Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ!

በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

በአገራችን የዘመን አቆጣጣር የ2012 አሮጌ ዓመትን አሰናብተን የ2013 አዲስ ዓመትን ለመቀበል እየተዘጋጀን ነው፡፡ ይህ ወቅት እንደ አገር የለውጥ ማግሥት ምስቅልቅልና ግጭት፣ የንፁኃን ግድያና መፈናቀል፣ የሕዝብ ሀብት ውድመትና ኪሳራ ተደጋግሞ የተስተናገደበት ነው፡፡ ወደ መጨረሻም ላይ የሕግ የበላይነት ባለመከበሩ ብዙ ውድ ዋጋ ተከፍሎ፣ አጥፊዎች ወደ መጠየቅ እየመጡ ያሉበትና መንግሥትም ሕዝብ የጫነበትን አደራ ወደ መወጣት ያተኮረበት ጊዜ መምጣቱ እንደ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

  በዚያው ልክ ኮሮናን የመሰሉ ዓለም አቀፍ የወረርሽኝ ሥጋቶች፣ አንበጣ፣ ጎርፍና መሰል የተፈጥሮ ጫናዎች በዜጎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩበት አሮጌ ዓመት ነበር  2012፡፡ ከነ ጉድለቱ መንግሥት አገራዊ ለውጡን ፈር ለማስያዝና የብልፅግና ጉዞን ለማሳለጥ ደፋቀና ማለቱ ባይካድም፣ በምርጫ ይካሄድ/ይራዘም መሀል የነበረው የፖለቲካ እሰጣ ገባም ገና የተቋጨ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ እንጥልጥል ውስጥ ሆነን ነው 2013ን ለመቀበል እየተዘጋጀን የምንገኘው፡፡

- Advertisement -

በነገራችን ላይ የአዲስ ዓመት የመጀመርያ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጃንዋሪ የመጀመርያው ዕለት የሆነበት አሠራር ውስጥ መገኘታችን እውነት ቢሆንም፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ እምነቶችና ባህሎች የየራሳቸው የዓመት ቆጠራ መነሻ ወርና ዓመት የሚመለከቱ አካሄዶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ በእስልምና ባህል ውስጥ የዓመት ቆጠራ መጀመሪያቸውን ከነቢዩ ልደት እ.ኤ.አ. ከ570 ጀምሮ አንድ ብለው የሚቆጥሩ እንዲሁም ነብዩ በስደት (ሂጅራ) ወደ ያስሪብ (Yathrib) የአሁኗ መዲና ከተጓዙበት ዓመት (ከ624 እ.ኤ.አ.) የሚጀምሩ፣ ወይም ከነቢዩ ሕልፈት (እ.ኤ.አ. ከ632) ጀምሮ ያደረጉ አሉ፡፡

ሌሎች ደግሞ የዓመት ቆጠራቸውን የሚጀምሩት ለታሪካቸው የማዕዘን ድንጋይ ከሆኑ ጉልህና አንፀባራቂ ታላላቅ ክንውኖች ከተካሄደበት ዓመት ያደረጉም አሉ፡፡ በእኛ አገር በብሔራዊ ደረጃ ዓመት የሚቆጠረው ከጌታ ልደት ዓመት ጀምሮ ሲሆን፣ ከመስከረም የመጀመርያ ቀን አንስቶ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የራሳቸውን የዓመት ቆጠራ መነሻ በታሪክና በባህል በጉልህ ክንውን መሠረት ያደረጉ ኅብረተሰቦችም በእኛም አገር አሉ፡፡ አዲስ ዓመት መጣ ሲባል ደግሞ ቀን ለመቁጠር ብቻ ሳይሆን በአዲስ መንፈስ ወደ ሌላ ምዕራፍም ለመሸጋጋር ነው፡፡

የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም የዓመት ቁጥር መነሻ ዓለም ከተፈጠረችበት ዓመትና ከሚያዝያ ወር የመጀመርያው ቀን ጀምሮ ነው በማለት አጥብቀው የሚከራከሩ ሊቃውንት በአገራችን አሉ፡፡ ‹‹የካም መታሰቢያ›› የተባለውን የአስረስ የኔሰው መጽሐፍ ማየት ይቻላል፡፡ አነሳሳችን ስለዘመን አቆጣጠር ሥርወ ታሪክ ለመተንተን ሳይሆን፣ አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ዓመት ሲተካ ለዚሁ የዓመት ለውጥ የሚመጥን የሰብዕና እና የባህሪ አካሄድ አስፈላጊነት ላይ ለመጨዋወት ነው፡፡

