መንግሥት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የብሔራዊ ቡድን ዝግጅቶችን ጨምሮ እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴዎችን አግዷል፡፡ ዘርፉን የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጪውን ዘመን ውድድር ለመወሰን የመንግሥትን ምላሸ እየጠበቀ መሆኑ እየተነገረ ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ክለቦችና የክለብ አመራሮች ወቅቱ ለ2013 የውድድር ዓመት ቅድመ ዝግጅት የሚደረግበት በመሆኑ በተለይም የፕሪሚየር ሊግ፣ የከፍተኛው ሊግ እና የብሔራዊ ሊግ ክለቦች ተጫዋቾችን እያዘዋወሩ ይገኛል፡፡ ይሁንና አወዳዳሪው አካል ውድድሮችን በሚመለከት መንግሥት በጉዳዩ የሚያሳልፈውን ውሳኔ መጠበቅ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ከዚህ ባሻገር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ከአሠልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ “ላይሰንስ” ጋር በተያያዘ በፌዴሬሽኑ ሲሰጥ የቆየው የብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና የጥራቱ ጉዳይ እስኪረጋገጥ ድረስ ሥልጠናው እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡ በእነዚህና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው ከፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እግር ኳሳዊ የሆኑ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል የ2013 የውድድር ዘመን መቃረቡን ተከትሎ ክለቦችም ዝግጅት ለመጀመር እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል፡፡ ይሁንና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በዚህ ጉዳይ እስካሁን ምንም አለማለቱ ደግሞ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፣ በዚህ ጉዳይ ፌደሬሽኑ የሚለው ምንድነው?
አቶ ባህሩ፡- ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እንደመሆኑ መንግሥት አስቸኳይ አዋጅ እንዲያውጅና ውድድሮችም እንዲቋረጡ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የ2012 ዓ.ም. የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ካለፈው ግማሽ ዓመት ጀምሮ እንዲቋረጡ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ በወረርሽኙ ምክንያት ችግር ውስጥ የገቡ ክለቦችና በስፖርቱ ዙሪያ የሚገኙ አካላት ማለትም ተጫዋቾች፣ ሙያተኞችና ዳኞች ለከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ በመዳረጋቸው መንግሥት ችግሩን ተረድቶ የማገገሚያ በጀት እንዲያመቻች ከስፖርት ኮሚሽን፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ብሔራዊ ዓብይ ኮሚቴና የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ጥናት በማድረግ የጥናቱን ውጤት ለመንግሥት እንዲቀርብ አድርጓል፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴው ሁሉንም ስፖርቶች የሚመለከት መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ለእግር ኳሱ ዘርፍ ግን እስከ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ የማገገሚያ በጀት ተጠይቋል፡፡ ገንዘቡ በአብዛኛው ለክለቦች ማገገሚያ የሚውል ሲሆን፣ ከዚያ ውጭ ያለው ደግሞ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስተዳደራዊና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እንዲውል ነው፡፡ ይህም ወረርሽኙ ባስከተለው ቀውስ ፌዴሬሽኑ ከተለያዩ ማለትም ከስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች፣ ከሜዳ ገቢና ተያያዥ ተቋማት ማግኘት የሚገባውን ገቢ ለመተካት በማለም ነው፡፡ ሌላው ውድድሮችን መጀመር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ይህንኑ በሚመለከት የሚሰጠውን መመርያ (ምክረ ሐሳብ) መነሻ በማድረግ የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት በሚሰጡት አቅጣጫ መሠረት ውድድሮች የሚጀመሩበትን ቅድመ ሁኔታ ላይ ሰነዶች ተዘጋጅተው ውይይት እንዲደረግባቸው ተደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ቅድመ ሁኔታ ሲባል ዝርዝር ጉዳዩ ይታወቃል?
አቶ ባህሩ፡- ውድድሮች እንዲከናወኑ የፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥትም ተስፋ ሰጪ ነገሮች ስላሉ፣ ውድድሮች በዝግ የሚከናወኑ ከሆነ በተቻለ መጠን ያንን ዕውን ለማድረግ ምን መደረግ ይኖርበታል የሚለው ዋናው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊት ፌዴሬሽኑ ውድድሮች እንዲጀመሩ ቀደም ሲል ሰነዶችን በማዘጋጀት ለስፖርት ኮሚሽን፣ ኮሚሽኑ ለጤና ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር ለኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይህ ተቋም ደግሞ ወረርሽኙን ለሚመራው ለአገር አቀፉ ብሔራዊ ተቋም እያለ በርካታ አማራጮች እንዲታዩ ተደርጓል፡፡ ሒደቱ ከፕሪሚየር ሊጉ ሼር ካምፓኒ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አካላት በጉዳዩ ሊኖራቸው የሚገባው ሐሳብ የተካተተበት ነው፡፡ ሲቀጥል ጤና ሚኒስቴር፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩትና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሰነዱን መነሻ በማድረግ ውድድሮች የሚደረጉት በዝግ ቢሆንም ከጉዞና መሰል እንቅስቃሴዎች ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው ሁኔታና ወረርሽኙን መቀነስ የሚቻለው እንዴት ነው በሚለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ሳይቋረጥ በተመረጡ ሜዳዎች ውድድሮች የአምስት አምስት ሳምንት ጨዋታዎች እንዲደረጉ ማድረግ የሚለው አንዱም ይጠቀሳል፡፡ ይህ የክለቦችን ሐሳብ ያካተተ እንዲሆንና ውድድሮቹ በየሦስት አልያም በየአራት ቀኑ ይደረጉ በሚለው ምልከታ ማለትም የቡድኖችን የጉዞና ተያያዥ ወጪ ታሳቢ ያደረገ እንዲሆንም ተደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ክለቦች ውድድር ከማድረጋቸው በፊት ለኮቪድ-19 ምርመራ የሚያወጡትን ክፍያ በተመለከተ ቅሬታ እንዳላቸው ይናገራሉ፣ እዚህ ላይ የፌዴሬሽኑ አስተያየት ምንድነው?
አቶ ባህሩ፡- ክለቦች ለኮቪድ-19 ምርመራ ወጪ እንዳለባቸው ይታወቃል፣ ወረርሽኙ ከሚኖረው ዓለም አቀፍ ይዘት አኳያ እንደ ትልቅ ነገር አንስተን የምናየው ጉዳይ ነወይ? የሚለውን ስንመለከት፣ ፌዴሬሽኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ያለው መረጃ ለአንድ ሰው ምርመራ የሚያስፈልገው 22 ዶላር እንደሆነ ነው፡፡ አንድ ክለብ ይህን ገንዘብ አውጥቶ የተጫዋቹን ደኅንነት መከታተል ያን ያህል ከባድ ነው የሚል እምነት ሊኖር አይገባም፡፡ ይሁንና ፌዴሬሽኑ ይህን ወጪ መንግሥት የሚሸፍን ከሆነ ጥያቄ ማቅረቡ አልቀረም፡፡ የማይሆን ከሆነ ግን ክለቦች ቀደም ሲል በነበረው የውድድር ሥርዓት ከሚያወጡት ወጪ አንጻር የአሁኑ በእጅጉ የተሻለና ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ ያንን ሊያካክስላቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ክለብ ቀድሞ በነበረው አካሄድ መቐለ ከተማ ሄዶ ለመጫወት ከስድስትና ሰባት ጊዜ በላይ የአየር ትራንስፖርት የሚያወጣውን ወጪ በአዲሱ የውድድር አካሄድ ሥርዓት መሠረት በአሁኑ በአንድ ደርሶ መልስ በረራ ያጠናቅቃል ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለወረርሽኙ በሚል ለምርጫ የቀረበውን የውድድር ሥርዓት በዋናነት የተቃወሙት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መሆናቸው ይደመጣል፣ የከፍተኛ ሊግና ብሔራዊ ሊግ ክለቦች በዚህ ጉዳይ ያላቸው አቋም ምንድነው?
አቶ ባህሩ፡- ክለቦቹ በእርግጥ መጠነኛ ጥያቄዎች ማለት አማራጭ ሐሳብ ካለ በሚል ካልሆነ፣ ከወጪ ጋር ተያይዞ ብዙም ቅሬታ የላቸውም፡፡ ውድድሮቹ እንደ ፕሪሚየር ሊጉ ሁሉ በተመረጡ ሜዳዎች በተመሳሳይ የውድድር ሥርዓትና ይዘት የሚከናወኑ ነው የሚሆነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት ተስፋ ሰጪ ነገር መኖሩን ካልሆነ ውድድሮች እንደሚጀመሩ እርግጠኛ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ክለቦች ለመጪው የውድድር ዓመት ዝግጅት ለመጀመር ተጫዋቾችን እያዘዋወሩ ናቸው፣ ካፍም የብሔራዊ ቡድኖችን ቀጣይ የማጣሪያ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ በኩል የፌዴሬሽኑ አቋም ምንድነው?
