ኩፍኝ የሰው ልጆችን ማጥቃት የጀመረው ከሺሕ ዓመታት በፊት ነው፡፡ ሆኖም በ20ኛው ክፍለ ዘመንም በየዓመቱ በዓለም አንድ ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ይገድላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1954 ስለ ቫይረሱ ምንነት ያወቁት ጆን ኢንደርስና ቶማስ ፔብልስ እ.ኤ.አ. በ1965 ክትባት ቢያገኙም፣ ኩፍኝ ዛሬም በተለይ ለደሃ አገሮች ችግር ነው፡፡
ለኩፍኝ ፍቱን የተባለ ክትባት ቢኖርም በ2015 ብቻ በዓለም 134200 ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ያትታል፡፡ ኩፍኝ ብቻ ሳይሆን ጆሮ ደግፍ (ፐምፕስ)፣ ጉድፍ (ሩቤላ) እና ሌሎችም በቫይረስ የሚከሰቱ ገዳይ በሽታዎች ክትባት ቢገኝላቸውም ኤችአይቪ፣ ወባ፣ ሔፒታይተስ ሲ እና ዚካ ክትባት ያልተገኘላቸው ገዳይ ቫይረሶች ናቸው፡፡
የዓለም ወረርሽኝ ከሆነ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው ኮቪድ-19 ደግሞ ምንነቱ ጥርት ብሎ በጥናት ያልተረጋገጠለት በአፍታ በርካቶችን የሚያጠቃና የሚገድል ቫይረስ ነው፡፡ ሩሲያ ለቫይረሱ ክትባት አግኝቻለሁ ብላ ቀድማ ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ ወደ ምርትም ገብታለች፡፡ ቻይና ከሩሲያ ቀጥላ ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እያመረተች መሆኗን ያስታወቀች አገር ነች፡፡ ነገር ግን አውሮፓና አሜሪካ የክትባቱን ፍቱንነት በጥርጣሬ ዓይተውታል፡፡
የክትባቱ ፍቱንነት በየአገሮቹ ተሞክሮ ተረጋግጧል ቢባልም ለዓለም ሕዝብ በጅምላ ለመስጠት ከማምረት እስከማድረስ ብሎም የሕዝቡ ተቀባይነት ላይ ከዚህ ቀደም እንደተሠሩ ክትባቶች ክፍተት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ የኮቪድ-19 ቫይረስ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ቫይረሶች ለየት እንደሚል፣ ከተከሰተ አጭር ጊዜው በመሆኑም በቂ ጥናትና ምርምር እንዳልተደረገበት፣ የቫይረሱ ባህሪ አጠቃላይ የሰው ልጆችን የመኖር ሕልውና የሚፈታተንና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮችን የሚያስተጓጉል መሆኑን የሚገልጹት የጤና ባለሙያዎች፣ በዚህ ሁኔታ የሰው ልጅ ሊዘልቅ ስለማይችል ከቫይረሱ ራስን ጠብቆ የመኖርን አማራጭ እንዲከተል መምከር ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡
ኮቪድ-19 ሥራን፣ ትምህርትን፣ ንግድን፣ ጉዞንና በአጠቃላይም ይሰውን ልጅ የቀን ተቀን ሕይወት አመሳቅሏል፡፡ ሰዎች በቤታቸው ታጥረው እንዲቆዩ፣ ግድ ከሆነ ከቤት እንዳይወጡ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ይህ ለሰው ልጆች አመቺ አልሆነም፡፡ ያደጉ አገሮች በሰዎች መንቀሳቀስ ላይ ሙሉ ለሙሉ ገደብ ቢጥሉም፣ ዘላቂ ማድረግ ግን አልተቻለም፡፡
ቀስ በቀስ ሰዎች ወደ ሥራ እንዲሄዱ፣ ተማሪዎችም በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ቫይረሱን መቆጣጠር ካለመቻሉ አንፃር የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም፣ ቫይረሱን በመቆጣጠር የዕለት ተዕለት ክንውንን መፈጸም ምርጫ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ዜጎቻቸው ላይ ሙሉ ገደብ አልጣሉም፡፡ ተማሪዎች ቤት እንዲቀመጡ ቢያደርጉም ሕዝባቸው በልቶ ማደር አለበትና ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የቫይረሱ ሥርጭት ከሌሎች አኅጉሮች ሲነፃፀር ትንሽ ቢሆንም፣ ቫይረሱ ውስጥ ለውስጥ እየደራ ሊሆን እንደሚችል ፍርኃትና ሥጋት አለ፡፡
ኢትዮጵያ ዜጎቿን ሙሉ ለሙሉ ባለመዝጋት የጥንቃቄ ዕርምጃ እየተወሰደ እንዲሠራ ካደረጉ አገሮች ተርታ ናት፡፡ ሆኖም በሕዝቡ ዘንድ ፈር የለቀቀ ቸልተኝነት ይስተዋላል፡፡ ቫይረሱ ኢትዮጵያ ተገኘ በተባለበት መጋቢት 2012 ዓ.ም. እና ለተከታታይ ሁለት ወራት ያህል የሥርጭቱ መጠን ከተመረመረው አንፃር ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ሥርጭቱ በመገስገሱ ታማሚዎች ቤታቸው የሚያገግሙበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ቅጠል ከረገፉት ከጣሊያን፣ ከብራዚል፣ ከአሜሪካና ሌሎች አገር ሕዝቦች ሊሚሩ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል የነበረ ቢሆንም፣ ብዙ አልተቀሰመም፡፡
ከኮቪድ-19 ጋር እንዴት መኖር ይቻላል?
ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት የተለያዩ ምርምሮች እየተካሄዱና በሩሲያና በቻይና ተገኙ የተባሉትም ወደ ምርት የገቡ ቢሆንም፣ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ለኮቪድ-19 ፍቱን ክትባት ማግኘት እንደሚከብድ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ አልበርት የቫይረስ ተመራማሪው ዴቪድ ማርቻንት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ቫይረሱ ብርቅዬ ሆኖ ከሰው ጋር ይኖራል፣ እኛ የምንዋጋው አይደለም፡፡ ከቫይረሱ ጋር የመኖር ዘዴን መማር፣ ጉዳቱን መቆጣጠርና የታመሙትን መንከባከብ አለብን›› ሲሉም ይመክራሉ፡፡
‹‹ቫይረሱን የምንዋጋው አይደለም›› የሚሉት ተመራማሪው፣ የቫይረስ መጠኑን የሚቀንሱ ወይም ሴል ውስጥ እንዳይገባ የሚያስችሉ መድኃኒቶች ሊሠሩ ይችላሉ የሚል እምነት ቢኖራቸውም፣ ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል፣ ቫይረሱን መገንዘብ የዕለት ተዕለት ሕይወት አካል መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ሔልዝላይን በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ መሠረታዊው የኮቪድ-19 መከላከያ በቀደመው አኗኗር ዘይቤ ላይ መሠረታዊ የባህሪ ለውጥ ማድረግ ነው፡፡ ፍቱን ክትባት አግኝቶ ለዓለም ሕዝብ ተደራሽ ማድረግ በቅርቡ የሚሆንም አይደለም፡፡ ብዙ ምርመራ፣ ቅኝትና ከታማሚ ጋር ንክኪ ያላቸውን ያማከለ ሥራ ቢሠራም፣ ይህ ብቻ መፍትሔ አይሆንም፡፡ መፍትሔው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ ርቀትን መጠበቅ፣ እንዲሁም እጅን በውኃና በሳሙና መታጠብ ነው፡፡ እነዚህ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉና የተፈተኑ መንገዶች ናቸው፡፡