Friday, June 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ያልመለሳቸው ጥያቄዎች

በፍሬው አበበ

የኮሮና ወረርሽኝ ችግር ልጆቻችንን ከቤት ካዋለ ከስድስት ወራት በላይ ተቆጠረ፡፡ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ሲወሰን፣ የበሽታው ሥርጭት ገና የጀመረበት አፍላ ወቅት ነበር፡፡ ዛሬ እጅግ ተስፋፍቶ በቀን ከ1,500 በላይ ሕሙማን በምርመራ የሚገኙበት ደረጃ ሲደረስ ደግሞ ስለ ትምህርት ምዝገባ ጉዳይ መወራት መጀመሩ በራሱ አስገራሚ ሆኗል፡፡ ሰሞኑን የትምህርት ሚኒስቴር ለ2013 የትምህርት ዘመን ከነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ እንዲያካሂዱ ፈቅጃለሁ ብሏል፡፡ ውሳኔው በተለይ በወላጆች ዘንድ ከፍተኛ መደናገርን ፈጥሯል፡፡ መደናገር የፈጠረው የመጀመርያውና ትልቁ ነገር ሚኒስቴሩ ያወጣው መመርያ ሾላ በድፍኑ ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ብዥታው በተለይ በወላጆች ዘንድ በርካታ ጥያቄዎችን እያጫረ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስትር  ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)፣ ሰሞኑን ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ የቀጣዩ ዓመት ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ በትክክል እንደማይታወቅ አረጋግጠዋል፡፡ አያይዘውም ትምህርት ለመጀመር ቢያንስ የበሽታው ሥርጭት መቀነስ እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ሲጀመርም መጀመርያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመክፈትና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መማርያ ክፍሎች ጭምር እየተጠቀሙ እንዲማሩ መታሰቡን ቢያወሱም የመጨረሻ ውሳኔ አለማግኘቱን ግን ጠቅሰዋል፡፡ የተማሪዎች ምዝገባ እንዲካሄድ የተፈቀደው ትምህርት ቤቶች አስቀድመው ዝግጅት እንዲያደርጉ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ ምዝገባውም በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲከናወንም አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የቀጣዩ ዓመት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ለጥንቃቄ የሚረዱ በቂ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አቅርቦት፣ ሳኒታይዘርና ሌሎች የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦቶችን ለማስተካከል አስቀድሞ ዝግጅት እንደሚደረግባቸውም ተናግረዋል፡፡

የሚኒስትሩን ማብራሪያ መነሻ አድርገን አንዳንድ ሐሳቦችን እናንሳ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንደ አንድ ወላጅ ይህ የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለምን?

ለትምህርት ቤቶች መዘጋት ትልቅ ምክንያት የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝን  ደረጃ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ወረርሽኙ ትምህርት ከተዘጋበት መጋቢት 2012 2012 ዓ.ም. አንፃር የነሐሴ ወር እጅግ አስከፊ ደረጃ የደረሰበት ነው ማለት እችላለን፡፡ ይህን የሚለው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አይደለም፡፡ የጤና ሚኒስቴር ሰዎች መረጃ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ እንደሚለው፣ በነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ 200 ሺሕ ሰዎችን የመመርመር መርሐ ግብር ተጀምሯል፡፡ ምርመራው በተጀመረ በሰባት ቀናት ውስጥ ብቻ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ80 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ እንደሚለው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከነሐሴ 8 እስከ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በነበሩት ሰባት ቀናት ብቻ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ 58 በመቶ አሻቅቧል፡፡ በዚህ ወቅት 4,767 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል፡፡

በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከነሐሴ መጀመርያ ተመዝግቦ ከነበረው 3,016 አንፃር 1,751 ወይም 58 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያሳያል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በተጠቀሱት ሰባት ቀናት በከተማዋ 119 ሰዎች በኮቪድ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በነሐሴ ወር መጀመርያ 93 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣  በሰባቱ ቀናት ብቻ 119 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል፡፡ 24 በመቶ የሚሆነው የሞት መጠን የተመዘገበው በያዝነው ወር በሁለተኛ ሳምንት በነበሩት ሰባት ቀናት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህም ካለፈው ሳምንት አንፃር 26 ሰዎች ሕልፈት ወይም 28 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ቢሮው ማስታወቁን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ረቡዕ ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም በአንድ ቀን (24 ሰዓት) ብቻ 1,533 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ዕለት 18,724 የናሙና ምርመራ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ወገኖች ቁጥር እስከዚህ ዕለት ድረስ 45,221 የደረሰ ሲሆን፣ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች ቁጥር ደግሞ በጠቅላላው 725 መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ቁጥሩ ምን ይነግረናል?

ቁጥሮቹ በአጭሩ የኮሮና ወረርሽኝ ሥጋትነቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያሉ፡፡ የመቀነስ አዝማሚያዎች አለመኖሩ ትምህርት ቤቶችን ያህል ተቋማት ለመክፈት እንደማያስችል ለመረዳት ነቢይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ አሁን ወደ ምዝገባው ጉዳይ እንለፍ፡፡

የትምህርት ቤቶችና የወላጆች ግንኙነት በውል ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ተገቢውን የትምህርት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ወላጆች ደግሞ ለተሰጣቸው አገልግሎት የተስማሙበትን ክፍያ ይፈጽማሉ፡፡ ግንኙነቱ ይኸው ነው፡፡  ነገር ግን ትምህርት ሚኒስቴር በሁለት ወገኖች ኮንትራት መካከል በድንገት ሲገባ ተገቢውን ጥንቃቄ ያደረገ አይመስልም፡፡ የሚኒስቴሩ ጣልቃ ገብነት ያስፈለገው አላስፈላጊ ውዝግቦችና አለመግባባቶችን ለመፍታት በሚል እንደሆነ ይገባናል፡፡ ግን የሚኒስቴሩ አገባብ ነገሮችን የሚደበላልቅ እንዳይሆን የቱን ያህል ጥንቃቄ ወስዷል? የሚለው በአግባቡ የታየ አይመስልም፡፡ በኮንትራት መካከል ሲገባ አንዱን ወገን ዝም ብለህ ገንዘብ ሰብስብ ማለት ወይም ለአገልግሎት ሰጪው ብቻ ማድላት ፍትሐዊ ውሳኔን አያሳይም፡፡ ገንዘቡ የሚከፈለው ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ እናም ገንዘብ የሰበሰቡት የትምህርት ተቋማት ከመስከረም ጀምሮ ለተከፈላቸው ወር አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችል ሁኔታ ላይ ናቸው ወይ? የሚለውንም አብሮ መመለስ ያስፈልግ ነበር፡፡ ለዚህ ነው ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ያልኩት፡፡

የትምህርት መጀመርያ ትክክለኛ ጊዜ ሳይታወቅ ትምህርት ቤቶቹ ገንዘብ እንዲሰበስቡ ተፈቀደላቸው፡፡ ወላጆችስ ምን ያገኛሉ? ለሚለው ሚኒስቴሩ በተገቢው ሁኔታ አልመለሰም፡፡ በአጭሩ ሚኒስቴሩ ያተኮረው በትምህርት ተቋማቱ ጥቅም ጉዳይ ላይ ብቻ መሆኑ ለምን የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ጉዳዩ ከሙስናና ብልሹ አሠራር የቱን ያህል የፀዳና የእኩል ተጠቃሚነትን መርህን (በወላጆችና በትምህርት ተቋማት መካከል) ያሟላ ነው የሚል ጥያቄንም የሚያስከትል ነው፡፡

 ሚኒስቴሩ በአንድ በኩል የትምህርት መጀመርያው ጊዜ እንደማይታወቅ ይናገርና ቢሆንም ግን ምዝገባ አካሂዱ ይላል፡፡ በተለይ በግል የትምህርት ተቋማት ዘንድ ምዝገባ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ወላጅ አዲስም ሆነ ነባር ልጁ የምዝገባ፣ የወርኃዊ ወይም የተርም ክፍያ የሚፈጽምበት ሥርዓት ነው፡፡ እናም ከዚህ አንፃር ሚኒስቴሩ ተመዝገቡ ሲል ምን እያለ ነው? ትምህርት በመስከረም ወር ቢጀምርም ባይጀምርም ክፍያውን ፈጽሙ ማለቱ ነው? ወይስ በእርግጠኝነት ትምህርት ስለሚጀመር ተመዝገቡ ማለቱ ነው፡፡ ግልጽ አይደለም፡፡ እናም አሁን እጅግ አጠያያቂ የሆነው ጉዳይ የወረርሽኙ ሁኔታ በተባባሰበት ምናልባትም በቀጣይ አንድና ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የመቀነስ አዝማሚያ ስለማሳየቱ እርግጠኛ መሆን በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር ዝግጅት ለማድረግ በሚል ሰበብ ተማሪዎች ምዝገባ እንዲያካሂዱ ለምን ወሰነ የሚለው ነው፡፡ የወረርሽኙ ሁኔታ የመቀነስ አዝማሚያ በሚያሳይበትና ትምህርት ለመጀመር ምቹ ሁኔታ አለ ተብሎ በሚታሰብበት ወራት ምዝገባ ቢካሄድ እስከዚያው ግን ወላጆች ተዘጋጅተው እንዲጠባበቁ ቢነገር ችግሩ ምንድነው?

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የትምህርት ሚኒስትሩ ለኢቲቪ የሰጡትን ማብራሪያ በደንብ ተከታትሏል፡፡ ከማብራሪያቸው የተረዳውም የቀጣዩ ዓመት ትምህርት በመስከረም ወር የመጀመር ዕድሉ እጅግ ጠባብ መሆኑን ነው፡፡ በእሳቸው ማብራሪያ መሠረት ትምህርት ለመጀመር የወረርሽኙ ሁኔታ ቢያንስ መቀነስ አለበት፡፡ ይህ አሁን ባለንበት ነሐሴ ወር አጋማሽ በተቃራኒው የተባባሰበት መሆኑ ተስፋውን ያደበዝዛል፡፡ ለተማሪዎች የሚያስፈልጉ የንፅህና መሣሪያዎች መሟላት ጉዳይ ገና የተቋጨ አይደለም፡፡ እንዴት ይማሩ የሚለውና ሚኒስትሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አቆይተን የአንደኛ ደረጃ እንከፍታለን ያሉበት ሁኔታ እንደምን ሊተገበር ይችላል የሚለው ገና ሰፊ ምክክር ተደርጎበት መግባባት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ሕፃናት ልጆችን ቀኑን ሙሉ ማስክ  አልብሶ በጥንቃቄ የመማር ማስተማር ሒደቱን ማካሄድ ይቻላል ወይ የሚለው በአያሌው የሚያነጋግር ነው፡፡ እናም በወላጆች ዘንድ እጅግ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሚኒስቴሩ እንዲህ ዓይነቱን ማኅበረሰቡን በቀጥታ የሚመለከት ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ቢያንስ በየደረጃው ምክክር ማድረግ አለመቻሉ ትልቁ ችግር ይመስለኛል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ወላጆችን የሚጎዳ ውሳኔ ሲያሳልፍ በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት በወራት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ሚያዝያ 12 ቀን 2012 ዓ.ም.  ባወጣው መመርያ ወይም መግለጫ  ልጆቻቸውን በግል ምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች ለወርኃዊ ክፍያ ከሚከፍሉት 50 እስከ 75 በመቶ ይክፈሉ አለ፡፡ ትምህርቱንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይስጡ ብሎ ነበር፡፡ ግን በአብዛኛው ወሬ ሆኖ ቀረ እንጂ፡፡ ይታያችሁ?! . . . ይህ ውሳኔ የተሰጠው ልጆቻችን ትምህርት ቤት ከመዘጋቱ ጋር ተያይዞ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በቤታቸው በተቀመጡበት ወቅት ነበር፡፡ ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች ያስከፈሉት 75 በመቶውን ነው፡፡ በእርግጥም ከእነሱ ጥቅም አንፃር ትክክል ነበሩ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ወላጆች ‹‹ልጆቻችን ቤት በተቀመጡበት ከ50 በመቶ በላይ መክፈላችን ትክክል አይደለም፤›› ቢሉም ሰሚ አላገኙም፡፡ ለበላተኛ አሳልፎ የሰጣቸው ሚኒስቴሩ ነውና፡፡

የአሁኑ ይባስ እንዲሉ፣ የሰሞኑ መመርያ (አንዳንዶች ማሳሰቢያ ይሉታል) ሾላ በድፍኑ ነው፡፡ ለምንድነው ወላጆች ልጆቻቸውን አስመዝግበው ከመስከረም ወር ጀምሮ የሚከፍሉት? ትምህርት በመስከረም ወር ባይጀመር በወላጆችና በትምህርት ተቋማት መካከል ውዝግብ አይነሳም ወይ? ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ ማድረግ አይችሉም ከማለት ውጪ ሰሞኑን ተመዝገቡ ሲል ሙሉ በሙሉ ከፍለው ነው ወይስ እንደዚህ ቀደም ከ50 እስከ 75 በመቶ ነው ለሚለው ያስቀመጠው ማብራሪያ የለም፡፡ ይህ ዝምታው ወላጆች መቶ በመቶ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ነው፡፡

እናም ሚኒስቴሩ የትምህርት መጀመርያ ጊዜ በትክክል ባልታወቀበት፣ የኮሮና ወረርሽኝም የመቀነስ አዝማሚያ ባላሳየበት ሁኔታ ያሳለፈው የትምህርት ምዝገባ መግለጫ ተገቢነት ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ቢቻል  ውሳኔውን መልሶ ሊያጤነው ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles