Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምማሊን በሲቪል መንግሥት የማስተዳደር ፈተና

ማሊን በሲቪል መንግሥት የማስተዳደር ፈተና

ቀን:

ባለፈው ሳምንት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገደችውን ማሊ ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የተጀመረው ድርድር ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡ የናይጄርያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን የሚመሩት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ልዑክ ቡድን፣ ከመፈንቅለ መንግሥት አድራጊው የማሊ ጦር አዛዦች ጋር የሲቪል መንግሥት ወደ ሚመጣበት፣ ሕገ መንግሥታዊ የሽግግር መንግሥት ስለሚመሠረትበት ቢመክሩም፣ ጦሩ የሦስት ዓመታት ጊዜ እንደሚያስፈልግ አሳውቋል፡፡

የማሊ ጦሩ ቃል አቀባይም ለማግባባት የተገኙትን የኢኮዋስ ልዑካን አመስግነው፣ የሽግግር መንግሥትን አወቃቀር የሚወስኑት ማሊያውያን ናቸው ብለዋል፡፡ ምርጫ ለማካሄድና ማሊን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማምጣትም የጊዜ ገደብ አለመቀመጡን፣ ይህ አመቺ በሆነ ጊዜ ሊከናወን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች የማሊ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ቡበከር ኬይታ ወደ ሥልጣን መመለስ አለባቸው የሚል ሐሳብ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ መሆን እንደማይችል ወታደራዊ ክፍሉ አሳውቋል፡፡ ሚስተር ኬይታም ወደ ሥልጣን መለለስ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡

ማሊን በሲቪል መንግሥት የማስተዳደር ፈተና

 

ማሊን ጨምሮ 15 አገሮችን በአባልነት የያዘው ኢኮዋስ መሪዎች፣ በማሊ ሲቪል መንግሥት ሥልጣን በሚይዝበት ዙሪያ ባደረጉት ድርድር ማሳመን እንዳልቻሉ  ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የማሊ መከላከያ ቃል አቀባይ ኮሎኔል እስማኤል ዋጉን ጠቅሶ ሮይተርስ እንዳሰፈረው፣ የማሊ የውስጥ ጉዳይ በሕዝቦቿ የሚወሰን ይሆናል፡፡

ለሁለት ቀናት የተደረገውን ድርድር የመሩት ሚስተር ጆናታን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ቢደርሱም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አለመግባባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሕግና ሥርዓት በጠበቀ መልኩ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም በኢኮዋስ አባላት የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ባያገኘም በመፈንቅለ መንግሥት ከፕሬዚዳንት መንበራቸው የተነሱት ሚስተር ኬይታ፣  ወደ ውጭ እንዲወጡ የሚል ሕሳብ ተነስቷል የሚል ጭምጭምታ አለ ተብሏል፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ከነ ወንድ ልጃቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦውቦው ሲሴና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በእስር ላይ ናቸው፡፡

ለሁለት ወራት ያህል በተቃዋሚ መሪዎች ጥምረትና በሲቪል ሶሳይቲ ወትዋቾች በፕሬዚዳንት ኬይቲ ላይ ሲደረግ የከረመው ተቃውሞ ፈንድቶ፣ ሰውየው በመፈንቅለ መንግሥት ሲነሱ አገሬው ደስታውን ለመግለጽ ወደ ጎዳና ወጥቷል፡፡ ለወታደራዊ ክፍሉ ይሁንታ ሲቸርም ተስተውሏል፡፡

የኢኮዋስ ልዑካን ቡድን አባላት የ75 ዓመቱን ኬይታ በማሊ መዲና ባማኮ በሚገኘው የመከላከያ ማረፊያ ቤት ሄደው መጎብኘታቸውም ተነግሯል፡፡

ሚስተር ጆናታን እንደሚሉት፣ ኬይታ ማሊ በአስቸኳይ ወደ ቀደመ የሲቪል አስተዳደር እንድትመለስ ይፈልጋሉ፡፡ የኢኮዋስ ዓላማም ይኼው ነው፡፡

ማሊ እ.ኤ.አ. ከ2012 ወዲህ በጎሳ ሸማቂዎች ምክንያት ሰላሟን አጥታ ከርማለች፡፡ ሸማቂዎችና ሌሎች ታጣቂዎች ጥምረት ፈጥረው የአገሪቱን ሁለት ሦስተኛ ክፍል በቆጣራቸውም፣ የማሊ የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፈረንሣይ ጣልቃ እንድትገባና ሸማቂዎች እንዲያፈገፍጉ ሆኗል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትና የኬይታ መንግሥት በሰሜን ያለውን ግጭት ወደ ሰላም ለመለወጥ የሚያደርጉት ጥረት በአገሪቱ ጥቃት እንዲባባስ አድርጓል፡፡ በዚህም እ.ኤ.አ. በ2016 እና በ2020 መካከል በማሊ፣ በቡርኪናፋሶና በኒጀር 4,000 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ተሰደዋል፣ ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል ተብሏል፡፡

ማሊን በሲቪል መንግሥት የማስተዳደር ፈተና

 

ሙስና፣ ሥር የሰደደ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የሰላም እጦት ከአልቃይዳና ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች መኖር ማሊን አንኮታኩቷት ከርሟል፡፡

ይህ በፕሬዚዳንት ኬይታ የመምራት ዘመን ተባብሷል፣ የሚባለው ወታደራዊ ክፍሉ፣ ሥርዓት አልበኝነትን ለማስተካከል ወታደራዊ መንግሥት ለሦስት ዓመታት መግዛት አለበት የሚል  አቋሙን አሳውቋል፡፡ እዚህ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በቁጥጥር ሥር የሚገኙትን ሚስተር ኬይታ እንደሚለቅ ማስታወቁንም ዶቹ ቪሌ ዘግቧል፡፡

በማሊ ለዓመታት የዘለቀ ግጭት እንዲሁም ላለፉት ሁለት ወራት ተቃውሞ ተደርጎ ፕሬዚዳንቱ በመፈንቅለ መንግሥት ሲነሱ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች ደግሞ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡

አገሬው እሰይ ብሎ ደስታውን ለመግለጽ ጎዳና ሲወጣ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)  ግን ድርጊቱን አውግዟል፡፡ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት የታሰሩት ይፈቱ ዘንድ ጥሪ ቢያቀርብም ሰሚ አላገኘም፡፡

የኢኮዋስ አባል አገሮች፣ ፈረንሣይና የአፍሪካ ኅብረትም ድርጊቱን ካወገዙት የሚገኙበት ሲሆን፣ አባል አገሮቹ ድንበር መዝጋትን ጨምሮ በማሊ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...