አቶ ባህሩ፡- የመንግሥት አቋም ፌዴሬሽኑ ከክለቦች ጋር በጉዳዩ ተነጋግሮ የሚደርስበትን ለመንግሥት እንዲያቀርብ ነው፡፡ ሰነዱ ተዘጋጅቶ ለመንግሥት ቀርቧል፣ የሚቀረው የመንግሥት ውሳኔ ነው፣ ይህ ሁኔታው ተስፋ ሰጪ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ማለት መንግሥት ስፖርቱ ወደ ነበረበት ተመልሶ መነቃቃት እንዲፈጠር ፍላጎት ያለው መሆኑ ነው፡፡ ችግሩ ያለው በተለይ በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አካባቢ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ከወጪ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን መቅረባቸው ይጠቀሳል፡፡ እውነት ነው ትልልቅ ደጋፊ ያላቸው ክለቦች አሉ፣ ከሜዳ ገቢ አኳያ ተጎጂ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ግን ደግሞ እንደነዚህ የመሰሉ ዓለም አቀፍ ችግሮች ሲፈጠሩ መጠባበቂያ ዕቅድ ሊኖራቸው አይገባም ወይ? የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ከሩጫው ጋር ያለውን ብንመለከት እንደ “ቨርቹዋል” የመሳሰሉ አማራጮች መታየት ጀምረዋል፡፡ ደጋፊውስ እውነተኛ የክለቡ የልብ ደጋፊ ከሆነ ክለቡን ለመደገፍ የግድ ሜዳ በመግባት ካልሆነ መደገፍ የሚችልበት ሌላ አማራጭ የለውም? ሌላው ከተጫዋች ዝውውር ጋር በተያያዘ በክለቡና በተጫዋቾች መካከል የሚደረገው ውል ካልሆነ ሌላ ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ ከስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ጋር ያለውን ጉዳይም በተመሳሳይ አማራጭ ሁለት፣ ሦስትና አራት በሚል መጠቀም መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ የካፍ ፕሮግራሞችን በተመለከተ የሚጠበቅ ነው፣ ምክንያቱም ከካፍ ተጠባባቂ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አህመድ ባህ ጋር በጉዳዩ በስልክ ተነጋግረናል፡፡ ፕሮግራሞቹ ሲወጡ የሴቶች ወጥቶ መሰረዙ እንደተጠበቀ፣ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሲወጣ የወንዶች አልወጣም ነበርና ለምን ለሚለው፣ አገሮች በወረርሽኙ ላይ ያላቸው ሁኔታና ቁርጠኝነት እየታየ ፕሮግራሙ እንደሚወጣ ተነጋግረን ነበር፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው የሚጠበቅ ነው ያልኩት፡፡ ይሁንና ካፍ አሁንም ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ፕሮግራሙ እንዲራዘም አድርጎታል፡፡ የወንዶቹ ፕሮግራም የወጣ ሲሆን፣ በቀጣይ ምን እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡ ምክንያቱም ካፍ የአገሮችን ዝግጁነት በማጥናቱ ረገድ ክፍተት እንዳለበት ብናውቅም እኛ ግን ዕቅዶቻችንን ለመተግበር የምንቸገርበት ሁኔታ ብዙም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ኮንትራታቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ውላቸው ተቋርጧል፣ በዚህ በኩል ዝግጅታችሁ ምንድነው?
አቶ ባህሩ፡- ከብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት በፊት የሊግ ውድድሮች መጀመር መቻል ይኖርበታል፡፡ የሊግ ውድድሮችን ስንመለከት ያለውን ሒደት ቀደም ሲል በገለጽነው መሠረት እየታየ ነው፡፡ አሠልጣኙን በተመለከተ በቀጣይ ምን ይሆናል ለሚለው ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው በሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ መሠረት የሚከወን ነው የሚሆነው፡፡ የነበረው ይቀጥል ወይስ አዲስ ይቀጠር የሚለው ታይቶ የመጨረሻው ውሳኔ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ካፍ ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ብሔራዊ ቡድን ለማዘጋጀት ወደ 80 ቀን የሚጠጋ ጊዜ ስላለን ችግር የለውም፡፡ እዚህ ላይ ከተጫዋቾች ወቅታዊ ብቃት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ክርክሮች አሉ፣ በእኔ እምነት ተጫዋቾች ለሙያቸው የሚመጥን አስተሳሰብ (Professional thinking) ሊኖራቸው ይገባል የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ተጫዋቾች እግር ኳስ ሥራቸው ነው፣ አሠልጣኝ ቢኖርም ባይኖርም ሙያቸውን አክብረው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ካፍ ለእግር ኳስ አሠልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ “ላይሰንስ” ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ግን ሥልጠናው ከጥራት ጋር በተያያዘ እንዲቆም አድርጓል፣ ብዙዎች በራሳቸው ገንዘብ ከፍለው ሥልጠናውን ወስደው የብቃት ማረጋገጫውን ያላገኙ እንዳሉም የሚናገሩ አሉ፡፡ የኢንስትራክተሮችም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው፣ ጉዳዩ በፌዴሬሽኑ በኩል እንዴት እየታየ ነው?
አቶ ባህሩ፡- ጥያቄው እኔም የምጋራው ነው፣ ምክንያቱም የእግር ኳሳችን ደረጃ የሥራችን ውጤት ነፀብራቅ ነው፡፡ ለዚህም ካፍ በተለይ ለኢንስትራክተሮች የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ የዕድሜ ልክ ነው ወይስ የሚታደስ? የሚለው መታየት እንዳለበት መመርያ ሰጥቶናል፡፡ ኢንስትራክተሮች መኖራቸው መልካም ነው፣ እንዲኖሩም ይፈለጋል፡፡ ይሁንና በአንድ ወቅት በዚህ ጉዳይ የካፍ ቴክኒክ ዳይሬክተር ራውል ችፖንዳ በዙም ኮንፈረስ አስተያየት ሲሰጥ አስታውሳለሁ፡፡ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ የኢንስትራክተር ማረጋገጫ ካልታደሰ በስተቀር መቀጠል እንደሌለበት ተናግሯል፡፡ በአገራችን የሚገኙ ኢንስትራክተሮች የአገልግሎት ጊዜያቸው አልፏል አላለፈም የሚለው ገና የምንፈትሸው ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በዚህ ደረጃ ሰው እያሰበ የሚሠራ ከሆነ የትም ሊደርስ እንደማይችል አምኖ፣ ለመለወጥና ለማደግ ከሆነ ሥራውን በተገቢው መስፈርት መሥራት ይኖርበታል፡፡ የአሠልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ “ላይሰንስ” ጋር ስላለው ጉዳይም ከራውል ችፖንዳ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ቀደም ሲል በነበረው የአሠራር ሥርዓት የ15 እና የ20 ቀናት ሥልጠና እየወሰዱ የ”ኤ” አልያም የ“ቢ” እና የ“ሲ” የአሠልጣኝነት ላይሰንስ የሚሰጥበት አካሄድ መቀጠል እንደሌለበት ተነጋግረናል፡፡ ካፍ ከቁጥር ይልቅ ለጥራት ትኩረት እንደሚሰጥ ወስኗል፡፡ ለዚህ ማሳያ አድርጎ የጠቀሰው “ኢትዮጵያ ከ2012 የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ለምን ጠፋች?” በማለት ነው፡፡ ስለሆነው ካፍ ችግሩ ሥልጠናዎች ላይ ያለውን ነገር እንደገና መመልከት እንደሚያስፈልግ ነው ድምዳሜ ላይ የደረሰው፣ እኛም ይህን መጋራት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም እግር ኳስ የአደባባይ ሥራ እንደመሆኑ የሚለካውም ሜዳ ላይ በሚያስመዘግበው ውጤት ነው፡፡ ስለሆነም የአገራችን የአሠልጣኝነት ብቃት ማረጋገጫ “ላይሰንስ” በዚህ ደረጃ መታየትና መለካት ይኖርበታል፡፡ ላይሰንስን በሚመለከት በካፍ በኩል ያለው ዝግጁነት ምን እንደሆነ አውቀናል፣ ተግባራዊ ማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መሥራት የእኛ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