Friday, December 8, 2023

የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እንዲቀጥል ፍላጎት መኖሩን ያመላከተው ጥናት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዜጎች በአገራቸው ስለሚከናወኑ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ባህላዊና ሌሎች ጉዳዮች ምን እንደሚያስቡና ምን ቢሆን የተሻለ ሊሆን እንደሚችል የማሰላሰልና የመብሰክሰክ ሁኔታ የዕለት ተዕለት የሕይወታቸው አንድ አካል ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በተለያየ መንገድ እነዚህን ጉዳዮች የተመለከቱ ጥያቄዎችና ሐሳቦች የሚነሱ ሲሆን፣ በተደራጀ መልኩ ደግሞ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ዜጎች ያላቸውን ምልከታ የሚዳስሱ በርካታ ጥናቶች ይከናወናሉ፡፡ እነዚህ ጥናቶችም የዜጎችን ምልከታና ፍላጎት ከመጠረዝ ባሻገር፣ ለፖለቲከኞችና ለፖሊሲ አውጪዎች እንደ ግብዓት ምንጭነት ሆነው ያገለግላሉ፡፡

የዜጎችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ አስተያየትንና ፍላጎቶችን የሚያጠኑ የተለያዩ ተቋማት ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መሀል አንዱ ዋና ጽሕፈት ቤቱን በጋናዋ ርዕሰ መዲና አክራ ያደረገው አፍሮባሮሜትር አንዱ ነው፡፡ ይህ ተቋም በአፍሪካ ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩ የጥናትና ምርምር ተቋማት ዋነኛው ሲሆን፣ ከጋናው ዋና ጽሕፈት ቤቱ በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካና በኬንያም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት፡፡

ተቋሙ አፍሪካ ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሠራ ገለልተኛ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን፣ በዋናነትም በዴሞክራሲ፣ ከአስተዳደርና በኑሮ ጥራት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን በማጥናትና በማጠናቀር ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1999 የጥናትና ምርመራ ሥራውን የጀመረውን ይህ ተቋም፣ እስከ 2018 እ.ኤ.አ. ድረስ በ38 የአፍሪካ አገሮች ላይ ባደረገው የሰባት ዙር ጥናትም ለፖሊሲ ግብዓትነትና ለተጨማሪ ምርምር እንዲሁም ለውይይትና ክርክር በር የሚከፍቱ በርካታ ጥናቶችን አከናውኗል፡፡

የአፍሮባሮሜትሮ ጥናቶች የሚከናወኑት በዋነኛነት በገጽ ለገጽ ቃለ መጠይቅ አማካይነት ሲሆን፣ የጥናቱ የመረጃ አሰባሰብ ሒደት ደግሞ ተሳታፊዎቹ በሚመርጡት አካባቢያዊ ቋንቋ ይሆናል፡፡ የተቋሙ ጥናቶች የሚደረሱበት ማጠቃለያን ተዓማኒ መሆኑን ለማረጋገጥ ወካይ የሆነ የናሙና መጠን ይወሰዳል፡፡

ይህ ተቋም የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን የተመለከቱ ጥናቶችን እንደሚያደርግ ቢታወቅም፣ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ግን ኢትዮጵያን በተመለከተ ጥናት ያከናወነው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. በ2013 ያከናወነው የመጀመርያው ጥናት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፋ የሆነውን የጥናት ውጤት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል፣ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችም እንዲታከሉበት እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን እንዲገደብ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳየው ጥናት፣ አንድ ወር በፈጀ የመስክ ሥራ መከናወኑን በኢትዮጵያ የአፍሮባሮሜትር ናሽናል ፓርትነር አቶ ሙሉ ተካ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

ጥናቱ የተካሄደው 2,400 ቃለ መጠይቆችን ዕድሜያቸው ከ18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በማሳተፍ የተከናወነ ነው፡፡ የናሙናው መጠን በአገር አቀፍ ደረጃ የተሠራና ወካይነት ያለው ሲሆን፣ የስህተት ህዳጉ +/-2 መቶኛና የአስተማማኝነት ደረጃውም 95 በመቶ እንደሆነ የዘንድሮው የጥናት ውጤት ይፋ በሆነበት ወቅት ተገልጿል፡፡

ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ በጥናቱ የተሳተፉ ዜጎች ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል፣ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲበዛና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመን መገደብ አለበት በሚለው ሐሳብ የተቀራረበ ምላሽ የያዙ ቢሆንም፣ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት ምላሽ ግን የተከፋፈለ እንደነበር ከጥናቱ ውጤት መረዳት ይቻላል፡፡

የተከፋፈለ ምላሽ ካስተናገዱ አገራዊ ጉዳዮች መካከል ደግሞ የመሬት ባለቤትነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ስለማቋቋም፣ በአገሪቱ ባንዲራ መሀል ላይ ያለው ዓርማ የተመለከተውና የአዲስ አበባ ከተማ የአስተዳደር ሁኔታን የተመለከቱት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሰኞ ዕለት ይፋ የሆነው ይህ የአፍሮባሮሜትር ኢትዮጵያን የተመለከተው የጥናት ውጤት፣ በውስጡ በርካታ ጉዳዮችና ግንኝቶቻቸው በአኃዝ ተደግፈው ቀርበዋል፡፡ በዋነኛነት ግን የጥናቱ ግኝት በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና አሁን አገሪቱ በምትከተለው የፌዴራሊዝም አወቃቀር ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት አብዛኛዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች ሕገ መንግሥቱ በአዲስ መተካት ሳይሆን መሻሻል እንዳለበት መስማማታቸውን ይፋ ሆኗል፡፡ በጥናቱ መሠረት ይህ ፍላጎት የመነጨው ደግሞ በአገሪቱ ዛሬ ላይ ያሉትን ፍላጎቶች ለማስታረቅና ለማካተት ያግዛል ከሚል መነሻ ነው፡፡ ሆኖም ሕገ መንግሥቱ በሚሻሻልበት ወቅት ከላይ ወደታች መንገድን የተከተለ ብቻ መሆን እንደሌለበትና ‹‹የተርታው›› ኅብረተሰብ ሐሳብና ተሳትፎ ሊኖር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አብላጫዎቹ በጥናቱ የተሳተፉ ዜጎች የፌዴራል መንግሥቱ ቋንቋ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችም እንዲካተቱ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን በሁለት የምርጫ ጊዜ ብቻ እንዲገደብና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጪ የሕገ መንገሥት ጉዳዮችን የሚያይ ፍርድ ቤት መቋቋሙን እንደሚሹ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል የተመለከተ የጥናቱ ግኝቶች

በጥናቱ ከተሳተፉ አሥር ኢትዮጵያውያን በመቶኛ ሲሰላ 69 በመቶዎቹ ሕገ የመንግሥቱን መሻሻል የሚፈልጉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አሥራ አንድ በመቶዎቹ ደግሞ አሁን በሥራ ላይ ያለውና በ1987 ዓ.ም. የፀደቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከነአካቴው መወገድ አልያም ደግሞ በአዲስ መተካት አለበት የሚል አቋም እንዳላቸው ጥናቱ አመላክቷል፡፡ በተጨማሪም አሥራ ስምንት በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት አሁን ባለበት እንዲቀጥል መሻታቸውን ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ተሻሽሎ እንዲቀጥል የሚሹት ምንም እንኳን 69 በመቶ ቢሆኑም፣ እንዲሻሻል የሚፈልጉት የሕገ መንግሥት አንቀጾች ላይ ግን የተለያየ ምላሽ እንዳላቸው ጥናቱ አመላክቷል፡፡ በዚህም መሠረት እንዲሻሻሉ ከሚፈለጉት አንቀጾች መሀል በፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎች እንዲካተቱ የሚሉት 73 በመቶ ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለት የምርጫ ጊዜ ብቻ አገልግሎ ሥልጣን እንዲያስረክብ የሚፈልጉትም እንዲሁ 73 በመቶ ሲሆኑ፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን የሚከታተል ፍርድ ቤት ቢቋቋም ፍላጎታቸው የሆነው ደግሞ 55 በመቶ እንደሆኑ የጥናቱ ግኝት አመላክቷል፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት በሕገ መንግሥቱ ላይ ከሚገኙ በርካታ አወዛጋቢ አንቀጾች መሀል አንቀጽ 39 ዋነኛ ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ ከፋፋይ፣ የኢትዮጵያን አንድነትና የሕዝቦቿን አብሮ መኖር የሚሸረሽር በሚል ሲብጠለጠል የከረመ አንቀጽ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በዚህ ጥናት መሠረት ግን አንቀጽ 39 በሕገ መንግሥቱ እንዲቆይ የሚፈልጉ ዜጎች ከማይፈልጉት መብለጡ ተጠቁሟል፡፡

 በዚህም መሠረት ከአሥሩ የጥናቱ ተሳታፊዎቸ አራቱ በመቶኛ ሲሰላም 43 በመቶ ገደማ የሚሆኑት አንቀጽ 39 ከሕገ መንግሥቱ እንዲወገድ መሻታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አንቀጽ 39 የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል ዋስትና የሚሰጥ እንዲሁም የራስን ክልል የማዋቀር መብት የሚያረጋግጥ መሆኑን በመጥቀስ አንቀጹ በሕገ መንግሥቱ እንዲቆይ የሚፈልጉት 50 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ሌላው የጥናቱ ግኝት የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ የተመለከተ ነው፡፡ እንደ አንቀጽ 39 ሁሉ በአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው የኮከብ ዓርማም እንዲሁ በከፍተኛ ሁኔታ ሲብጠለጠል የነበረ አጀንዳ ነው፡፡ ሆኖም በጥናቱ ግኝት መሠረት ሰንደቅ ዓላማው መሀል ላይ ያለው ዓርማ ከሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲወገድ የሚፈልጉት በመቶኛ ሲቀመጥ 37 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ፣ 52 በመቶ የሚሆኑ በጥናቱ የተሳተፉ መላሾች ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ ባለበት እንዲቆይ ምርጫቸው መሆኑን ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል ብትሆን እንደሚመርጡ የገለጹት 35 በመቶ ሲሆኑ፣ ይህን ሐሳብ የሚቃወሙት ደግሞ 54 በመቶ እንደሆኑ ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ሕገ መንግሥቱ መቼ ይሻሻላል?

