Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናአሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ዕርዳታ በከፊል በማቋረጥ ጫና ለመፍጠር መወሰኗ ተሰማ

  አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ዕርዳታ በከፊል በማቋረጥ ጫና ለመፍጠር መወሰኗ ተሰማ

  ቀን:

  አሜሪካ ታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ኢትዮጵያ በያዘችው አቋም ላይ ጫና ለማሳደር በማሰብ፣ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ በከፊል ለማቋረጥ መወሰኗ ተሰማ።

  የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዋና ኃላፊ ማይክ ፖምፒዮ በተጠናቀቀው ሳምንት ውስጥ ውሳኔውን እንዳሳለፉ ጠቅሶ መረጃውን ያወጣው፣ ፎሪን ፖሊሲ የተባለ ዲፕሎማሲያዊ መረጃዎችን የሚከታተል የመረጃ አውታር ነው። 

  ኃላፊው ባፀደቁት በዚህ ውሳኔ ምክንያትም ኢትዮጵያ እስከ 130 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ልታጣ እንደምትችል መረጃው ያመለከተ ቢሆንምስለ ውሳኔው አስተያየት የሰጡ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግን እንዲቋረጥ የተወሰነው የገንዘብ ድጋፍና ዕርዳታ ዝርዝር ላይ ውሳኔ ባለመሰጠቱ የገንዘቡ መጠን 130 ሚሊዮን ዶላር ሊያንስ እንደሚችል መግለጻቸውን መረጃው አመልክቷል። 

  በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ዕርዳታ ከሚቋረጥባቸው የትብብር ዘርፎች መካከል የፀጥታና ደኅንነት ዘርፍ አንዱ ሲሆን፣ በዚህም ዘርፍ ሽብርን የመከላከል፣ ወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና ትብብር፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የመከላከልና የተለያዩ የልማት ዘርፎችን ለማገዝ የሚሰጡ የገንዘብ ድጋፎች እንደሚሆኑ መረጃው አመልክቷል።

  ነገር ግን የሰብዓዊ ዕርዳታ፣ የምግብ ዕርዳታና የጤና ዘርፍ በተለይም የኮሮና ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቋቋም የሚያስችሉ ድጋፎች እንደማይቋረጡ መረጃው አመልክቷል። 

  ሪፖርተር መረጃውን በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ለኅትመት እስከገባንበት ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻለም። 

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዲፕሎማቲክ ምንጮች በበኩላቸው አሜሪካ አሳልፋዋለች የተባለው ውሳኔ በተገለጹት ዘርፎች ላይ ብቻ ከሆነ፣ ከምልክታዊ ፋይዳ የዘለለ ትርጉም እንደማይኖረው ይገልጻሉ። 

  ለዚህ የሚያነሱት ምክንያት ደግሞ አሜሪካ በተጠቀሱት ዘርፎች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ትብብር ካላላች የቆየ መሆኑንና ታደርግ የነበረውም ድጋፍ የጋራ ሥጋትን ለመቅረፍ ያለመ እንደነበር ጠቁመዋል።

  ዕርዳታ ይቋረጥባቸዋል ተብለው ከተጠቀሱት የትብብር ዘርፎች ኢትዮጵያ ታገኝ የነበረው ድጋፍ የሚናቅ ባይሆንም፣ ከአጠቃላይ የውጭ ድጋፎች አንፃር ኢምንት የሚባል እንደሆነ ገልጸዋል። 

  አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታደርገውን የሽብር እንቅስቃሴ የመከላከል ተግባር በዋነኛነት ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ትከውን የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያን አጋርነት በኬንያ ከተካች ሁለት ዓመታት ገደማ መቆጠራቸውን ገልጸዋል። 

  አሜሪካ የኬንያ መንግሥትን የፀረ ሽብር አጋሯ ብታደርግም፣ በተለይ በሶማሊያ አልሸባብን በማዳከም ረገድ ከኬንያ የጠበቀችውን ያህል ማግኘት በመቸገሯ በራሷ የአየር ኃይል ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ እንደተገደደችም ጠቁመዋል። 

  በዚህም ምክንያት በአካባቢው የምታፈሰው ወታደራዊ ወጪ በመናሩ ለኢትዮጵያ ታደርግ የነበረውን ድጋፍ ማቋረጧ ወጪዋን ለመቀነስ ያግዛት እንደሆን እንጂ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እንደማይኖር ገልጸዋል። 

  ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ አሜሪካ ከምታደርገው ድጋፍ ይልቅበድርጊቱ ቀጥተኛ ተጎጂ የሆኑት የአውሮፓ አገሮች ድጋፍ፣ ወትሮውንም ሰፊ እንደሆነና ይህ ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል። 

  የአሜሪካ መንግሥት .. 2019 ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠው ድጋፍ 824 ሚሊዮን ዶላር እንደነበርና ከዚህ ውስጥ 497.3 ሚሊዮን ዶላሩ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የተደረገ ድጋፍ መሆኑን ፎሪን ፖሊሲ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ጠቅሶ ዘግቧል። 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...