Friday, June 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ባንኮች ከውጭ ባንኮች ተበድረው እንዲያበድሩ መፈቀዱ ጥሩ ዕርምጃ ነው ‹‹ግን››

በመታሰቢያ መላከሕይወት ገብረ ክርስቶስ

በመጀመርያ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ሐሳቤን ከመግለጼ በፊት በቅርቡ ያሳተምኩትና ለንባብ የበቃው ‹‹አቃፊ ማንነት›› በሚል ርዕስ የተጻፈ መጽሐፍ እንድታነቡ የተከበራችሁ አንባቢያንን እየጋበዝኩ፣ መጽሐፉ የእኔን ብቻ ሳይሆን ከአሥር በላይ ታላላቅ ምሁራን ሥራዎች የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ሁለቱም በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መፍትሔ አፈላላጊ ሐሳቦችንና እጅግ በርካታ ሳይንሳዊ ጥናቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡

በቅርቡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለየት ያለ አዲስ መመርያ ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ይህ መመርያ ባንኮች ከውጭ አገር ባንኮች እየተበደሩ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ማበደር እንደሚችሉ የሚፈቅድ ሲሆን ይህ ውሳኔ በእርግጠኝነት በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሆነ ማዕበል መፍጠሩ አይቀርም፡፡

ሁሉም የአገራችን ባለሀብቶች በአንድ ላይ ቢጠየቁ፣ ለመሆኑ ያለባችሁ ዋነኛ ችግር ምንድነው ተብለው ቢጠየቁ፣ ‹‹ችግራችን እንደልባችን የምንበደረው ገንዘብ አለመኖሩ ነው›› ማለታቸው አይቀርም፡፡ ሰሞኑን የወጣው መመርያ ይህንን እጥረት በመዝጋት እጅግ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ይህ መመርያ ብቻውን ምንም ዓይነት ለውጥ አያመጣም፡፡ ምክንያቱም ከመመርያው ጋር ተያይዞ በርካታ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመርያው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ እንደሚታወቀው የአንድን አገር ሉዓላዊነት ከኢትዮጵያ ላይ አንስቶ ለብሔር ብሔረሰቦች የሰጠ በመሆኑ ክልሎች የእኛ ሥልጣን ከፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ይበልጣል ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በባለሀብቶች ላይ ከፍተኛ ወከባ ስለሚፈጥሩና ባለሀብቶች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ከውጭ የመጣውን ብድር እየተጠቀሙ በየክልሉ ልማት እየሠሩ ብድራቸውን መክፈል ካልቻሉና ካቃታቸው አገሪቷን ወደ አስከፊ ድህነት ውስጥ ነው የሚከታት፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት ከውጭ አበዳሪዎች እየተበደረ ስኳር ፋብሪካ ለመገንባት የሄደበት መንገድ በኪሳራ እንደተጠናቀቀ ለማንም ግልጽ ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ የግሉ ሴክተር እየተበደረ ዕዳውን መክፈል ካልቻለ ዕዳው ወደ መንግሥት ዕዳነት ነው የሚዞረው፡፡ ምክንያቱም የውጭ ባንኮች ለኢትዮጵያ ባንኮች ያበደሩትን ገንዘብ ማስመለስ ካልቻሉ በቀጥታ የብድሩን ሰነድ ለዓለም ባንክ የሚሸጡ በመሆኑ የዓለም ባንክ ደግሞ ያንን ሰነድ ተረክቦ የኢትዮጵያ አገራዊ ዕዳ ላይ ይከምረዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ዕዳውን ሲከፍል ከታክስ በተሰባሰበ ገንዘብ ላይ ወይም ከሌላ ምንጭ ያገኘውን ገንዘብ ለዕዳ ክፍያ ያውለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል የሚችልበት ሁኔታ ስለማይኖር በቀጥታ የአገሪቱ ሕዝቦች ወደ ድህነት እንሄዳለን ማለት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ብድር መበደር በጣም ቀላል ነው፡፡ ችግሩ ሁልጊዜ ብድርን በአግባቡ የመክፈል ብቃት ነው፡፡ ብድርን ደግሞ በአግባቡ ለመክፈል ያሉትን ሁሉንም ዓይነት ‹‹ደንቃራዎች›› ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ አንዲት ቁንፅል መመርያን ብቻ በማውጣት የሚያመጣው ምንም ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢሕአዴግ ዘመን የተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ በኪሳራ ነው የተጠናቀቁት፡፡ አንድ ፕሮጀክት ተገንብቶ፣ በጊዜው ተጠናቆ፣ ወደ ሥራ ገብቶ የራሱን ዕዳ ራሱ መክፈል ካልቻለ በኪሳራ እንደተጠናቀቀ ነው የሚቆጠረው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት የዚያን ፕሮጀክት ዕዳ ለመክፈል ከሕዝብ የተሰበሰበን የታክስ ገንዘብ ለመጠቀም መገደዱ አይቀርም፡፡

እነ ቻይና አገራቸውን ከድህነት ለማውጣት ሲነሱ የብድር ገንዘብ አይደለም የተጠቀሙት፡፡ እንደ መነሻ ካፒታል (Upfront Capital) የተጠቀሙት የሕዝባቸውን ጉልበት ነው፡፡ እኛ ይህን ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ በዓለም ላይ የተትረፈረፈ በትሪሊዮን የሚቆጠር ካፒታል አለ፡፡ ይህንን ሀብት ወደ አገራችን በማስገባት ሥራ ላይ ማዋል እጅግ ብልህነት ነው፡፡ ነገር ግን ገንዘቡን ብቻ ወደ አገር ቤት ማምጣት ዋጋ የለውም፡፡ የግድ ተዛማጅ ሥራዎች ሁሉ መሠራት አለበት፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የሕገ መንግሥት ዕርምት፣ የመሬት ፖሊሲ ጉዳይ፣ አገራዊ ወጥነት ያለው ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ የላይኛው (የፌደራል መንግሥት)፣ መካከለኛው (የክልል መንግሥታት)፣ የታችኛው (ዞንና ወረዳ) ተናበው መሥራት የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋት የውጭ ዕዳ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ሊሠሩ ከሚገቡ ተግባራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ሌላው ደግሞ ባለሀብቶች ያለችግር ተበድረው ወደ ምርት ገብተው ቶሎ ዕዳቸውን መክፈል እንዲችሉ የመንግሥት ቢሮክራሲ የበለፀገ አዕምሮ ባላቸው ምሁራን መተካት አለበት፡፡

ዓባይ ተገድቦ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ወደ ሥራ ሲገባ ከኤሌክትሪኩ ጋር የሚመጣጠን የገንዘብ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ግድ ነው፡፡ ገንዘቡ ደግሞ በፍጥነት ተገኝቶ ባለሀብቶች ፋብሪካን የመሳሰሉ የከፍተኛ ኢነርጂ ፍጆታ ያላቸው ተቋማትን እየገነቡ፣ የተመረተውን ኤሌክትሪክ መግዛት መቻል አለባቸው፡፡ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት ማለት አሁን እያመረተ ካለው ኤሌክትሪክ ከዕጥፍ በላይ በመሆኑ፣ የገንዘብ አቅርቦቱም አሁን ካለው የገንዘብ አቅርቦት አኳያ ከዕጥፍ በላይ የውጭ ምንዛሪ ባንኮች ሊኖራቸው ይገባል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ባለው ወፍ በረር ምልከታ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የግሉም ሆነ መንግሥት ሊበደረው የሚችለው መቶ ቢሊዮን ዶላር ለሥራ ዝግጁ መሆን አለበት ብሎ ያምናል፡፡

ዶ/ር ይናገር ደሴ እንደነገሩን፣ አንዲት ቁንጽል መመርያ ይዞ ብቅ በማለት የሚመጣ ለውጥ የለም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መታረም የሚገባቸውን ሥራዎች ሁሉ ያለ ምንም ማቅማማት ማረም መቻል አለበት፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንደልባቸው የሚበደሩት ገንዘብ ባለመኖሩ እስከ አሥር በመቶ ጉቦ እየከፈሉ እንደሚበደሩ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ አሁን ባንኮች ከውጭ ባንኮች እየተበደሩ ማበደር ሲጀምሩ ምናልባት ሁኔታዎች ተገልብጠው ባንኮች ተበዳሪዎችን እየለመኑ ማበደር ይጀምሩ ይሆናል፡፡ በባንኮች መካከል ከፍተኛ ፉክክር መፈጠሩም አይቀርም፡፡ በሌላ አነጋገር እስካሁን ባለው ሁኔታ ባንኮች ገንዘብ እንዲያስቀምጡ ነበር ውትወታ የሚያካሂዱት፡፡ አሁን ደግሞ ባለሀብቶች ብድር እንዲወስዱ መወትወት ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡

ሌላው ትንሽ ፈገግ የሚያሰኘው መመርያ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ በቢሮ ወይም በመኖሪያ ቤት ማስቀመጥ መከልከሉ ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ የፌዴራል መንግሥት፣ በትግራይ ክልል የሚገኘውን በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠረውን ገንዘብ እንዴት አድርጎ ነው ወደ ባንክ ሥርዓት የሚያስገባው?

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ የመጀመርያ ሥራቸው መሆን የነበረበት ገንዘብ መለወጥ እንደነበር በተደጋጋሚ ለማሳሰብ ሞክሯል፡፡ ገንዘብ መቀየር ደግሞ የሚያስፈልገው መቶና ሃምሳ ብርን ብቻ ነው፡፡ ለመለወጥ ደግሞ ወይ ቀለሙን ወይም ደግሞ ከላይ ያለውን ቁጥር ትልልቅ እንዲሆን በማድረግ ብቻ መለወጥ ይቻላል፡፡ ወጪው መደበኛ ብር ከማሳተም ብዙም ልዩነት የለውም፡፡

መንግሥት ይህንን ሲያደረግ ብቻ ነው በትክክል በመላው አገሪቱ ያለው ገንዘብ ከየተደበቀበት እየወጣ ወደ ባንክ ሥርዓት የሚገባው፡፡ ይህ ሲደረግ ትግራይ ክልል ያለውም ገንዘብ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ባንክ ሥርዓት ይገባል፡፡

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ገንዘቡ ወደ ባንክ ሲመጣ ገንዘቡን ይዞ የሚመጣው ግለሰብ ገንዘቡን እንዴት እንዳገኘው ማስረዳት ስለሚገደድ ወንጀል ሊፈጸምበት የነበረን ገንዘብ ሁሉ ከባንክ እንዳይወጣ ማድረግ ይቻላል፡፡ በአገራችን ውስጥ በአሁኑ በአሁኑ ጊዜ በገዛ ገንዘባችን ሽብርተኞች እያደረሱብን ያለው ሰቆቃ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ይቻላል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት፣ በሚያስገርም ቸልተኝነት እንደ ኤፈርት ያሉ ለዘመናት የኢትዮጵያን ሕዝብ እስከ አጥንታችን ድረስ ሲግጡን የነበሩ ድርጅቶችን ከሁለት ዓመት በላይ በመታገስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከባድ ሰቆቃ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ ከሕወሓት በኩል የምንሰማው ትርክት ‹‹ዶ/ር ዓብይ ኤፈርትን ከነካ የሱን ጉድ ስለምናወጣ ዶ/ር ዓብይ መቼም ኤፈርትን የመንካት አቅም አይኖረውም›› የሚል ሲሆን፣ እውነት ከሆነ በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡

በጣም የሚገርመው የኤፈርት ገንዘብ ምንጭ የሆኑ ተቋማት አብዛኞቹ ከትግራይ ውጭ በመሆናቸው እዚህ ያፈሩትን ሀብት ነው መልሰው የእኛን ሕይወት ለማመሰቃቀል የሚጠቀሙበት፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጋት አስተዳዳሪ መሪ ሳይሆን አብዮተኛ መሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ የተበላሹ ነገሮች ስላሉ እነዚህን ደረማምሶ አዲስና በዓለም አቀፍ ተሞክሮ ትክክለኛውንና የተሻለውን መንግሥታዊ አሠራር ተግባራዊ የሚያደርግ ጠንካራ አብዮተኛ ያስፈልጋታልና፡፡ ወንጀለኞች ዘግናኝ ወንጀል እየፈጸሙ ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ›› አንታገስም የሚል ቀልደኛ መሪ ኢትዮጵያ አያስፈልጋትም፡፡

ሕግ ለማስከበር ቀጠሮ አይያዝም፡፡ ሕግ መከበር ባለበት ፍጥነት በማንኛውም ጊዜ ያለ ምንም መለሳለስ መከበር አለበት፡፡  

ምዕራባውያን ከፍተኛ አቅም ያላቸውን አገሮች በብልሹ አመራር ሥር እንዲወድቁና፣ ሙስና ተስፋፍቶ የሚዘረፈው ገንዘብ ወደ አገራቸው እንዲገባ በማድረግ ምን ጊዜም የእነሱ ሀብት አቀባይ እንዲሆኑ ተግተው ነው የሚሠሩት፡፡ እኛ የእነሱን ገንዘብ እየተበደርን (ያለ በቂ ዝግጅት) የምናባክን ከሆነ ለሚቀጥለው ትውልድ አስከፊ መከራ ነው የምናወርሰው፡፡ ብድር መበደር ጥሩ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በአግባቡና ብቃት ባለው አመራር ማካሄድ ካልቻልን ባንበደር ይሻላል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አሁን ያለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚመራው መንግሥት፣ ገና እንደ መንግሥት ያልተዋቀረ መንግሥት በመሆኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ማስተናገድ የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብሎ አያምንም፡፡ ዶ/ር ዓብይ ብዙ ሰዎች ሲሉ እንደሰማሁት፣ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ለመላው ኢትዮጵያ ሳይሆን የአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር እየተባሉ ነው፡፡ በመሆኑም በዚች አገር ገና በርካታ መተግበር ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡

የውጭ ብድር ያውም በግለሰቦች ደረጃ ለማስተናገድ ከመሞከራችን በፊት በርካታ ሊሠሩ የሚገቡ ተግባራት አሉ፡፡ በተለይ ተቆጣጣሪው የመንግሥት መሥሪያ ቤት በሰው ኃይልና በሁሉም ጉዳዮች ተጠናክሮ መገኘት አለበት፡፡

በአገራችን የለውጥ ኃይሉ ያለፈውን ሥርዓት እያፈራረሰ ነው ይባል እንጂ፣ ከሕወሓት ከቤተ መንግሥት መነሳት በስተቀር ምንም የመጣ ለውጥ የለም፡፡ ቲም ለማ የሚባለውም ኃይል ተጠናክሮ ሥር ነቀል ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ራሱ በመፍረክረክ ላይ ነው፡፡ የለውጥ ኃይሉ ርዕዮት፣ ግብ፣ ወይም ሊያሳካቸው ያሰባቸው ዓላማዎች ምን እንደሆኑ ማንም አያውቅም፡፡ መጪው ዘመን ደግሞ በውዥንብር የተሞላና በተጨማሪም ምንነቱ የማይታወቅ ምርጫ እየመጣ ነው፡፡ ምርጫው ደግሞ ሁኔታዎችን ወደ አልተጠበቀ መንገድ ሊወስድ ይችላል፡፡

ሃይማኖተኞች ደግሞ እንደሚሉት 2013 ዓ.ም. ከቁጥሩ ጀምሮ በጾምና በጸሎት መታለፍ ያለበት ዓመት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙሩቱ አንድ ላይ ቁጥራቸው አሥራ ሦስት ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ተለይቶአቸው ቁጥራቸው በመጉደሉ ቁጥሩ ተወዳጅ ቁጥር አይደለም፡፡ 2013 ዓ.ም. ክፉ ነገር ይከሰታል ተብሎ የሚታመንበት ዓመት ነው፡፡

በዶ/ር ዓብይ የሚመራው መንግሥትና የብልፅግና አባላት መለያቸው ውጫዊ ማንነታቸውን መገንባት እንጂ፣ ውስጣዊ ማንነታቸውን በዕውቀትና በሳይንስ የመገንባት ብቃት የላቸውም፡፡ ውጫዊ ማንነታቸው ፊታቸውን በማሳመር፣ ልብሳቸውን በማሳመር ትልቅ ሰው ለመምሰል ይሞክራሉ እንጂ፣ በተከታይ ዕውቀታቸውን ለማዳበር አይጥሩም፡፡ ለውጥ መጣ ከተባለ ሁለት ዓመት ተኩል እየሆነ ነው፡፡

እስካሁን የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ያሳተፈ መሠረታዊ ለውጥ እየተካሄደ አይደለም፡፡ ሁኔታዎች ሳይታረሙ የውጭ ዕዳ በገፍ ለመውሰድ ወይም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት ማድረግ በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት በዋናነት ጊዜውን የሚያሳልፈው የለውጥ ሥራ በመሥራት ሳይሆን ከብልፅግና አባላትና ከሕወሓት አባላት ጋር በጭቅጭቅና በንትርክ ነው፡፡ ራሱን ያላጠራ ፓርቲ አገራዊ ውጤት ያመጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ተረስቷል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles