Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም ለውድድር መዘጋጀቱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ገቢውን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዷል

መንግሥት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ገበያውን ለውጭ ኩባንያዎች ለመክፈት መወሰኑን ተከትሎ ኢትዮ ቴሌኮም ለገበያ ውድድር ራሱን እያዘጋጀ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

ኩባንያው የሦስት ዓመት የዕድገት መርሐ ግብሩንና የ2013 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅዱን ይፋ አድርጓል፡፡ ረቡዕ ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ድርጅቱ ባለፈው በጀት ዓመት መተግበር የጀመረውን ‹‹ብሪጅ›› የተሰኘውን የሦስት ዓመት የዕድገት ስትራቴጂ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ከልሶ እንዳዘጋጀው ተናግረዋል፡፡ ስትራቴጂው የሚሸፍነው ከሐምሌ 2012 እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ ነው፡፡

ተለዋዋጭ የሆነውን የቴሌኮም ኢንዱስትሪ፣ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታና የደንበኞችን ፍላጎት በመመልከትና በመተንተን የዕድገት ስትራቴጂው ተሻሽሎ መቅረቡን ወ/ሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡

‹‹ስትራቴጂው በዋናነት ዓላማ ያደረገው በአገራችን ያለውን የቴሌኮም ገበያ ሪፎርም ነው፡፡ ገበያው ለአዳዲስ ተዋንያን ክፍት የሚሆንበትና ኢትዮ ቴሌኮም ሪፎርም የሚያደርግበትን አቅጣጫ መንግሥት ማስቀመጡ ይታወቃል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣውን የድርጅቶችና ግለሰቦች የኢንተርኔት አገልግሎት ፍላጎት፣ የቴክኖሎጂ ለውጥ ግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ ስትራቴጂ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ዓላማ ተመራጭ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ተቋም መሆን እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ የደንበኞች ተሞክሮና እርካታ በማሻሻል የድርጅቱን ዕድገትና ትርፋማነት ማስቀጠል ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዓላማችን ኢትዮ ቴሌኮም በደንበኞቹ፣ በቢዝነስ አጋሮቹና በሠራተኞቹ ተመራጭ ኩባንያ ማድረግ ነው፡፡ የደንበኞቻችንን ፍላጎት በማጥናትና በመተንተን አንደኛ አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንዲሆን ለማድረግ ተግተን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ድርጅቱ የቀረጸው ስትራቴጂ ሰው ተኮር እንደሆነ የገለጹት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ የሠራተኛ ማኅበሩ ፍላጎት በማጤን ሠራተኛው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ደስተኛ ሆኖ እንዲሠራ፣ ከውጭ ያሉም ባለሙያዎች ተቀጥረው ለመሥራት የሚፈልጉበት ተቋም ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አዲስ ተዋንያን ሲገቡ ኢትዮ ቴሌኮም የነበሩትን ደንበኞች፣ ባለሙያዎችን፣ የሥራ አጋሮቹንና ገበያውን ለማቆየት የሚያስችለውን ሥራ በመሥራት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ማንኛውም ገበያ ለውድድር ሲከፈት ነባሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋም የነበረውን ገበያ ለማስጠበቅና አዲስ ገበያ ለማግኘት ፈተና እንደሚገጥመው ገልጸው፣ ኢትዮ ቴሌኮም በውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ተቀዳሚ የአገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማካሄድ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመካሄድ ላይ ባለው የብሔራዊ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ለውጥ ፕሮግራም መሠረት የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ለውጭ ኩባንያዎች ሁለት ፈቃዶች ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ባለሥልጣኑ በመስከረም ወር ጨረታውን እንደሚያወጣ፣ ፈቃዱን እስከ ታኅሳስ 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ወ/ሪት ፍሬሕይወት ፈቃዱ በታኅሳስ ወር ቢሰጥ ኩባንያዎቹ ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ ሊገቡ የሚችሉት በአራተኛው ሩብ ዓመት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ በገበያችን ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ገምግመናል፡፡ የውጭ ተዋንያኖች መግባት ፈተና ብቻ ሳይሆን መልካም አጋጣሚም እንደሆነ ተመልክተናል፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉትን የቴሌኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ለሚገቡት ኩባንያዎች በማከራየት ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሞባይል ምሰሶዎችና ፋይበር መስመሮች በማከራየት ከፍተኛ ገቢ ማግኘት እንደምንችል ተመልክተናል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ባቀረበው የ2013 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አጠቃላይ ገቢውን ከ47.7 ቢሊዮን ብር ወደ 55.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ እንዳቀደ ይፋ አድርጓል፡፡ ኩባንያው ከዓለም አቀፍ አገልግሎት 157 ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት አቅዷል፡፡

ኩባንያው እንደ ሮሚንግ ያሉ የውጭ አገልግሎቶች ገበያ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ የተቀዛቀዘበት ቢሆንም፣ ከባለፈው ዓመት ካገኘው 147 ሚሊዮን ዶላር በ6.3 በመቶ ለማሳደግ እንዳቀደ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር ከ46.2 ሚሊዮን ወደ 52.12 ሚሊዮን ለማሳደግ አቅዷል፡፡ የሞባይል ደንበኞች ቁጥር ከ44.5 ሚሊዮን ወደ 49.7 ሚሊዮን፣ የዳታና ኢንተርኔት ደንበኞች ቁጥር ከ23.58 ሚሊዮን ወደ 27.47 ሚሊዮን ለማሳደግ አቅዷል፡፡ የመደበኛ ስልክ አገልግሎት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ቢመጣም፣ አሁን ካለበት 980,000 የደንበኞች ቁጥር ወደ 1.08 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ ታስቧል፡፡

የብሮድባንድ ኢንተርኔት ደንበኞችን ቁጥር በ215.3 በመቶ በማሳደግ ከ212,000 ወደ 669,400 ለማድረስ ታልሟል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር በ135 በመቶ በማደግ 212,000 ደርሷል፡፡ ወ/ሪት ፍሬሕይወት የብሮድባንድ ኢንተርኔት ደንበኞች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊጨምር የቻለው ኩባንያው ባደረገው የታሪፍ ማሻሻያና ባከናወነው የማስፋፊያ ሥራዎችና እንቅፋቶች በማስወገዱ እንደሆነ ገልጸው፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሰዎች ከቤታቸው ለመሥራት በመገደዳቸው ለብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ያለው ፍላጎት እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የአገሪቱን ቴሌኮም ስርፀት ከ46.1 በመቶ ወደ 51.3 በመቶ ከፍ ለማድረግ ግብ አስቀምጧል፡፡

ኩባንያው በአዲሱ በጀት ዓመት የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎች በአዲስ አበባ፣ በክልል ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች እንደሚያከናውን ተገልጿል፡፡ ተቋሙ 842 አዲስ ጣቢያዎች እንደሚገነባ ከዚህ ውስጥ 150 ያህሉ በአዲስ አበባ እንደሚሠሩ ተነግሯል፡፡ የማስፋፊያ ሥራዎቹ በውስጥ አቅም እንደሚሠሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆኑ የኢኮኖሚ አዋጭነትን ሳይመለከት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የቴሌኮም መሠረተ ልማት ሲዘረጋ መቆየቱን የገለጹት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ከዚህ በኋላ ገበያው ለውድድር ክፍት የሚሆን በመሆኑ ኢኮኖሚ አዋጭነት ከግምት ውስጥ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው በገጠር የማስፋፊያ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቀጥል ገልጸው፣ ይህን ለማድረግ ግን የዩኒቨርሳል አክሰስ ፈንድ ድጎማ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ ጋር እንደሚወያዩ ተናግረዋል፡፡

‹‹የሚመጡት ኩባንያዎች ኢንቨስተር በመሆናቸው የሚሠሩት ለትርፍ በመሆኑ አትራፊ በሆኑት ኢኮኖሚ ዞኖች ላይ እንደሚያተኩሩ ይጠበቃል፡፡ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋም በገጠር እንደሚሠራ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹በገጠር መሠረተ ልማት በማስፋፋት አገልግሎት ለመስጠት በከተማ ገበያችንን ማስጠበቅ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስና የተሻሻሉ አገልግሎቶች ለገበያ ያቀረበ ሲሆን፣ በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ አድርጓል፡፡ በሞባይል ዳታ ጥቅል አገልግሎት እስከ 35 በመቶ፣ በሞባይል ድምፅ ጥቅል አገልግሎት እስከ 29 በመቶ፣ በሞባይል ድምፅና ዳታ ጥምር አገልግሎት እስከ 28 በመቶ ቅናሽ እንዳደረገ አስታውቋል፡፡ በሳተላይት አገልግሎት ላይ እስከ 61 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ አድርጓል፡፡ አዳዲስ ካቀረባቸው አገልግሎቶች መካከል ማይ ኢትዮ ቴል የሞባይል መተግበሪያ፣ ኢትዮ ኢኬር ዌብ ፖርታልና የሞባይል ጥቅል ዱቤ አገልግሎት ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች