እነሆ ከመርካቶ ወደ ፈረንሣይ ሌጋሲዮን ልንጓዝ ነው። ያደረሰን መንገድ ዳግም ሊመልሰን፣ የመለሰን ደግሞ እንደገና ሊወስደን ታክሲ ጥበቃ ተሠልፈናል። የሠልፉ አድማቂ ሆነው እንዲህ ቆመው ሲያዩት ተንቀሳቃሹ ነገር ሁሉ ያስቀናል። መጓጓዣ ማጣቱ ቀርቶብን ጉልበት እያነሰን የተቸገርን በዝተናል። ሠልፉ ውስጥ የሚደመጠው ዝብርቅርቅ ጉርምርምታ አንዱን ሳይጠግቡ አንደኛውን ለመስማት ያጓጓል። ‹‹እህ! ቆመን ቀረን አይደለም?›› ብሎ ሳይጨርስ አንዱ ሠልፈኛ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ኧረ እናንተ ዘንድሮስ ከዓለም የመጨረሻ ሆነን ቆመን መቅረታችን ብርቅ እንዳይሆን? ቆመን በመቅረታችን መስሎኝ ዓለም የሚያስታውሰን?›› ይላል። የነገር ቅብብሎሹ ይቀጥላል። ሐሳብ ከድካም ጋር ተባብሮም በነገር መተጋተጋችን የሚለዝብ አይመስልም። ‹‹በየአቅጣጫው ድምፅ አልባ ተቃውሞ በማቅረብ አገራችንን የሚደርስባት ይኖር ይሆን?›› ስትል መሬት መሬት የምታይ ወጣት፣ ‹‹እኔ የምፈራው በዚህ አያያዛችን አንድ ቀን በሕገወጥ ሠልፈኝነት ታፍሰን ጉድ እንዳንሆን ነው፤›› ይላል። የቸገረው ማለት ይህ ነው!
‹‹እሱም አለ ለካ?›› ይላል ነገር አዳናቂው። እውነት የመሰለው ግራ ግብት ሲለው ይስተዋላል። ቀልዱ ቀልድ አይመስል፣ ሀቁ ሀቅ አይመስል እንዲያው ብቻ ውጥንቅጣችን ወጥቷል። ጠግቦ አዳሪው ሜዳ አዳሪውን አያስበውም። አገልጋዩ በቅንነት ከማገልገል ይልቅ አመፅና ጩኸት ናፋቂ ይመስላል። ጎዳናውን የሞላው ከአንገት በላይ ፍቅር፣ ተግባራዊ የማይሆን መፈክርና እያደር ጫናው የሚጨምረው ኑሮ የራስ ምታት ነው። ኮሮና መጣና ገታው እንጂ ከሆስፒታል እስከ እምነት ተቋማት ከአንገት በላይ ሕክምናና የፈውስ ፕሮግራም ተጨናንቀው ነበር። ስለአገር ማሰብ ሲገባን የቤት ኪራይ ተደቅኖ ስለጓዳችን ስናስብ ነገሩ ተለጥጦ የሁላችንም ጉዳይ ይሆንና ናላችን ሲዞር ይውላል። በወዲያ በኩል ሊሮጡ ሲያስቡ መንገዱ ቀድሞ ይናዳል። በወዲህ ሊያመልጡ ሲቃብዙ ነገ የሚበራው የብርሃን ጭላንጭል ልብን እየማለለ ያስታግሳል። መንገዱ ይወስዳል መንገዱ ያመጣል። መመላለስ አታካች በሆነበት ጊዜ እያሰበ ብቻ በድካም የሚያረጀው የትና የት ደርሷል። እንዲያው ምን ይሻላል? የመነጠል ዘመን ላይ ሆነን ስናስበው ግን ያሳቅቃል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ደመኝነት ይታክታል!
ቢዘገይም የማይቀረው ታክሲ መጣና መሳፈር ጀመርን። የዛሉ እግሮች ዕፎይ ብለው ለመቀመጥ ይቻኮላሉ። ‹‹እግርስ ሲደክመው ታጥፎ ይቀመጣል፣ ሐሳብ እንዴት ይሆን?›› ይላል ቀይ ረጅም ጎልማሳ። ታክሲውን በኮሮና ሕግ መሠረት እንደ ሞላን ጎስቆል ያለ ጎልማሳ ሲሮጥ መጣ። የታክሲውን በር እንቅ አድርጎ ሲይዝ በተለመደው ዓይነት የአለማመን ሥልት፣ ‘እርቦኛል ዳቦ ግዙ!’ ሊለን መስሎን ችላ አልነው። እንዲያውም አንዳንዱ ለነገር መቸኮል የሚወድ፣ ‹‹የራሳችን ዳቦ እያረረ ዳቦ የሚጠይቀን መብዛቱ ያስፈራል፤›› ሲል ይደመጣል። ሳናጣራ ማውራትና ማቀባበል ዋናው ሥራችን አይደል!
ሆኖም እንዳሰብነው ሳይሆን ጎልማሳው የጠየቀው የቶምቦላ ሎተሪ እንድንቆርጥለት ነበር። ‹‹አለ ቶምቦላ የአዲስ ዓመት ቶምቦላ እንዳያመልጣችሁ፣ ወሳኝ ወሳኝ ዕጣዎችን አካቷል። ዕድል አያምልጣችሁ ግዙ…›› እያለ ይለማመጣል። በእጁ የያዘው ባለ ቁጥር ቲኬት ነው። በዚህ መሀል አንዱ፣ ‹‹ዕጣውን አውጪው ማን ነው?›› ብሎ ሲጠይቀው ትካዜ ገባው። ‹‹የሰው ዕጣ አውጪ ማን ይሆናል? እሱ ፈጣሪ እንጂ! እኔና እናንተን እንዲህ ያደረገን ማን ነው? ፈርዶብን እርስ በርስ እኛ እንባባላለን እንጂ በመሀላችን ያለውን ክፍፍል ያመጣው ፈጣሪ ነው። ሲሻኝ ደሃ ሲሻኝ ባለፀጋ አድርጌ እፈጥርሃለሁ ምን ታመጣለህ አይደል እንዴ ነገሩ። ዕጣውንማ የሚያወጣው ፈጣሪ ነው!›› ብሎ ሲመልስልን አስደነገጠን። ጉድ እኮ ነው!
ለምን እንደሆን እንጃ ፍልስፍናውም ሃይማኖቱም በእንዲህ ዓይነት ሰዎች አፍ ሲወራ ቆንጠጥ ያደርጋል። ነገሩ በቴክኒክ የታገዘ የራሱ ሥልት መሆኑ ሲገባን ደግሞ ግራ መጋባታችን በአግራሞትና በፈገግታ ተተካ። ገሚሱ፣ ‹አይ ፈጠራ! አይ ጭንቅላት! ምናለበት በደረቁ የሚላጩን ቅዠታም ፖለቲከኛ ተብዬዎች ከዚህና ከመሰሎቹ ቢማሩ?› እየተባባለ ይሳሳቃል። አንድ ወጣት፣ ‹‹ታዲያ ዕጣው ምን ምን እንደሆነ ንገረና?›› አለው። ጎልማሳው ጎዳና ተዳዳሪ፣ ‹‹አንደኛ ዕጣ ሰላም፣ ሁለተኛ ዕጣ ኔትወርክ፣ ሦስተኛ ዕጣ ውኃ፣ አራተኛ ዕጣ ትራንስፖርት፣ አምስተኛ ዕጣ ኤሌክትሪክ . . .›› እያለ ሲቀጥል ተሳፋሪዎች ሳይወዱ በግድ ሳቅ በሳቅ ሆኑ። መፋዘዙ ላይ ፈገግታ ጭሮ ሕይወት ስለዘራበት ብቻ ከቶምቦላው ቲኬት ዋጋ ላይ ጨመርመር አድርገን ሰጥተን ሸኘነው። ዕጣዎቹ ሕልም እንደሆኑ ብናውቅም የምር አልተመኘናቸውም ማለት ግን ይከብድ ነበር፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!
ታክሲያችን መንቀሳቀስ ከመጀመሩ ወያላው ታሪፍ በቅርቡ እንደሚጨምር ለመንገር፣ ስለነዳጅ ዋጋ መጨመር አይቀሬ መሆን ማውራት ጀመረ። ከሾፌሩ ጀርባ ዘናጭ ቦርሳ ያነገበች ዘንካታ፣ ‹‹ዘንድሮ እኮ ዘወርዋራው ነው የገደለን ሌላ ምንም አይደለም…›› ስትል ትደመጣለች። ‹‹ንክኪው በዛ፣ ምን ይደረግ ብለሽ ነው? በተለይ ይኼ ነዳጅ? በቃ ‘ጆከር’ በይው። የማያካልለው፣ የማይገባበት፣ የማይመለከተው ነገር ምን አለ? ‘ቤት ኪራይ ተወደደ!’ ነዳጅ! ‘ወጡ ጨው አነሰው!’ ነዳጅ! ‘ፍቺው በዛ!’ ነዳጅ! በቃ እኮ ከኮሮና የባሰ ‘ቫይረስ’ ሆነ እኮ? ተቀጣጣዩ ፈሳሽ ነገር አይመስልሽም ኑሮን የሚያንረው…›› ሲላት ከኋላዋ የተቀመጠ ጮሌ አፏን ከፍታ ትሰማዋለች።‹‹በነዳጅ አሳቦ. . . እንበል ይሆን?! እያየህልኝ ነው ‘ለቫላንታይንስ ዴይ’ ሲያመቻች?› የሚሉት ኋላ መቀመጫ የተቀመጡ ሁለት ወጣቶች ናቸው።
‹‹ግን እንዲያው የለም የሚል ቃል ራሱ አልሰለቻችሁም?›› መሀል መቀመጫ የተቀመጠች ወይዘሮ ስትናገር ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹እኔን የሚገርመኝ ደግሞ የለም የሚባለው ነገር ልክ ባጣበት የእኛ ችክክ ብሎ መኖር ነው…›› ይላታል። ‹‹ኔትወርክ’ የለም፣ ኤሌክትሪክ የለም፣ ትራንስፖርት የለም፣ እኛ ግን አለን! አይገርምም? ያውም እኮ ጥንት አያቶቻችን እንዳስቀመጡ…›› ሲል ጎልማሳው በምሬት ይጮሃል። ‹‹ያደለው ሕዝብ ‘የለም’ የሚባል ቃል ከመዝገበ ቃላቱ ተሰርዞለታል፣ እኛ በየለምና በአልቋል ታሽተን ማለቃችን ነው፤›› በማት አንድ ወጣት በምፀት ሳቅ ይናገራል። ‘ሆድ ያባውን መንገድ ያወጣዋል’ የሚባል ይመስል መንገድና መንገደኛ በተገናኙ ቁጥር የምንሰማው ብሶት እያደር አይሏል። ወያላው “ሒሳብ” እያለ ሲዘዋወር “ስንት ነው?” እያለ የለመደውን መንገድ ታሪፍ እንደ አዲስ የሚጠይቀው ተሳፋሪም ነበር። የየወቅቱ የዋጋና የታሪፍ ለውጥ ወሬ የታከተው ዝምታ ውስጥ ነበር። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የአኗኗር ዘዬ ለሚደቆሰው የኅብረተሰብ ክፍል ከጉሮሮው ላይ የምትቀነሰው ሰባራ ሳንቲም ትርጉሟ ቀላል አይደለምና፡፡ ‹‹ሻይም፣ ቡናም፣ ዳቦም፣ ሽሮም፣. . . ዋጋቸው ሲንር ምን ይደረግ ታዲያ?›› ይላል አንዱ በሐሳብ ውስጥ ሆኖ ለራሱ እያወራ፡፡ ሰሚ ሲጠፋ ምን ይደረግ!
ያች ወይዘሮ፣ ‹‹እናንተ ይኼ የክልል እንሁን ጥያቄ ጉዳይ መያዣ መጨበጫ አጣሳ? ባለፈው ‘ከዚህ በኋላ ጥያቄ አቀራረቡ በሰላማዊ መንገድ ካልሆነ ድርድር አይኖርም’ አሉ ተባለ። በሌላ በኩል ደግሞ በመብታችን ማንም አያገባውም ተባለ። ደግሞ ይኼን ሰምተን ሳናድር በራስ ጊዜ ክልል ለመሆን መሞት ቀጠለ ይባላል። ኧረ እንዴት ነው ነገሩ?›› ከማለቷ ያም ያም ይናጠቃት ያዘ። ‹‹ዕድሜ ለፖለቲከኛ ተብዬዎች ተቀምጠን መክረን በጋራ በመወሰን አንታወቅ! እህ ምን እናድርግ ታዲያ? መጨረሻውን ማየት ነው እንጂ!›› ብሎ ጎልማሳው ጀመረ። ‹‹‘ሲያባብሉት የሚያለቅስ ቢቆነጥጡት ምን ሊሆን ነው’ እንዳይሆን እስከ መጨረሻው ጉዳያችንን በበሳል ሐሳብ ማስረዳት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው…›› ትላለች ከሾፌሩ አጠገብ የተቀመጠች ሽቅርቅር ወጣት። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች አንደኛው፣ ‹‹አይ እናንተ ቀና ልብ ጠፍቶ እንጂ አስተማሪውና አስረጂውማ እንደ ዘንድሮ ሞልቶ የተረፈበት ዘመን አልነበረም። ምን ዋጋ አለው ሕፃን አዋቂው፣ ሠለጠንኩ ባዩም ሆነ ኋላ ቀሩ ነገር መጎንጎን ሱስ ሆነበት። በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚለው ምሁር የሚባለው ዝም ሲል አያሳዝንም? የቸገረ ነገር እኮ ነው!›› አለ። ‹‹የአገራችን ምሁራን ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል ቢባል የሚቀል ይመስለኛል፡፡ ፀጉሩ ከተመለጠው እስከ ሸበተው ድረስ ግራ የገባው ፖለቲካ ላይ ተንጠልጥሎ ይራኮት እንጂ፣ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲሆን መቼ ይታያል? የሌላ አገር ፖለቲከኞችና ምሁራን በየቀኑ ይጠቅመናል የሚሉትን ነገር ሁሉ ሲጽፉና አስተያየት ሲሰጡ የኛዎቹ የታሉ? አርቲ ቡርቲ ነገር ላይ ተጥደው ያሰለቹናል፡፡ መጥኔ ለእነሱ…›› እያለች ወጣቷ በደም ፍላት ተናገረች፡፡ በስንቱ እየተቃጠልን እንኖር ይሆን!
ወደ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ተጠግተናል። ወያላችን ‹‹መጨረሻ›› ሊለን የተወሰኑ ሜትሮች ብቻ ቀርተውናል። በኔትወርክ መቆራረጥ ሳቢያ በስልኩ የሚጮህ ተሳፋሪ ሌሎቻችንን ጨምሮ እየረበሸን ነው። ‹‹የማያልፍላት አገር!›› ይላል እየቆየ። ‹‹አይዞን ዓባይ ተገድቦ ኃይል እስከሚያመነጭ ነው!›› ይላል አብሮት ያለው። ‹‹ተወኝ እስኪ የፈረደበት ዓባይ!›› ሲል ይመናጨቃል። ለወትሮው ተረጋግቶ አረጋጊው ዛሬ አጉል ዝምታ ውጦታል። አንዳንዴ ቃልም እንደ ‘ኔትወርክ’ እና ኑሮ ይወደዳል መሰል? ‹‹አሁን እስኪ ሠርተን እንዳንበላ ነው እንዲህ እያዳናቆሩ የሚጫወቱብን? ምን ዓይነት ጣጣ ነው?›› በሽቋል። ‹‹በበኩሌ የቅድሙ ጎልማሳ ያመጣው ሐሳብ አሪፍ ሳይሆን አይቀርም ባይ ነኝ። ያወጣነውን ያህል አውጥተን ኔትወርክ ማቅረብ የሚችል ሥራ ፈጣሪ ብንፈልግ የሚሻል ይመስለኛል…›› ቢል አንዱ ወጣት፣ ‹‹በሉ ደግሞ እንደ እሱ እያላችሁ አስበሉን፣ ትቀልዳለህ ልበል? ሌብነቱን እንኳን በቀላሉ ሊሰወር በሚችል ግለሰብ ደረጃ በተቋም ደረጃም መቆጣጠር አልቻልንም…›› ስትል ወይዘሮዋ መረር ባለ ድምፅ ተናገረች። ‹‹ታዲያ ምን ይሻላል?›› ብሎ ቢጠይቅ ከወደ ጋቢና፣ ‹‹ያ ምስኪን እንዳለው ፈጣሪ ዕጣውን እስኪያወጣልን የምኞት ሎተሪ መቁረጥ ነው እንዳልልህ ተስፋ መቁረጥ ይከተላል!›› ሲለው፣ ‹‹ምን ነካህ! ተስፋ መቁረጥማ አይታሰብም፡፡ ባይሆን ተስፋ አስቆራጮችን ራሳቸው ተስፋ እንዲቆርጡ እያደረግን ከዋሻው መጨረሻ ያለውን ብርሃን እንፈልጋለን…›› እያለ በሞራል ሲናገር ኋላ መቀመጫ ላይ የነበሩት ሁለቱ ወጣቶች በፉከራ ዓይነት ‹እንዲያ ነው እንጂ!› በማለት አስተጋቡለት። ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን ከፈተው። መልካም ጉዞ!