የሟቾች ቁጥር እስከ ዓርብ 758 ደርሷል
የጤና ሚኒስቴር ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በለቀቀው የኮሮና ወረርሽኝ መረጃ፣ በ24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 18,766 የላቦራቶሪ ምርመራ 1733 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 48,140 መድረሱን የገለጹት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ በዕለቱ የ13 ሰዎች ሕይወት በቫይረሱ ምክንያት ማለፉን ተከትሎ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 758 መድረሱን ገልጸዋል።
እስከ ነሐሴ 22 ቀን ድረስ ለ850,236 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ እስከ ዓርብ ቫይረሱ ያለባቸውና ሕክምና እየተከታተሉ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር 29,965 ነው፡፡ የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚሳየው፣ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 17,415 ሲደርስ፣ 357 ሰዎች በፅኑ ሕሙማን ክፍል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ናቸው።
ኮቪድ-19 በወረርሽነት ዓለምን ካካለለ ስምንት ወር ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ወራት ሕዝበ ዓለም ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅ፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ እንዳይያዝ የጤና ባለሙያዎችና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ ተቋማት ማስገንዘቢያዎችን ከመስጠት ችላ ያሉበት ጊዜ አልነበረም፡፡
ኮቪድ-19 የሚተላለፍበት መንገድ አስመልክቶ እስካሁን ያለው አቋም፣ በሽታው ከሕመምተኛው አፍንጫ ወይም አፍ በሚወጣ ጥቂት ፈሳሽ አማካይነት የሚተላለፍ መሆኑ ነው፡፡ ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ሲያስነጥስም ሆነ ሲተነፍስ ወደ ሌሎች ከማስተላለፍ ባለፈ፣ ከሕሙማን የሚወጣ ፈሳሽ ያረፈበትን ቦታ የነኩ ሰዎችም በበሽታው በቀላሉ ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸው ቅርርብ ከአንድ ሜትር በላይ መሆን አለበት የተባለውም በሽታው በትንፋሽ ስለሚተላለፍ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ቫይረሱ በአየር ውስጥ ሳይሆን በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የመተንፈሻ አካላት ከወጡ ፍሳሾች ጋር በሚኖር ንክኪ ብቻ የሚተላለፍ መሆኑን ነው፡፡
ይሁን የቅርብ መረጃዎች የኮሮና ቫይረስ በአየር ላይ የመተላለፍ ዕድሉ ሰፊ መሆኑ እየገለጹ ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት በቫይረሱ የመጋለጥ ወይም ያለመጋለጥ ዙርያ የቀረቡ ጥናቶች ላይ እየመከረ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በአየር ላይ ቫይረሱ በመቆየት ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
ተተኳሪ ጉዳዮች
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት አገላለጽ፣ ኮሮና ቫይረስ የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችን የያዘ የቫይረስ ቤተሰብ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ በሰዎችና በእንስሳት ላይ በሽታን ያስከትላል፡፡ በሰዎች ላይ የሚከሰተው ኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ከተራ ጉንፋን እስከ ከፍተኛ የመተንፈሻ አካል ችግር የሚያደርስ ነው፡፡