Monday, May 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

እኔም ትንሽ ስለፊታውራሪ መርዳሳ ገዳ (አባ ሙላት)

በክብረማርያም ተክለጊዮርጊስ

ሚያዝያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ፣ በአስተያየት ዓምድ ሥር አቶ በዛወርቅ ሺመላሽ  ̋መርዳሳ ገዳ (አባ ሙላት) ማነው” በሚል ጀግናውን አርበኛ ፊታውራሪ መርዳሳ ገዳን በማስታወስ አቅርበዋል፡፡

ፊታውራሪ መርዳሳን በልጅነታችን የወልቂጤ ወረዳ ገዢ ሆነው እናውቃቸዋለን፡፡ ልጅ ይወዱ ስለነበር ትኩረት ሰጥተው ያናግሩን ነበር፡፡  ለመጨረሻ ጊዜ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ምናልባት በ1978 ዓ.ም. አውቶቡስ ተራ ተገናኝተን በአክብሮት ሰላምታ ሰጥቻለሁ፡፡

አቶ በዛወርቅ እኚህን በጣሊያን ጊዜ በጀግንነት የተዋጉ አርበኛን፣ እንዲሁም በሰላሙ ጊዜ በወረዳ ገዢነት ያገለገሉትን በማስታወሳቸው እያመሰገንኩ እኔም ስለፊታውራሪ የማውቀውን ትንሽ ልጨምር፡፡ ስለሳቸው መረጃ ለማሰባበሰብ ብዙ ጥረት አድርጌ በጊዜው ሁኔታና እሳቸውን በደንብ የሚያውቁ ሰዎች በሕይወት አለመኖር ምክንያት ሊሳካ ካለመቻሉም በላይ ብዙ ጊዜም ወሰደ፡፡

ፊታውራሪ ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ በሚወስደው መስመር ከጊቤ ወንዝ ወዲህ ጣደሌ በሚባል አካባቢ እርሻ፣ የእርሻ መሣሪያዎች እንዲሁም የከብት እርባታ ነበራቸው፡፡ በደርግ የመሬት አዋጅ የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም. ሲታወጅ ሁሉም ተወረሰ፡፡ እሳቸውም እንዴት እነጠቃለሁ በሚል እልህ ለመሸፈት ወሰኑ፡፡ አብረን እንሸፍት ብለው ካነጋገሯቸው ከፍተኛ የጦር መኰንኖች መሃል አንዱ ብሸፍትም ገዳም ነው እንዳሏቸውና በዚህም በጣም እንዳዘኑ ይነገር ነበር፡፡

አብረው ከሚሸፍቱ ጓዶቻቸው ጋር ከተስማሙ በኋላ ጠመንጃቸውን ታጥቀውና በበቅሏቸው ሆነው ጣደሌ እርሻ ቦታ የነበሯቸውን ከብቶች እያስነዱ ወደ አዲስ አባበ የሚወስደውን ዋናውን አውራ ጎዳና ተከትለው ወልቂጤን እና ወሊሶን አቋርጠው በገደባኖ በኩል ወደ ጎደዱላ አምርተዋል፡፡ ጎደዱላ የተወለዱበት፣ ያደጉበትና መጨረሻም ሸፍተው የተዋጉበት አካባቢ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በመቀጠል ባለቤታቸውም ወ/ሮ በለጠች የቀሩትን በግ እና ፍየል አስነድተዋል፡፡ ይህም በወቅቱ በነበሩ የወልቂጤ ነዋሪዎች የሚታወስ ሲሆን፤ ልጆቻቸውም አስቴር መርዳሳና ጌታቸው መርዳሳ የሚያውቁትና የተሳተፉበት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ደርግ ስድሳ የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ባለሥልጣናትን በግፍ ከረሸነ በኋላ ነው፡፡

ከመሬት አዋጅ በፊት የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ አዋጅ በታኅሣሥ ወር 1967 ዓ.ም. ታውጆ ዘማቾች በየወረዳው ተመድበው ነበር፡፡ ቡኢ ወረዳ ከተመደቡ ዘማቾች ውስጥ የወልቂጤ ልጆች ነበሩበት፡፡ ይህም እሳቸው ለሸፈቱበት አካባቢ ቅርብ ነበር፡፡ ፊታውራሪ እነዚህን ዘማቾች ምሳ ጋብዘው በሽፍቶች በኩል ዘማችን የማጥቃት ሐሳብ እንዳለና እሳቸውም “ድንጋይ ያልያዘ ተማሪ መነካት የለበትም” የሚል አቋም ይዘው መከራከራቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ በተጨማሪም እኔ ከወላጆቻችሁ ጋር የበላሁና የጠጣሁ ስለሆነ እዚህ አካባቢ ባትቆዩ የሚል አስተያየት ሰጥተዋቸዋል፡፡

በኋላም እነ ፊታውራሪ ስብሰባ ላይ ተቀምጠው እያለ ለዘማቾች በጎን ደብዳቤ አስልከው በዘማች ጉዳይ ክርክር ላይ መሆናቸውንና የሳቸው ሐሳብ ውድቅ ከተደረገ ሊጠቁ ስለሚችሉ አካባቢውን ለመልቀቅ እንድትዘጋጁ ብለው ማስተላለፋቸውን የወቅቱ ዘማቾች ያስታውሳሉ፡፡ ይህም በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ወቅት ቡኢ ወረዳ ጣቢያ ዘማች የነበሩና ግብዣ የተደረገላቸው በኋላም ደብዳቤ የተጻፈላቸው አቶ ፍርዱ አየለና አቶ አስፋው ንጋ ያረጋገጡት ነው፡፡

የፊታውራሪ መርዳሳን ታሪክ በመጽሐፍ መልክ የማዘጋጀት የአቶ በዛወርቅ ሺመላሽ ምኞት  እውን እንዲሆን እኔም እመኛለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles