ኢትዮጵያን ከድህነት፣ ከኋላቀርነትና ከዘርፈ ብዙ ችግሮች ማላቀቅ የሚገባቸው ልጆቿ በቅራኔ ተወጥረው ስለሰላም ማሰብ ይከብዳል፡፡ ይሁንና በዚህ ፈታኝ ጊዜ ኢትዮጵያ ደፋርና የመጣው ይምጣ የሚሉ ልጆች ያስፈልጓታል፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገራቸው ህልውና የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነትና በፍትሐዊነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር በግንባር ቀደምትነት መሠለፍ አለባቸው፡፡ ይህ ጉዞ የሚጀምረው የተኮራረፉ ወገኖች ለምን በጠረጴዛ ዙሪያ የሚነጋገሩበት ዕድል አያገኙም? መሠረታዊ የሆነ ቅራኔ ሳይኖር በመለስተኛ ችግሮች ለምን የጠላትነት ስሜት ይፈጠራል? ጥያቄዎች ያሉዋቸው ወገኖች ለምን በአግባቡ አይስተናገዱም? በሠለጠነ መንገድ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ ሐሜትና አሉባልታ ለምን ይቀድማሉ? ወዘተ. በመሳሰሉት ላይ መነጋገር የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ቤታቸው እንደሆነች በመግባባት፣ የዘመናት ችግሮቿን ለመፍታት መረባረብ ይጠቅማቸዋል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡
ሁሌም የተሻለ መንገድ መኖር እንዳለበት ይታመናል፡፡ የተሻለ መንገድ እንዲኖር ግን መተማመን የግድ ነው፡፡ ‹‹በዚህ ዘመን በዓለማችን ዋነኛውና ውዱ ነገር ነዳጅ፣ አልማዝ፣ ወይም ወርቅ ሳይሆን መተማመን ነው፤›› እንደሚባለው ሁሉ፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ቀና ጎዳና ለማስገኘት መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ይህ መተማመን መምጣት ያለበት ከዘረኝነት፣ ከቂም በቀል፣ ከሴራ፣ ከክፋትና ከዕብሪት በመላቀቅ ቅን በመሆን ብቻ ነው፡፡ ቅንነት ማለት ሞኝነት ወይም የዋህነት ተብሎ መተርጎም የለበትም፡፡ ቅንነት የብልሆችና የአስተዋዮች ፀጋ ነው፡፡ ይህ ፀጋ በዕውቀትና በክህሎት የሚመራ ከሆነ መተማመን አይከብድም፡፡ የበዳይና የተበዳይ ትርክትን ወደ ጎን ብሎ፣ እንደ ሠለጠነ ሰው በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየትና መደራደር ባህል ሊሆን ይገባል፡፡ ልዩነትን አክብሮና ዕውቅና ሰጥቶ በእኩልነት መንፈስ መነጋገር መቻል ሊያዳግት አይገባም፡፡ ሕጋዊነትን በሕገወጥነትና በሥርዓተ አልበኝነት ላይ የበላይ በማድረግ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዝ ጨዋነትና ባህሪ በመላበስ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ አላስፈላጊ ሽኩቻዎችንና ጥላቻዎችን በማስወገድና ከመሰሪ ራስ ወዳድነት በመላቀቅ ወደፊት መራመድ ይቻላል፡፡ በዚህ መንፈስ ሁሌም የተሻለ መንገድ እንዳለ ለሕዝብ ማረጋገጥ ይገባል፡፡
የሕዝብ ፍቅርና ክብር የሚገኘው ለአገር የሚጠቅምና በታሪክ የሚታወስ ተግባር ማከናወን ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ የግል ፍላጎትንና ዓላማን በብሔርና በእምነት ጭምብል ጋርዶ፣ አገር ማተራመስና ሕዝብን ግራ ማጋባት መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ለነገሩ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩ ኃይሎች ዋነኛ ፍላጎት መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ማጋበስ፣ ወደፊት ሊጠቅም የሚችል የፖለቲካ ኃይልን በግርግር ሥልጣን ላይ ለማውጣት መረባረብ፣ በነጋ በጠባ ሴራ መጎንጎን፣ ተቃራኒ ተብሎ የሚታሰብ ወገንን ስም ማጥፋትና ቢቻል ማስወገድን ጭምር ያካተተ ዘመቻ ማድረግ ነው፡፡ ችግርን ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ ጉልበት ላይ ማተኮርና ማስፈራራት በዚህ ዘመን አይታሰብም ቢባልም፣ በግልጽ በአደባባይ የሚታየው ግን ይኼ እውነታ ነው፡፡ ከትናንት የተበላሹ ድርጊቶች መማር ያቃታቸው አንዳንድ ወገኖች፣ ከኋላ ያሠለፉትን ኃይል ተማምነው ሲያስፈራሩና መንግሥትን ጭምር አላሠራ ሲሉ በጣም ይደንቃል፡፡ ትናንት ለነፃነትና ለእኩልነት እንጮህ ነበር ሲሉ የነበሩ ዛሬ የጉልበተኝነትን መንገድ ሲያያዙት ያሳፍራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጉዞ የት ያደርሳል ቢባል መልሱ የትም ነው፡፡ ለግል ክብር፣ ጥቅምና ዝና ሲባል የጋራ እሴቶችን መናድ ከሕዝብ ጋር ያጣላል፡፡
‹‹አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ›› እንዲሉ፣ ፋታ የማይሰጡ የአገር ትልልቅ ጉዳዮችን ወደ ጎን ብለው ጥቃቅን ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ አፍለኞች እየበዙ ነው፡፡ በተለይ በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ የሚርመሰመሱ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ ከአገር ደኅንነትና ጥቅም በላይ በመረማመድ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ የረባ አገራዊ አጀንዳ ሳይኖራቸው በአጋጣሚ ራሳቸውን ያገዘፉ ግለሰቦች፣ ሚዲያውን ጭምር የጥላቻና የቂም በቀል መወጫ አድርገውታል፡፡ የወጣቶችን ደካማ ጎን በመጠቀም በስሜት ኮርኳሪ ቅስቀሳዎች፣ አገሪቱን ከዕለት ወደ ዕለት ሰላምና እረፍት እየነሷት ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅም አማራጭ ሐሳብ ሳያቀርቡ፣ በሌሎች ሐሳቦች ላይ በመንተራስ የጥላቻ ቅስቀሳ ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ መንግሥት ሲሳሳት በበሰለ ሐሳብ መተቸት፣ አላስፈላጊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ወቀሳ ማቅረብና ትክክለኛውን መስመር ማስያዝ ሲገባ፣ የሚቀድመው ስድብና ዛቻ ሆኗል፡፡ በአገሪቱ ሐሳብ የነጠፈ ይመስል ልዩነትን ማክበር ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁባቸው መልካም ሥነ ምግባሮችና እሴቶች እየተጣሱ፣ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ አሳፋሪ ስድቦችና ዘለፋዎች ይሰማሉ፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ አጀንዳዎች እየተመዘዙ፣ ከዕለት ወደ ዕለት ወደ ቀውስ መንደርደር ልማድ ሆኗል፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ ነገሮች ከሕዝብ ጋር ያቆራርጣሉ፡፡
አንድ ሰው የፈለገውን ሐሳብ በነፃነት የማራመድ ተፈጥሯዊ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ደግሞ ለሌሎችም ጭምር እንደሚሠራ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ አገር ወደ ተሻለና የሚያስደስት ሥርዓት መንደርደር የምትችለው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች እንዲከበሩ አንዱ ለማኝ ሌላው ተለማኝ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም ይህንን ሥርዓት በጋራ ለማቆም በልዩነት ውስጥ የጋራ የሆነ ነገር መፍጠር ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች የሚደምቁበት ማዕድ ስለመሆኑ የጋራ ግንዛቤ ሊኖርም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ አንዱ ጉልበተኛ ሌላው ተንበርካኪ፣ አንዱ ሕግ አክባሪ ሌላው ሕገወጥ ለመሆን መሞከር ከባድ ጥፋት ያስከትላል፡፡ በሌላ በኩል ሕዝብ አገለግላለሁ የሚል ማንም ወገን መጀመርያ ራሱን ከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከሴራና ከቂም ነፃ ማውጣት አለበት፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ ራስን አጉል ነፃ አውጪና አርበኛ በማድረግ፣ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ውስጥ መገኘት ፀቡ ከሕዝብ ጋር ነው፡፡
በተደጋጋሚ እንደምንለው ከምንም ነገር ላይ መቅደም ያለበት የአገር ህልውና ነው፡፡ የአገር ህልውና አስተማማኝና ዘለቄታዊነት የሚኖረው በልዩነት ውስጥ መኖርን መልመድ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የአገርን ህልውና ከፓርቲ በላይ መመልከት የሚችል ሰብዕና የተላበሱ አመራሮች ሲኖሩ የሕዝብ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ከሥልጣን በላይ አገርን የሚያስቀድሙ አመራሮች የሕዝብ አክብሮት ይቸራቸዋል፡፡ ሕዝብ ድጋፍ የሚሰጠው ፓርቲ ሁሌም የሚጨነቀው ለአገር ህልውና ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በሕዝብ ስም መነገድ፣ ሥልጣንን ለግላዊና ለቡድናዊ ጥቅም ብቻ መጠቀምና ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ መገኘት ክብር ያሳጣል፡፡ ሁለት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕዝብ ዘንድ የሚቀርቡት የተሻለ ድጋፍ ለማግኘት ነው፡፡ ይህ ድጋፍ የሚገኘው ደግሞ የተሻለ ብቃት፣ ሥነ ምግባርና ለሕዝብ የሚጠቅም ምርጥ ሐሳብ ይዞ መገኘት ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ቁመና ላይ መገኘት የሚገባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራት መሆን የግድ ይላቸዋል፡፡ ዴሞክራት ደግሞ በልዩነት ውስጥ መኖር የሚችልና ከሕገወጥነት የራቀ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ተቀባይነት ያለው ባህሪ በመላበስ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት የሚቻለው፣ ልዩነትን በማክበርና የሕዝብን የልብ ትርታ በማዳመጥ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ በቃላት ጦርነት ሳይሆን በተግባር እንደሚመዝን መገንዘብ ይገባል፡፡ የኋላ ታሪክንም እየመረመረ የዛሬውንም ሁኔታ እንደሚገመግም ማጤን ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፉና ደጉን አብሮ በማሳለፍ ለረዥም ዘመናት አኩሪ የሆነ ታሪክ አለው፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋ ባለቤት የሆነን ሕዝብን በአልባሌ ነገሮች በመከፋፈል፣ የድህነትና የኋላቀርነት መዘባበቻ ማድረግ ነውር ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና ማማ ማድረግ እየተቻለ፣ ይህንን ምስኪን ሕዝብ ሁልጊዜ ችግር ውስጥ መክተት ወንጀል ነው፡፡ ፖለቲከኞችና በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ስም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችም ሆኑ ሌሎች፣ የየዕለቱን ድርጊታቸውን ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ አካሄዷ ካልተስተካከለ በርካታ ችግሮች እየተጋረጡ ነው፡፡ እንኳንስ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የአገር ህልውና አጠራጣሪ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አገርን በወጉ መምራት የተሳናቸው ወገኖች፣ ዛሬ ተነስተው በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና በፌዴራሊዝም ስም ሲማማሉ ይገርማል፡፡ ከአገር ህልውና በላይ ለሥልጣናቸው ሲሟሟቱ እንዳልነበር፣ ዛሬ ተነስተው የአዞ እንባ ሲያፈሱ እንቆቅልሽ ይሆናሉ፡፡ ለሰላምና ለመረጋጋት መጥፋት እጃቸውን አስረዝመው የሚተጉ ኃይሎች፣ ራሳቸውን ከደሙ ንፁህ በማድረግ ሲቅበጠበጡ ያስደምማሉ፡፡ መሆን የነበረበት ግን ጥፋትን አምኖ መታረምና ለሕግ የበላይነት ተቆርቋሪ መሆን ነበር፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደምና ራስን ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ ይተፋቸዋል፡፡ ምክንያቱም ማታለል አይቻልምና!