵያና ሱዳን ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት እንዳላቸው የጠቀሱት ግንኙነቱ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል እንደሚሠሩ ያወሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ሱዳን እንደምታከብር ጠቁመው፣ የህዳሴ ግድብን በሚመለከት የሚነሱ ጉዳዮች በድርድርና ውይይት ብቻ መፈታት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።