አዲስ ዓመት ሲገባ የእኛ ሰብዕና ባህሪና አካሄድ ዕድሳት ካላገኘ አዲሱን ዓመት የምንቀበለው በአሮጌ የባህሪ አቁማዳችን ከሆነ፣ በአሮጌ የባህሪ ጨርቃችን ላይ የአዲሱን ዓመት ልብስ እራፊ የምንጥፍ ከሆነ በአዲሱ ዓመት ማግኘት ያለብንን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቃሜታዎችን እናጣለን፡፡ በአሮጌው ዓመት (ዓምና) ይዘን የከረምነውን ያረጀ ባህሪና አካሄድ ከራሳችን ላይ አስወግደን ራሳችንን ለአዲሱ ዓመት በሚመጥን ሁኔታ አዘጋጅተን ካልተገኘን እንኳን ከዘመኑ ልንጠቀም ይቅርና በራሳችን ላይ የምናስከትለው ጉዳት እጅግ የከፋ ይሆናል፡፡ አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ማኖር አይቻልም፡፡

አዲሱን ዓመት በአሮጌ ባህሪና አካሄድ  መቀበል ማለት በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ አዲሱን ወይን ጠጅ እንደማኖር ያለ ነው፡፡ አሮጌውን ልብስ በአዲስ እራፊ እንደ መጣፍ (እንደ መደረት) ያለ ነው፡፡ ጉዳት እንጂ ጥቅም አያመጣም፡፡ ይኸው ጉዳይ ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ (ማቴዎስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 16-17) ጎልቶና ተደጋግሞ  ይገኛል፡፡

‹‹በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፣ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፣ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፡፡ ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡››

ስለዚህ አዲሱ ዓመት ይዞልን የመጣውን የአዲስ ሕይወትና አካሄድ ወይን ጠጅ በአግባቡ ለመጠቀም ሕዝብም ሆነ መንግሥት በውስጣችን ያለውን የአሮጌ አስተሳሰብና አመለካከት አቁሞ፣ የአሠራር  ልምድና አካሄድ አቁማዳችን መቀየርና ለአዲስ ዓመት (ዘመን) የሚመጥን ባህሪ፣ ዘዴ፣ ታክቲክና ስትራቴጂ ይዘን መቅረብ አለብን፡፡ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የተለመዱት የዕቅድ አወጣጣችን በአብዛኛው በቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ሰዎች ለየራሳቸው ‹‹በአዲሱ ዓመት ቤት እሠራለሁ፣ መኪና እገዛለሁ፣ አገባለሁ፣ እወልዳለሁ፣ ብር አጠራቅማለሁ፣ ሥራ እቀይራለሁ፣ ሲጋራ፣ መጠጥ. . . አቆማለሁ›› ወዘተ. ማለታቸው ያለና የሚኖር ነው፡፡

መንግሥት በበኩሉ በአዲሱ ዓመት የሚያደርገውን ያቅዳል፡፡ ‹‹የሕዝብ ሰላምና ደኅንነትን አስከብራለሁ፣ የሕግ የበላይነትን አረጋግጣለሁ፣ ፋብሪካ እገነባለሁ፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግርን እቀርፋለሁ፣መንገድ እሠራለሁ፣ ስልክ፣ መብራት፣ ውኃ አስገባለሁ፣ ትራንስፖርት አሻሽላለሁ፣ ግድብ እገድባለሁ፣ ትምህርትና ጤና፣ እርሻ. . . በገጠርና ከተማ አደርሳለሁ፡፡ መከላከያና ደኅንነትን አጠናክራለሁ፣ ዓለም አቀፋዊ ግዳጆቼን እወጣለሁ፣ የውጭ ግንኙነቴን አበረታለሁ፡፡ ለዚህም በቂ በጀት ይዣለሁ፤››  ወዘተ እያለ ይተጋል፡፡ እነዚህ ዕቅዶች (ሐሳቦች) ቢሳኩም ባይሳኩም መታቀድ ያለባቸው ናቸው፡፡ የሚያስመሰግኑ እንጂ የሚያስወቅሱ አይደሉም፡፡

ዋናው ለውጥ ግን በነዚህ ቁሳዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ እነዚህ ዕቅዶች የሚሳኩት ሕዝብና መንግሥት በየፊናቸው ያለባቸውን የአመለካከትና የአካሄድ ችግር ከየውስጣቸው አውጥተው በአዲስና ልማታዊ የአሠራር ሒደት ለመቀየር ራሳቸውን ሲመረምሩና ሲደማመጡ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብም ሆነ መንግሥት የተፈጠረው ለታላቅ ምድራዊና ሰማያዊ ዓላማ ነው፡፡ ማንም ዝም ብሎ እንዲፈነጭና ቀጪ፣ ተቆጪ ሳይኖረው እንደ እንሰሳ ያገኘውን እየበላ መረን ሆኖ እንዲኖር አልተፈጠረም፡፡ የየራሱን ፍላጎትና ጥቅም ብቻ እያሳደደ ሕዝብ በመንግሥት ላይ፣ መንግሥትም በሕዝቡ ላይ ጣቱን እየቀሰረ፣ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል መንግሥትን እያስቸገረና እያማረረ፣ መንግሥትም በሕዝብ ላይ እንደ ልቡ እየዘለለና እየጨፈረ እንዲኖር አልተፈጠረም፡፡

ሕዝቡ እርስ በርሱ በፍቅርና በሰላም ተቻችሎ መኖር አለበት፡፡ በመልክ፣ በፆታ፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በባህል፣ በአካልና በአዕምሮ ተለያይቶ የተፈጠረው እርስ በርሱ እንዲተዋወቅና አብሮ እንዲኖር መሆኑ በቁርዓንም ውስጥ አለ፡፡ ይህ ልዩነት ጌጥ እንጂ ሸክም አይደለም፡፡ አምላክ አለያይቶ የፈጠረውን ሕዝብ የግድ አንድ ዓይነት ለማድረግ የእኔን እምነት፣ የእኔን ባህል፣ የእኔን መንገድ መከተል አለበት ማለት ፈጣሪን መዳፈር ነው፡፡ በዚያው ልክ የሰዎችን ልዩ ባህሪ አለመቀበልና አለማስተናገድም በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው፡፡

ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ልጅም  በልዩነታችን ኮርተን፣ በአንድነታችን ፀንተን ተከባብረንና ተደማምጠን የመኖር ግዴታ አለብን፡፡ ለምድራዊ ቆይታችንም ሆነ ለሰማዩ ቤታችን የሚጠቅመንም ይህ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተመራጩ መንገድ ራስን መመርመር (መገምገም) እና ራስን መታገል እንጂ አንዱ በሌላው ላይ እያላከከ፣ ጣት እየተቀሳሰረ ባለፈው ዓመት ጆሮ እየሰማ መጥፎ አሠራርን መቀጠል አይደለም፡፡

ሕዝብ እንደ ሕዝብ የተፈጥሮ በረከቶቹንና ሕገ መንግሥታዊ መብቶቹን ለራሱ ሲል በራሱ ማስከበር አለበት፡፡ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን መዋጋት አለበት፡፡ ኢፍትሐዊነትን፣ አለመከባበርን፣ አለመተባበርና ለሰላም እንቅፋት መሆንን ራሱ መታገል አለበት፡፡ ሕዝብ መብቱን በራሱ ማስከበር ካልቻለ፣ መብቱ ሲነካ ‹‹ለምን?›› ብሎ ካልጠየቀ፣ ሕገ ወጥነትን ካልተቃወመ በቀር የሌቦች፣ የነፍሰ ገዳዮችና የትራንስፖርት ታሪፍ ቀርጣፊዎች፣ የአሻጥረኛ ነጋዴዎች መጫወቻ ይሆናል፡፡

መንግሥት ያወጣለትን ሕግጋት የማስከበር ኃላፊነት የሕዝብ ነው፡፡ የራሱን ሚና ሳይጫወትና የራሱን ኃላፊነት ሳይወጣ ለትልቁም፣ ለትንሹም የመንግሥትን እጅና ጣልቃ ገብነት መጠበቅ የለበትም፡፡ በየጊዜው በክፉ ሰዎች እየተፈበረኩ ለሚሠራጩ (በተለይ የፌስቡክና የማኅበራዊ ድረ ገጽ ያልተረጋገጡ ወሬዎች) ሰለባ ከመሆን ራሱን መጠበቅ የሕዝቡ ግዴታ ነው፡፡ እውነቱን ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ካልቻለ መንግሥትን መጠየቅ አለበት፡፡ መንግሥትም ቢሆን አስቀድሞ፣ አለዚያ ቢዘገይም ተገቢ  መልስ መስጠት አለበት፡፡

የእምነት አባቶቻችንና ሚዲያዎቻችን የሚነግሩንን እየሰማንና እውነቱን እያረጋገጥን መጠቀም አለብን፡፡ አሳዋቂ፣ አስተማሪና አስጠንቃቂ መልዕክቶችን በጥሞና ማዳመጥ አለብን፡፡ ለሚነግሩን ሰዎችና ሚዲያዎች የተለያዩ ስም አጥፊ ቅጽሎችን እየለጠፍን ከመተቸትና ከማጣጣል ይልቅ ከመልዕክቱ በስተጀርባ ሊኖር ስለሚችለው ሥውር ዓላማ ከመጨነቅ ይልቅ ፊት ለፊት በግልጽ የተላለፈውን መልዕክት ማየትና የተሻለውን መምረጥ የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡ መመርመር፣ መጠይቅ፣ ለአመኑበት በሰላማዊ መንገድ መታገል የጠንካራ ሕዝብ ባህሪ መሆኑን ማመንና መተግበር አለብን፡፡

መንግሥት ሲነግረን ‹‹ውሸቱን ነው›› ካልን፣ መንግሥትም ሲነግሩት ‹‹ስሜን ሊያጠፉ ነው፣ ቀጣፊዎች ናቸው›› የሚል ከሆነ የሕዝብና የመንግሥት ቋንቋ ካልተገናኘ ውኃ አምጣ ሲሉት ድንጋይ መቀባበል ከሆነ ውድቀታችን ከባቢሎን የባሰ ይሆናል፡፡ ሕዝብና መንግሥት መደማመጥ አለባቸው፡፡ ሕዝብ መንግሥትን፣ መንግሥትም ሕዝብን መስማት አለበት፡፡ ሕዝብ እንደሰው ሲፈጠር ሁለት ጆሮና አንድ አፍ እንዲኖረው ተደርጎ ነው፡፡ ይህም ከሚናገረው እጥፍ እንዲሰማ ነው፡፡ መስማትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ እንደማመጥ! ተዳመጡ! (ገና ከለውጥ ማግሥት አንስቶ እባካችሁ የሕግ የበላይነት ይከበር የሚለውን የሕዝብ ጩኸት የሰማ ቢኖር ይሄ ሁሉ ውድ ዋጋ ይከፈል ነበርን!)

በእርግጥ መንግሥትም የራሱ መስሚያዎች (ጆሮዎች) አሉት፡፡ የእሱ ጆሮዎች ቁጥር ደግሞ ከሁለት በላይ ናቸው፡፡ ዋነኛው የመንግሥት ጆሮ ሕዝብ ነው፡፡ ተቃዋሚ ቡድኖችና ግለሰቦች፣ ገለልተኛ የሆኑና ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጠቀሙ ዜጎች፣ የውስጥና የውጭ ሚዲያዎችና የራሱ በርካታ ተቋሞች በሙሉ መንግሥት ስለ ባህሪ (አካሄዱ) የሚሰማባቸው ዕድሎቹ ናቸው፡፡ እነዚህን መስማት አለበት፡፡ ሰምቶም አቅም በፈቀደ መጠን ምላሽ መስጠትና የዕርምት ዕርምጃ አመዛዝኖ መውሰድ ግድ ይለዋል፡፡

እንዳሳለፍነው የሕወሓት/ኢሕአዴግ ያለ  ‹‹እኔ ብቻ ልናገር፣ የኔን ብቻ ስሙ. . .›› የሚል መንግሥት ዋጋ የለውም፡፡ ምላስ ብቻ እንጂ ጆሮ ያልፈጠረበት መንግሥት፣ ፍቅርን አያገኝም፡፡ ለራሱ የሚጠቅመውን ብቻ እየመረጠ የሚሰማ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ መስጠት ይሳነዋል፡፡ በዚህም ሕዝቡ ይንቀዋል፣ ይጠላዋል፡፡ ለንግግሩም ጆሮውን ይነፍገዋል፡፡ ቀኝ ሲጠይቁት ግራ የሚያወራ መንግሥት፣ ሕዝቡ ምን ያመጣል? የሚልና በጉልበቱ የሚመካ ትዕቢተኛ መንግሥት መጨረሻው አያምርም፡፡ ምንም እንኳን ብልፅግና እርሾው ያው ልክፍተኛው ኢሕአዴግ ቢሆንም ከዚያ ብልሹ አካሄድ ወጥቶ አገርና ሕዝብን ማዳመጥ አለበት፡፡ በፅንፈኞች ብቻ ከመደንቆርም መላቀቅ ይገባዋል፡፡

