በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደውን የመሬት ወረራና ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ማስተላለፍ ሒደት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ያዘጋጀውን ጥናት ይፋ ለማድረግ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ በፖሊስ ታገደ፡፡
ፓርቲው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደውን የመሬት ወረራና ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ማስተላለፍ ሒደት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማጥናት ከብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚው የተውጣጣ ኮሚቴ አቋቁሞ ጉዳዩን ሲመረምር መሰንበቱን የገለጸ ሲሆን፣ ዓርብ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ለአገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙኃን ውጤቱን ይፋ ለማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ጠርቶ ነበር፡፡ ሆኖም ‹‹ፍቃድ የለውም›› በሚል ምክንያት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መግለጫው እንዳይሰጥ መከልከሉን፣ የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ አስታውቀዋል፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫውን ስናዘጋጅ እንደ ከዚህ በፊቱ ለሆቴሉ አስቀድመን በማሳወቅ ክፍያ ፈጽመናል በማለት ሒደቱን የሚገልጹት አቶ ናትናኤል፣ የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመሆናችን ሰላም ሚኒስቴር እንዲህ አዓይነት ስብሰባዎች ሲደረጉ ማወቅ አለበት በሚለው መሠረት አስቀድመው ለሚኒስቴሩ ደብዳቤ መላካቸውንም አክለው አስታውቀዋል፡፡
‹‹ሰላም ሚኒስቴር ከዚያ በኋላ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይወጣ አይወጣ የእኛ ኃላፊነት አይደለም፡፡ ዛሬ (ዓርብ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም.) ግን ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመስጠት ስንመጣ ያጋጠመን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ጋዜጣዊ መግለጫውን ፍቃድ ስለሌለው መስጠት አትችሉም የሚል ዕቀባ አስቀምጦብናል፡፡ በዚህም ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫውን መስጠት አልቻልንም፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
የክልከላውን ምክንያት አስመልክቶም፣ ‹‹ከዚህ በፊት የምናደርገውም ሆነ የምንከተለው ተመሳሳይ አካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ችግር አጋጥሞን አያውቅም፡፡ እኛ ዛሬ ከምንሰጠው መግለጫ ይዘት ጋር ቀጥታ የተያያዘ ክልከላ እንደሆነ ነው የምናምነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
በሕጋዊ መንገድና አስፈላጊ ሒደትን በማለፍ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት የፓርቲው ፍላጎት መሆኑን ያወሱት አቶ ናትናኤል፣ ‹‹ይዘቱን ግን ወደ ፊት ስናወጣ እንደምታዩት እንዲሁም በርካታ ሕገወጥ የሆኑ ሥራዎች ሲሠራ የመንግሥትና የፀጥታ አካላት ማስቆም ሲገባቸው እንደውም የማስቻል ሥራ ሲሠሩ እንደነበር ማስተዋል ችለናል፡፡ ስለዚህ ችግሩ ያለው መከተል የሚገባንን ቅደም ተከተል ሳንከተል ቀርተን አልያም ሕግ ጥሰን ሳይሆን ከጥናታችን ውጤት ፍራቻ ጋር የተያያዘ ነው ብለን ነው የምናምነው፤›› በማለት ዕገዳው ከጥናታቸው ይዘት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
አገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ ችግሮችን ይፈታል ብሎ ፓርቲው የሚያስበው በረዥም ጊዜና በስክነት በሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ግን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ሒደትን የሚጎዱ ናቸው፤›› በማለት አቶ ናትናኤል አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም መንግሥት ተሳስቶ ከሆነ ስህተቱን ማወቅ እንዳለበትና በዚያ መሠረት የእርምት ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት በመጠቆም፣ ‹‹ከዚያ ውጪ ባለ መንገድ የሐሳብ ነፃነትን በመገደብና መረጃዎች ለሕዝብ እንዳይደርሱ በመከላከል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አይገነባም፡፡ ያ ማለት ደግሞ አገራችን ውስጥ ያለው የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ችግሮች አይፈቱም ማለት ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