Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየትግራይ ምርጫና የወደፊት ምልከታ

የትግራይ ምርጫና የወደፊት ምልከታ

ቀን:

በደረጀ ተክሌ ወልደ ማርያም

ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ በትግራይ ክልል ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ የወሰነው የሕወሓት አመራር፣ ምርጫውን ቢያካሂድ በክልሉም ሆነ በአገር ደረጃ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አስቸጋሪ ቢመስልም፣ አሁን እየታየና እየተሰማ ካለው ሁኔታ በመነሳት ጥቂት ነገሮችን መገመት ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሲናርዮ (የወደፊት ምልከታ) የሚባለውም አሁን የሚታየውን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ሁኔታውን ከፈጠረው የጀርባ ታሪክ ጋር በማጣመር ወደፊት ምን ሊከሰት እንደሚችል መተንበይ በመሆኑ እኔም አሁን ከሚታየውና ከሚሰማው ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ወደፊት ሊፈጠር ስለሚችለው ነገር የሚከተለውን ማለት ፈለግሁ፡፡

ለዚህም እንዲረዳ በአሁኑ ወቅት ምርጫውን አካሂዳለሁ ብሎ የቆረጠው ሕወሓትና አታካሂድም፣ ብታካሂድም በአመራሩ ላይ ለውጥ ካመጣህ የእርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ጣልቃ እገባለሁ ያለው የፌዴራል መንግሥት አሁን ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታና ያለፈው ይዞታቸው ምን ይመስላል? የሚለውን መመልከት መጪውን ለመገመት ጠቃሚ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሕወሓትን በተመለከተ

ኢትዮጵያ በሕወሓት ሥርዓት ሥር በቆየችባቸው 27 ዓመታት ውስጥ በተካሄዱት አምስት አገር አቀፍ ምርጫዎች ተወዳድሮ ሁሉንም ምርጫዎች በማጭበርበር ማጠናቀቁን በውጭ ታዛቢዎች ሳይቀር የተረጋገጠ መሆኑ፣ የሕወሓት ባለሥልጣናትም ሆኑ አባሪዎቻቸው ዓይናቸው ባረፈበትና እጃቸው በደረሰበት ቦታ ሁሉ ያገኙትን የአገሪቱን ሀብት በመዝረፍና የጠሉትንም ሆነ የፈሩትን በማስወገድ የሚታወቁ መሆናቸው፣ ከዚህም አልፎ ሕወሓት ታላቁን የጣና በለስ ፕሮጀክት ማውደሙና አገሪቱን የባህር በር ማሳጣቱ በኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ ገና ከጅምሩ የዘመተ መሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስለሚታወቅ ከላይ የተጠቀሱት ማስረጃዎች ሕወሓት አሁን የሚያካሂደውን ምርጫ ከጅምሩ አመኔታ እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትን በተመለከተ

አብዛኛዎቹ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለረጅም ዓመታት ከሕወሓት አመራር ጋር በመሆን የሕወሓት መራሹን ሥርዓት በማገልገል በዘመኑ ለተሠራው ጥፋት ተጠያቂነቱን የሚጋሩ ናቸው፡፡

የፌዴራል መንግሥቱ ከሕወሓት ጋር ያለውን አለመግባባት እንደ ውስጥ ጉዳይ በመቁጠር ችግሩን በሰላም ለመፍታት ጥረት ማድረጉ ከፍላጎት የሚመነጭ ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊም ሆነ ብሔራዊ ግዴታ መሆኑ፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካስመዘገቡት መልካም ስምና በአካባቢያችን ከገነቡት ተፅዕኖ የማድረግ አቅም አንፃር የማስገደጃ ኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ ሩቅ መሆናቸው መታመኑ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች የፌዴራል መንግሥቱ ሕወሓት ለሚያካሂደው ክልላዊ ምርጫ የኃይል አፀፋ እንደማይወስድ ያረጋግጡበታል፡፡

ይሁን እንጂ የፌዴራል መንግሥቱ ዝምታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሕወሓትን ሥጋት ሊያስቆመው አልቻለም፡፡ የሕወሓት አመራሮች ሥጋት በትንሹ በሦስት መንገዶች ሊገለጽ ይችላል፡፡

ለረጅም ዓመታት ለውጥ ፈላጊው የትግራይ ሕዝብ ያፈራቸው ወጣቶች የትግሉን ዙር እያከረሩት መምጣታቸውና በመሀል አገር በክልሉ ተወላጆች እየተመሠረቱ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕወሓትን ለመጣል እየተዘጋጁ መሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ሕወሓትን ለማንበርከክ እርጋታን የተላበሰ ከጥርጣሬም ከፍ የሚል ሥውር ተግባር ሊያደራጅ እንደሚችል መገመቱ፣ ከላይ ከፍ ብለው በተገለጹት የሕወሓት ጥፋቶች ምክንያት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሕወሓት መሪዎች ላይ ጠንካራ ዕርምጃ ቢወሰድ የሚደግፍ መሆኑ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ስለዚህም ሕወሓት ከተደገሰለት መዓት ለማምለጥ የሚችልበትን መንገድ ማከናወን የሚችለው ምርጫውን በተለመደው መንገድ ሳይሆን ባልተለመደ መንገድ ሲያካሂደው ብቻ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ ለምርጫው መካሄድ ጥርሱን ነክሶ የሚታገለውም ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡

ምርጫውን ባልተለመደ ሁኔታ ለውጭው ሰሚ አካል በሚመች መንገድ ማከናወኑ ሕወሓትን ወደ ድል እንደሚያቃርበው ቢያምንም አንድ ያልተጠበቀ ማስጠንቀቂያ ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ መሰጠቱ ላቀደው ዓላማ መሰናክል እንደሚሆንበት ይገምታል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው መግለጫ ቁልጭ ባለ መንገድ የሚለው ሕወሓት በሚያከናውነው ምርጫ አመራሩን የሚቀይር ከሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ ይገባል የሚል ነው፡፡

ስለዚህም የሕወሓት መሪዎች ሁለት ምርጫ አላቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማስጠንቀቂያ በማጤንና ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ በመገመት ምርጫውን በተለመደው የቀድሞ መንገድና በጀት በማካሄድ ራሱን አስመርጦ ጥልቅ ተሃድሶ በሚለው የጨዋታ መርሕ በመቀጠል ከሚቃጣበት አደጋ ራስን ማዳን ሲሆን፣ ይህ አንደኛው ሲናርዮ ይሆናል፡፡

ሌላኛው ሲናርዮ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ ቦታ ባለመስጠት ምርጫውን ባልተጠበቀ ውጤት ማካሄድ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት በምርጫው የሚካተቱና ከነዚሁም ውስጥ የሚመረጡ አባላት ለክልልና ለወረዳ ምክር ቤት እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡ ከነዚሁ ውስጥ በተለይም ዓይን ለሚያርፍበት ለክልሉ ምክር ቤት በግድያም ሆነ በዘረፋ ያልተሳተፉ በሰላማዊነታቸው የትግራይ ሕዝብም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት አካላት የሚያውቁአቸው ወጣትና አዳዲስ የሕወሓት አባላት ለክልል ምክር ቤት እንዲመረጡ ተደርጎ ከፍተኛውን ሥልጣን እንዲይዙ ይደረጋል፡፡

ልብ በሉ የመጫወቻ ሜዳው በአዲሶቹ የክልሉ መሪዎች እጅ ቢሆንም ሥውር እጅ ከጀርባቸው ይቀመጣል፡፡ ይህ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘመን ልምድ የተካበተበት ነው፡፡

አዲሶቹ የክልሉ መሪዎች ሥልጣን እንደጨበጡ ስለ ወደፊቷ ትግራይ ልማት፣ ዕድገትና ሰላም በዝርዝር የሚገልጹ ሲሆኑ፣ በንግግራቸውም ውስጥ ከዚህ በፊት የተፈጠረውን ልዩነት በመግባባት በማስወገድና ያለፈውን ቁርሾ ለታሪክ በመተው በአዲስ መንፈስ መራመድ እንደሚገባና የወልቃይትም ሆነ የኮረም ጉዳይ በሠለጠነ ውይይት እንደሚፈታ በርቱዕ አንደበት ይገልጻሉ፡፡

ይህ አዲስ አስተሳሰብ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ቀልብ የሚስብ ከመሆኑም በላይ በውጭዎቹም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ስለሚያደርግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጣልቃ ገብነት ማስጠንቀቂያ ዋጋ እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥቱ ዕርምጃ እንዳይወስድ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ዋነኛው፣ የሰላም ጥሪ ባደረገ ክልል ላይ ጥቃት ማሰብ የሥነ ልቦናን ሕግ የሚፃረር ከመሆኑም በላይ በውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሰላም ጥሪን እንደማደፍረስ ሆኖ ስለሚቆጠርበት ነው፡፡

ስለዚህም ተጠርጣሪዎቹ የሕወሓት መሪዎች የዕፎይታ ጊዜ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ ጥቂት ዘግየት ብለው ግን አዲሶቹ የሕወሓት መሪዎች የተጀመረውን የሰላምና የዕርቅ መንገድ ለማጎልበት እንዲቻል ለተጠርጣሪዎቹ የቀድሞ ሕወሓት ባለሥልጣናት የውጭ ሕክምና ፈቃድ ጥያቄያቸውን ለፌዴራሉ መንግሥት ማቅረባቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ የዚያ ሰው ይበለን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...