በጥናቱ ከተሳተፉ 69 በመቶ የሚሆኑት ዜጎች ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት በሚለው ሐሳብ መስማማታቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሥራ መቼ ይከናወን? በሚለው ላይ ግን የተለያየ ፍላጎት እንዳላቸው ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በዚህም መሠረት 34 በመቶ የሚሆኑት ሕገ መንግሥቱ ከስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስቀድሞ ቢሻሻል መሻታቸው መሆኑን ማስታወቃቸውን ሲገለጽ፣ 33 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ምርጫው ተካሂዶ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ቢሻሻል በማለት መልሰዋል፡፡ የተቀሩት 29 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ምርጫው ተካሂዶ ከአንድ ዓመት በኋላ ቢሻሻል እንደሚመረጡ ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡ በጥናቱ መሠረት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል በሚለው ሐሳብ ላይ ስምምነት ቢኖርም፣ አብዛኛዎቹ በጥናቱ የተሳፉ ዜጎች በመቶኛ ሲቀመጥ 92 በመቶ የሚሆኑት ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሒደት ‹‹ተርታው›› ማኅበረሰብን ባሳተፈ መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ከሰባት በመቶ የሚበልጡት ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በሚሻሻልበት ሒደት በምርጫ የተመረጡ የፖለቲካ አመራሮችን ባሳተፈ መልኩ እንዲሆን ጠቁመዋል፡፡

ፌዴራሊዝምን የተመለከተው የጥናቱ ግኝት

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን በፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር መቀጠል ላይ ብዙም ልዩነት ባይታይባቸውም፣ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ወይስ የመልከዓ ምድር አቀማመጥን መሠረት ያደረገ በሚለው የአተገባበር አካሄድ ላይ ልዩነት መኖሩን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በዚህም መሠረት ከአሥሩ በጥናት ከተካተቱ ተሳታፊዎች መካከል ስድስቱ በመቶኛ ሲሰላ ደግሞ 61 በመቶ የሚሆኑት በአገሪቱ ከአኃዳዊ ይልቅ ፌዴራላዊ መንግሥት መኖር ምርጫቸው መሆኑን ጥናቱ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ 37 በመቶዎቹ ደግሞ ፌዴራሊዝምን ከፋፋይ አድርገው በማየት አገሪቷ ወደ አኃዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ብትቀየር እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ምን ዓይነት ፌዴራሊዝም የሚለው ላይ የተለያየ አተያይ መኖሩን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሥርዓት አወቃቀር በአገሪቱ የሚቀጥል ከሆነ ግማሽ የሚሆኑት ወይም 49 በመቶ ገደማ በአገሪቷ ያለውን ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝምና በእሱ መሠረት የተዋቀሩት ክልሎች እንዲቀጥሉ ፍላጎት እንዳላቸው የተመላከተ ሲሆን፣ በተቃራራቢ ማለትም በመቶኛ ሥሌት 48 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ምርጫቸው የክልሎች አወቃቀር መልከዓ ምድራዊ አቀማጥ መሠረት ቢያደርግ እንደሚመርጡ ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

የዜጎችን ስሜት ለመለካት የሚደረጉ ጥናቶችን አስመልክተው ከሚነሱ ውስንነቶች መካከል ጥናቶቹ ከተከናወኑ በኋላ በጥናቱ የተገኙትን ግኝቶች ተከታትሎ ለማስፈጸም አልያም ለሚያስፈልጉ የፖሊሲ ግብዓቶች መጠቀም አለመቻል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የአፍሮባሮሜትር ግኝት እንዲህ ያሉ ውስንነቶችን እንዴት ይቀረፋል? ለሚለው ጥያቄ ‹‹ውጤቶቹን ከማሠራጨት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ውይይቶችንና ክርክሮችን በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ማከናወን ዋነኛው የአፍሮባሮሜትር ጥናት መለያ ነው፤›› በማለት አቶ ሙሉ ተካ ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡

በዚህ መሠረት ይፋ የሆነውን የሪፖርቱን ግኝቶችን አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከፓርላማው፣ ከአስፈጻሚው፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ከለጋሽ አገሮች፣ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር ቀጣይ ውይይቶችን እንደሚያዘጋጁም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -