ተጎሳቁለዋል፡፡ ጉዳታቸውን ሰውነታቸው ይናራል፡፡ ዕድሜያቸው ወደ ሰባዎቹ የሚጠጋው አቶ ገና አማረ አላገቡም፣ አልወለዱም፡፡ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ መሬት እየተኙ እንደኖሩ ይናገራሉ፡፡ ለዕለት ጉርስ የሚሆናቸውን ገንዘብ ሳር እየሸጡ ቢያገኙም፣ ከ40 ዓመታት በላይ ያሳለፉት ቤት ውስጥ አልነበረም፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ልብስም ሸራም እየሰጧቸው ክረምትና በጋን ፀሐይና ዝናብን በሸራቸው ውስጥ ለዓመታት አሳልፈዋል፡፡ በደቡብ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ጂንካ አልጋ ቀበሌ ነበር ያገኘናቸው፡፡ ስናገኛቸው አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ብቻቸውን ተቀምጠው እየተከዙ ነበር፡፡ አቶ ገና የሚጎበኛቸው ልጅ የላቸውም፡፡ ከጎናቸው የምትሆን ባለቤትም እንዲሁ፡፡ ይህ ደግሞ ሕይወትን በብቸኝነት እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡
ያለፉት ሁለት ዓመታት ግን ለእሳቸው መልካም ነበር፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ሒደቱ በተጨማሪ ወደ ማኅበረሰቡ በመውረዱ ተጠቃሚ ካደረጋቸው ሰዎች አንዱ ሆነዋል፡፡
አቶ ገና ለዓመታት ከኖሩበት የሸራ መጠለያ ወጥተው ቤት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ‹‹ማንም ያላየኝን ዩኒቨርሲቲው ነው ያየኝ፡፡ ከማረፊያዬ ባለፈ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ዘይትና የመሳሰሉትን ቀለብ ይሰጡኛል፡፡ ለዚህም አመስግኜ አልጨርስም፡፡ አሁን ከተወለድኩ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፤›› ይላሉ፡፡
አቶ ገና ቤት ማግኘታቸው ብቻ አይደለም ደስታቸው፡፡ ቢያንስ በተወሰነ ጊዜ ቀለብ ለመስፈር የሚመጡ ያገኟቸዋል፣ ያዋሯቸዋል፡፡ ይህ ለእሳቸው ሌላው ደስታ ነው፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት መስጠት ከጀመረ ዘንድሮ ሦሰት ዓመት ጨርሷል። በነዚህ ዓመታት ውስጥ የችግረኞችን ጎጆ ከመዳሰስ ባለፈ በዞኑ ያሉ ወረዳዎችንና የተለያዩ አካላትን ጎብኝቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎቹ ጋር በመሆን አቶ ገናን እና ሦስት አቅመ ደካሞችን ከችግር አንስቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ፣ ‹‹የሠራነው ሥራ ሐሳብ ካልሆነ በስተቀር የሚያኩራራ አይደለም፡፡ በአካባቢያችን በርካታ አቅመ ደካሞች አሉ፡፡ ሥራችንም የሚቀጥል ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
በመማር ማስተማር ሒደቱና በምርምር ጉዞው ከተቋቋመበትና ካገለገለበት ዕድሜ አንፃር በርካታ ሥራዎችን ያከናወነው ጂንካ ዩኒቨርሲቲ፣ በማኅበረሰብ አገልግሎቱም የሚበረታታ ሥራ ማከናወኑን ሪፖርተር በቦታው ሄዶ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
አቶ አርጋቸው ቦቸና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ መምህርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በ2010 ዓ.ም. የተቋቋመው ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማሩን ሒደት ከጀመረ ሦስት ዓመት ቢሆነውም፣ የማኅበረሰብ አገልግሎትና ምርምር ተግባራትን የጀመረው ግን በ2011 ዓ.ም. እንደሆነ ያወሳሉ፡፡ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጀት ባለመመደቡ ሥራው ዘግይቶ መጀመሩንም ያክላሉ፡፡
በጀቱ ከተመደበ በኋላ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ፣ የትኩረት መስክ ልየታ በማከናወንና ለተለያዩ አካላት የአቅም ግንባታ በማድረግ ሰፊ ሥራዎችን ማከናወን ችለናልም ብለዋል፡፡
ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ለተቋማትና ለተለያዩ ወረዳዎች መረጃን በተደራጀ መልኩ ለማስቀመጥ ይረዳ ዘንድ የ300 ኮምፒዩተርና የ75 ፕሪንተር ድጋፍ ማድረግ፣ ከተማዋ የብዙ ቱሪስቶች መናኸሪያ ከመሆኗ አንፃር ለሆቴል አስተዳዳሪዎች፣ ለአስጎብኚዎች፣ ለምግብ አዘጋጆች፣ ለእንግዳ ማረፊያ አገልግሎት ሰጪዎችና ለተለያዩ አካላት ሥልጠና መስጠት፣ ለ35 የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሠረታዊ የኮምፒውተር ችሎታን ማስገንዘብና የ950 ኮምፒውተሮች ድጋፍ ማድረግ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የመጽሐፍት እጥረት በሰፊው ስለሚታይ በኮምፒውተሮቹ ላይ መጽሐፍትን በመጫንና ለተማሪዎች የመጽሐፍ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ማዕከል ላይ ካለው ተማሪ ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ የሥራዎቹ አካል ናቸው፡፡
‹‹አንድ ቀን ለሕዝቤ›› በሚል መሪ ቃልም ለሦስት አቅመ ደካሞች ቤት ገንብቶ ማስረከብ፣ የከተማዋን አረንጓዴ ልማት ማስፋፋት፣ በገበያዎች አካባቢ የመፀዳጃ አገልግሎቶች መክፈት፣ ትምህርት ቤቶችን ማደስ እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሳኒታይዘር ማምረትና የመመርመሪያ መሣሪያዎችን መግዛት ይጠቀሳሉ፡፡ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የኮሌራ በሽታና የጎርፍ አደጋ በተከሰተ ጊዜም ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ አድርጓል፡፡
እንደ አቶ አርጋቸው፣ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ የተከናወኑትን ሥራዎችም እንደ ሞዴል የተመረጡ ቦታዎች ላይ በመገኘት ሪፖርተር ለማየት ችሏል፡፡
የመጀመርያ መዳረሻችን የነበረው በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ በሆነው የበና ፀማይ ወረዳ ነው። የበና ፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሞ በዛብህ ይባላሉ፡፡ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመምጣቱ በፊት ምን እየታሰበ ነበር? ከመጣስ በኋላ ምን ዓይነት ውጤቶች ተገኝተዋል? የሚለውን ገልጸውልናል፡፡
ደቡብ ኦሞ ዞን ድንበር አካባቢ ከመሀል ከተሞች በርቀት የሚገኝ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች አርብቶ አደሮች ናቸው፡፡ በትምህርትም ኋላ ቀር ኅብረተሰብን ያቀፈ አካባቢ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪ የትምህርት ዕድል በሰፊው አላገኘም፡፡ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው ወደዚህ ሲመጣ ያልተማረው ማኅበረሰብ ትምህርቱን የማግኘት እንዲሁም ስለ ትምህርት ዕውቀት እንዲጨብጥ አድርጓል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ወደ ዞኑ ሲመጣ፣ ዕድሉ ከተገኘ ከሥር የተማረ የሰው ኃይል እንፈጥራለን ብለን ነበር፡፡ በዚህም መሠረት እኛ እንደ ወረዳ በርካታ በመንግሥት ሥራም ሆነ ከመንግሥት ሥራ ውጪ ያሉ ሰዎችን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ዕድሉን አግኝተው እንዲማሩ አድርገናል፡፡
የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ማሟላት ላልቻሉ የአርብቶ አደር ልጆች ገንዘብ እየከፈልን በዩኒቨርሲቲው እንዲማሩ ዕድል አመቻችተናል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ስምንት የአርብቶ አደር ልጆችን ከፍለን እያስተማርን እንገኛለን፡፡ የአመራር አካላት ትምህርታቸውን ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ እንዲያሻሽሉ አድርገናል፡፡ ይኼም ለእኛ አጠቃላይ የተማረን የሰው ኃይል ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ አቀፍ እንቅስቃሴው ላይ የወረዳውን አቅም ከማጎልበት አኳያ ትልቅ ሚናም ተጫውቷል ይላሉ፡፡ ትኩረቱንም ከላይ ላለው የተማረ ክፍል ብቻ ሳይሆን ከታች ለሚመጣው ትውልድ ጭምር በማድረግ በወረዳው በሚገኙ ሁለት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር ድጋፎች አድርገዋል፡፡ እንዲሁ ለመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ለሚሠሩ ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ለወረዳው የ18 ኮምፒውተሮችም ተበርክቷል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር የኔትወርኪንግ ሥርዓት በመዘርጋት ወረዳን ከወረዳ ጋር ለማገናኘትና ጥናት ለመሥራት እየተሠራ ነው፡፡ ‹‹የጥናት ቦታዎችን መርጠናል፡፡ በከተማው አቅራቢያ የሚገኘው ማኅበረሰብም ለጥናት ይረዳ ዘንድ 36 ሔክታር መሬት አዘጋጅቶ ለዩኒቨርሲቲው በነፃ ለማስረከብ ዝግጅት ላይ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ደሞ ከዩኒቨርሲቲው ጉዞ ምንጠብቀው ነገር አለ ይላሉ። ሌሎች ቅርንጫፎችን ቢከፍትና ለየወረዳው በቅርበት ተደራሽነቱን ቢያሰፋ፣ ወረዳው ውስጥ የሚገኙትንና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የበኔ፣ ፀማይና ብራይሌ ብሔረሰቦች መታደግና በኢኮኖሚ የማኅበረሰቡን አቅም ከማጎልበት አኳያም ብዙ ሚና ቢጫወት የሚለውን ያነሳሉ፡፡
ቀጣይ መዳረሻችን በጂንካ ከተማ የሚገኘው የጂንካ ሚሊኒየም ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በ2001 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ ትምህርት ቤት ሰፊ ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡ ነገር ግን የያዘው ጥቂት ክፍሎችን ነው፡፡ እዚያ በደረስንበት ሰዓት ቅጥር ግቢው እየታረሰና የተለያዩ ዘሮችም እየተበተኑ ነበር፡፡ ከዘጠነኛ እስከ አሥራ አንደኛ ክፍሎችን የያዘው ይኸው ትምህርት ቤት 935 ተማሪዎች አሉት፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ተማሪዎች ያሉት ስምንት ክፍሎች ብቻ ናቸው፡፡ የክፍል እጥረት ለጂንካ ሚሊኒየም ትምህርት ቤት ሥጋት እንደሆነ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ካሳሁን ኃይሉ ይገልጻሉ፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት ከክፍል እጥረት በተጨማሪ የኮምፒውተር፣ የላይብረሪና የላቦራቶሪ ቁሳቁሶች እንዲሁም የመጽሐፍት እጥረት በዋነኝነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የትምህርት ቤቱ ችግሮች ነበሩ፡፡ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ ነበር የሚሉት አቶ ካሳሁን ‹‹ነገር ግን ከ2011 ዓ.ም. በኋላ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ሀብት በመስጠት እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉልን አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩ ሒደት እንዲፋጠን 50 ኮምፒውተሮችን በመግዛትና መጽሐፍት በመጫን ለተማሪዎችና ለአስተማሪዎች ሥልጠና በመስጠት የትምህርት ሒደቱን እንዲቀላጠፍ አድርጓል። ተማሪዎች ላይብረሪ ውስጥ የሚጠቀሙበትን 20 ጠረጴዛ፣ 50 የተማሪ ወንበርና ጠረጴዛ የመጽሐፍ መደርደሪያዎች፣ 500 የሚጠጉ ማጣቀሻ መፅሐፍት አበርክቷል። ለእያንዳንዱ ቢሮ መቀመጫና ጠረጴዛ፣ ለቢሮ የሚያገለግል ሁለት ኮምፒውተርና ፕሪንተር፣ 152 ሺሕ ብር የሚያወጣ የማባዣ ማሽንም አበርክቷል።
እንደ አቶ ካሳሁን፣ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው መሠራቱ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል። ከክፍል እጥረት ውጪም አብዛኛው ችግራቸው መቀረፉንም ገልፀዋል።
ሁሉም አካል እንደ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሁላ ለትምህርት ትኩረት ቢሰጥ ጥሩ ፍሬን ማግኘት እንደሚቻል አቶ ካሳሁን ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው በ2011 ዓ.ም. የደቡብ ኦሞ ባህል ፌስቲቫልን ጀምሯል። የፌስቲቫሉ ዓላማ በደቡብ ኦሞ ያሉ 16 ብሔረሰቦች ቱባ የሙዚቃ፣ የምግብ እንዲሁም የዕደ ጥበብ ባህል ስላላቸው፣ ይህን ለተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ ማምጣት ነው።
የቀይ አፈር ወረዳ ነዋሪውና የወረዳው የቀድሞ አስተዳዳሪ አቶ መለስ ማያ በዩኒቨርሲቲው ሥራ በጣም እንደተደሰቱ ገልጸውልናል፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲው መከፈቱ ለብዙ ዘመናት በማኅበረሰቡ የነበሩ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንትም ወደ ማኅበረሰቡ ዝቅ ብለው በመግባትና የነበሩ ችግሮችን በመፍታታቸው አመስግነዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ ዩኒቨርሲቲው እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ከክልሉ ጤና ኢንስቲትዩት የጂንካ ቅርንጫፍ ላቦራቶሪ ጋር በመተባበር ሳኒታይዘር ማምረት ጀምሯል።
የሳኒታይዘር ማምረቻው የሚገኘው በኢንስቲትዩቱ ላቦራቶሪ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው። የላቦራቶሪው ተወካይ አቶ መስፍን ታምራትና የጥራት ቁጥጥር ኦፊሰር አቶ ወንድምነህ መርሻ ስለሳኒታይዘር ምርት ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
የላቦራቶሪው ኃላፊዎች፣ ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሳኒታይዘር እያመረቱ፣ ጥሬ እቃም ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ እጠቀረበላቸው መሆኑን ነግረውናል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ከኬሚስትሪ ዲፓርትመንት ባለሙያዎችም በትብብር እየሠሩ ነው፡፡ 1,000 ሊትር ሳኒታይዘር ለማዘጋጀት አራት ቀን እንደሚፈጅባቸውና ጥራቱ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መሥፈርት ማሟላቱን አረጋግጠው እንደሚያከፋፍሉ ገልጸዋል፡፡ ኦሞ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሳኒታይዘር፣ በመጀመርያው ዙር የተመረተው 2,000 ሊትር በነፃ ለኅብረተሰቡ ታድሏል። በቀጣይ የተመረቱትም በተመጣጣኝ ዋጋ እየተከፋፈሉ ይገኛሉ።
ዩኒቨርስቲው ከጂንካ ቅርንጫፍ ጤና ላቦራቶሪ ጋር በመተባበር አምስት ሚሊየን ብር ያህል በማውጣት የኮቪድ-19 መመርመርያ ማሽን በመግዛትና ለዚህ የሚሆኑ ግንባታዎችን በማከናወንና ያሉትንም በማደስ ሥራ ሊያስጀምር ነው፡፡ የማሽኑ ሥራ ሲጀምር በ24 ሰዓት ውስጥ ከ500 በላይ ሰዎችን ለመመርመር እንደሚያስችል ተገልጿል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው በ2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. ለአራተኛ ጊዜ ተማሪዎችን ይቀበላል። ዩኒቨርሲቲው አራት ኮሌጆችና 14 ዲፓርትመንቶች አሉት። አራቱ ኮሌጆች የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ፣ ማኅበረሰብ ሳይንስ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም የግብርና ሳይንስ ናቸው። የተፈጥሮ ሳይንስና የግብርና ሳይንስ ኮሌጆች እያንዳንዳቸው አራት ዲፓርትመንቶች አሏቸው። የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ እያንዳንዳቸው ሦስት ዲፓርትመንቶች አሏቸው፡፡ በ2013 ዓ.ም. አሥር ዲፓርትመንቶችን ለመጨመር ዝግጅት በማድረግ ላይም ይገኛል።