ለእሱ የሚስማሙ ሐሳቦችን ብቻ በሚያቀርቡለት አራጋቢ አማካሪ ተብዬዎች የተከበበ መንግሥት እንዳይሆንም ሊጠነቀቅ ግድ ይለዋል፡፡ እውነቱን ፍርጥርጥ አድርጎ የሚገልጽ መልካም ምክር ከሌለ ሕዝብም ሆነ መንግሥት ይወድቃል፡፡ በመልካም መካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል ይላልና መጽሐፉ፡፡

በነገራችን ላይ ቅዱስ መጽሐፍ ስንል የእስላሙን፣ የክርስቲያኑን በሚል ለመለያየት ሳይሆን፣ የአምላክን መንገድ የሚያሳዩ ሁሉም መጻሕፍት የሚጋሯቸውን ፀጋዎች ሁሉ ለመነካካት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ቁርዓኑም  እጅግ በጣም ግልጽ ነው፡፡ ቁርዓንን ያላነበበ ሰው በጣም ብዙና ትልቅ ነገር የቀረበት ስለመሆኑ የመስኩ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ቁርዓኑ ግልጽ የሆነውን ያህልም መንግሥትና ሕዝብ የሚተዳደሩበት የአገራችን ሕገ መንግሥትም ግልጽ ነው፡፡ የሃይማኖት እኩልነትን አረጋግጧል፡፡ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄም የለም፡፡ ከዚህ አንፃር በአዲሱ ዓመት በዚህ ሳቢያ የሚነሱ በይዘታቸው ፖለቲካዊ ለሆኑ ጥያቄዎች ሁሉ ተገቢውን መልስ እንደሚያገኙ ተስፋችን ነው፡፡ ሁሉም ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር እያለ ሕዝብን በማደናገር ወደ ግጭትና ሕገ ወጥነት የሚያደርገውን መጣደፍ ማቆምና ማስቆምም የጋራ ኃላፊነታችን ነው፡፡ እልህና ካልበላሁት ልድፋው ለፖለቲካችን አይበጅም፤ ተያይዞ ከመጥፋት በስተቀር፡፡

አገሪቱ የጀመረቻቸውና የምታስቀጥላቸው የለውጥና የብልፅግና ጎዳናዎች፣ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ችግር እንዳያገኛቸው መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ዕርዳታም ሆነ ብድር እየደከመ ላለ አገር መንግሥት አይሳካምና ቁመናችንንና አገራዊ ደኅንነታችንን ማረጋጋጥ የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት፡፡ ከገቢ ግብር ጋር የተገናኙ ተግዳሮቶችም ተፈትተው በተሳለጠ አካሄድ ግብር የሚሰበሰብበት ሥርዓት እንደሚጠናከርም እምነታችን ነው፡፡ የሚገኘውን ውስን ሀብት በግልፅነትና ተጠያቂነት መርህ ከሥራ ላይ ማዋልም ለነገ የማይባል ሥራ መሆን አለበት፡፡

በአዲሱ ዓመት ከነባር ችግሮቻችን ለመላቀቅ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ መንግሥትም እንደ መንግሥት ራሳችንን እንመረምር፡፡ ከሐሰተኛ ወዳጅ እውነተኛ ጠላት ይሻላል፡፡ ዋናው ነገር አንዳችን ሌላኛችንን የምንሰማ፣ ብሔራዊ ራዕይ ያለን ዜጎች እንሁን፡፡ አጉል የመንግሥትን ጀርባ ሳይበላው የሚያክኩም ሆነ ሁሉንም ነገር ለመተቸትና ለመቃወም ብቻ የተዘጋጁ ኃይሎች እንዳንሆን መልካሚቱን መካከለኛ መንገድ የምንከተል እንሆን ዘንድ እንደማመጥ፡፡ የዛሬን ብሥራት በአሮጌ ጆሮ የማዳመጥ ባህል (ተለምዶ) አይጠቅመንምና ይቅርብን፡፡ ያለፈው አልፏልና. . . ዳግም ላይመለስ ሄዷልና. . . አዲሱን ዓመት በአዲስ መደማመጥ ተቀብለን እናስተናግደው!

መልካም አዲስ ዓመት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...