Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትአዲስ ጧፎችና ደም የላሱ ገጀራዎች

አዲስ ጧፎችና ደም የላሱ ገጀራዎች

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

የሰኔ 20ዎቹ (2012) የግድያና የውድመት ዶፍ ባህሪ

በኢትዮጵያና በሌላው ዓለም ውስጥ፣ አሁን ባለንበት ዘመንና ሰዓት የጭካኔ ግድያዎች ተፈጽመዋል፡፡ ይፈጸማሉ፡፡ ‹‹የጭካኔ ግድያ›› የሚል ሚዛንም አለ፡፡ የጭካኔ ግድያ ይዘገንናል፡፡ እናፍርበታለን፡፡ ጭካኔን ከርህራሄ ጋር የሚያነፃፅር ሥነ ምግባር ያለበት ባህል ውስጥ ስለምንኖር፡፡

- Advertisement -

ከሃጫሉ የግድያ ሌት እስከ ሰኔ 24፣ በተለይም በሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በተወሰኑ አካባቢዎች ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጸሙት ግድያዎችና የውድመት ተግባሮች ‹‹ጭካኔ›› የተሰኘ አገላለጽ የሚያንሳቸው ናቸው፡፡ ‹‹አዲስ ነፍጠኛ›› እንዳይወለድ በሽል ላይ እስከመጨከን የከፋ ‹‹ብቀላን›› አንዳንድ ሰዎች ለመግለጽ ብለው አረመኔያዊ (ባርባሪክ) ይሉታል፡፡ በአገራችን የታየው ግድያና ውድመት ግን አረመኔያዊ ባህሪ ያለው አልነበረም፡፡ በዓለማችን ዛሬ አረመኔያዊ (ባርባሪክ) አገዳደል አለ ወይ? ብለው ቢጠይቁኝ የዓለምን ጉራንጉር አጣርቼ ስለማላውቅ አላውቅም እላለሁ፡፡ አረመኔያዊ መሰል አገዳደልና አውዳሚነትስ አለ ወይ? ቢሉኝ አዎ እላለሁ፡፡ እንደዚያ ዓይነት ባህሪ ሲከሰት አልፎ አልፎ ስላየሁ፡፡

በዘመነ አረመኔ (ባርባሪዝም) ዘመቻና ቅጣት ውስጥ ዛሬ ልንዘገነንበት የምንችለውና ጨካኝ ብለን የምንሰፍረው ድርጊት በዘመኑ የማይዘገንን፣ ነውር የሌለበት፣ ተገቢ የሆነ ቅጣት ነበር፡፡ ፈጣሪ ምን ይለን ብለው አይሸማቀቁም፡፡ ምክንያቱም በእነሱ ዘመን ህሊና፣ አምላክም ከነሱ ጋር አብሮ ዘምቶ፣ አብሮ የሚቀጣ፣ አብሮ የሚጨፈጭፍና የሚያወድም፣ አብሮ ምርኮ የሚሰበስብ ነው፡፡ በአገራችን በሰኔ 20ዎች ጥቂት ዕለታት ውስጥ የተፈጸሙት ግድያዎች በዚያ ዓይነት ህሊና የተፈጸሙ አልነበሩምና በአረመኔያዊ ባህሪ ሊገለጹ አይችሉም፡፡

የሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል በፈጠረው ዓይነስቡ የጠፋ ቁጣ የተካሄደው ቅጣት መደዴ ቅጣትም አልነበረም፡፡ ቁጣው ከሞላጎደል ኢላማውን የመረጠ ነበር፡፡ ዒላማ የተደረገው ማኅበረሰብ ወይም የኅብረተሰብ ክፍል የሃጫሉ ጠላት የነበረና ሃጫሉን የሚገድል/በሃጫሉ ግድያ እሰይ የሚል ተብሎ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ሃጫሉ ከተገደለበት ሌት አንስቶ በጥቂት ዕለታት የተፈጸመውን ግድያና ውድመት ‹‹የነፃነት ትግል›› አድርገው ያሞካሹና ‹‹ግፋ በለው!›› ያሉ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም፣ የተደረገው ነገር ሙሉ ለሙሉ ከነፃነት ትግል ጋር አንዳችም የባህሪ ግንኙነት አልነበረውም፡፡ ጥቃት የተካሄደባቸው ውጥንቅጤ ሰዎች የኦሮሞ ነፃነት ፀሮች አልነበሩም፡፡ በሚዲያ ‹‹ገርስስ! ናድ!›› ሲሉ የነበሩት ሰዎችም ለነፃነት ሲሉ የሚጮሁ አልነበሩም፡፡

አብዲ ኢሌም ስለ ሶማሊ ነፃነት ለመናገር ደፍሮ ነበር፡፡ ግን ከነፃነት ጋር ትውውቅ አልነበረውም፡፡ የአብዲ ኢሌንና የጀሌዎቹን ግፍ ለማስቆም የፌዴራል ኃይል ሶማሌ ክልል ውስጥ ሲገባ ሕወሓታዊ ሸሪኮቹና ተስፈኞቹ በሉዓላዊነትና በነፃነት መጣስ ስም ተቃውመዋል፡፡ ስሙን የሕገ መንግሥታዊ ነፃነት መጣስ ይበሉት እንጂ ምክንያታቸው ፍጅቱ እንዲቀጥልና እንደሰደድ እንዲዛመት ከመፈለግ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ በ‹‹ኦኤምኤን›› ላንቃቸውን ሲሰነጥቁ የነበሩም ሰዎች ውድመትና ፍጅቱ በኦሮሚያ ከተሞች እንዲዛመትና አዲስ አበባ ድረስ እንዲዘልቅ ይፈልጉ ነበር፡፡ ያንን መፈለጋቸውስ ለኦሮሞ ጥቅም ብለው? ፈጽሞ አልነበረም፡፡ በውድመትና በግድያው የተገኘው ውጤት ሕዝቤ የሚሉትን ሕዝብ የጎዳ እንጂ የጠቀመ አልነበረም፡፡ የኦሮሚያ ክልልን መንግሥት ከገቢ በላይ በበጎ ገጽታ ረገድ እጅጉን የጎዳ፣ ነዋሪዎችን በሥራ ቅጥርም ሆነ በቋሚና በተባራሪ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚገኝ መተዳደሪያን ያደረቀ ነበር፡፡ ይህም ትንሹ ነው፡፡ ጃዋር መሐመድ በ‹‹ኤል›› ቲቪ ላይ፣ ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ ‹‹ሃምሳ ሚሊዮን ከሚሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ አንድ ሚሊዮን እስኪቀር ድረስ›› ለመታገል ሲዝትም፣ የዛቻው ማዕዘን የኦሮሞ ጥቅም ነበር? ይህን ያህል ሚዛን አልባ የትርፍና ኪሳራ ሥሌት እንዴት ሆኖ ለኦሮሞ ማሰብ ይሆናል!?

‹‹የነፍጠኛ›› ክምችት በተባሉ (ኦሮሞዎችም ባሉበት ውጥንቅጦች) ላይ የተፈጸመው ቅጣት ኢሰብዓዊና ፀረ ሕዝብ መሆኑ አንዳችም ጥርጥር የለውም፡፡ ሰዎችን መርጦ ለሰው ልጅ ተቆርቋሪነት ብሎ ነገር የለም፡፡ የተወሰነ ክፍለ ሕዝብን/ሕዝብን ዓይንህ ላፈር ብሎ እያጠቃ ለሌላ ሕዝብ የሚቆረቆር ‹‹ሕዝባዊነት›› ብሎ ነገር የለም፡፡ እሳት ውስጥ የገባ የሞራ ቅርናት ቆንጆና ፉንጋ የለውም፡፡ በሰው ላይ በሚፈጸም ወንጀልና በጅምላ ጥቃት ከቀረኑ ቀረኑ ነው፡፡ የተፈጸመው ድርጊት በፀረ ሕዝብ ድርጊት፣ በደቦ ወንጀል ወይም በኢሰብዓዊ ግፍ መፈረጅም የማይበቃው ነው፡፡ የሰኔ 20ዎቹ ዒላማውን የለየ ጅምላ ጥቃት፣ ‹መአሕድ›ን ከወለደው የ1984 ዓ.ም. አካባቢ ጥቃት ጋር ዘመዳም ነው፡፡ ሁለቱም ፋሽስታይ ቀመሶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ፋሽስታዊ ድጦችና ዝንባሌዎች አሉ ሲባል፣ ‹‹አሉ›› የተባሉት ነገሮች ፀባይ ፋሽስታዊ መሆኑን እንጂ ፋሽዝም መኖር አለመኖሩን ወይም ፋሽስታዊ ፀባይ ያላቸውን ነገሮች የፈጸሟቸው ፋሽስቶች መሆን አለመሆናቸውን አይናገርም፡፡ አሁንም አባባሎቹን በቅጡ እንረዳ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነገሮች አሉ ሲባል፣ በዴሞክራሲ ውስጥ የምናገኛቸው ነፃነቶች ዘመድ የሆኑ ነገሮች መኖራቸውን ይናገራል እንጂ ዴሞክራሲ ስለመኖር አለመኖሩም ሆነ ዴሞክራቶች ስለመፍካት አለመፍካታቸው አይናገርም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ የለም፡፡ ያላበለፀግናቸውና ያልተጠቀምንባቸው ዴሞክራሲያዊ ቅርሶች አሉን፡፡ ዴሞክራሲን ለመገንባት  መፍጨርጨርም አሁን አለ፡፡ የዴሞክራሲ አንዳንድ ሰበዞች ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡ ጣዕማቸውን መቅመስና ማሽተት ጀምረናል፡፡ እነሱ እንዲበራከቱና ሥር እንዲይዙ የማድረግ እንክብካቤውን ግን ገና አላወቅንበትም፡፡ ካለማወቅም በላይ በትርምስና በዘግኛኝ ግፍ እየደነቆልናቸው እንገኛለን፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ፋሽዝም የለም፡፡ ፋሽስት መንግሥት የለም፡፡ ሥልጣን የያዘ ፋሽስት ግለሰብም ሆነ ፋሽስት ፓርቲም የለም፡፡ ነገር ግን ፋሽስት ፓርቲና እንቅስቃሴ ሊወልዱ የሚችሉ አውቀውም ሆነ ሳያውቁት ለዚያ የሚሠሩ ቡድኖችና ግለሰቦች አሉ፡፡ ለፋሽስታዊ ጭፍጨፋ የሚሆኑ የልቦና ማህፀኖች ተሰናድተዋል፡፡ የተወሰነ ማኅበረሰብን ለይቶ በድፍኑ የጠመደ ጥላቻ፣ የገረረ ጭካኔና በቀለኛነት በደንብ በስሏል፡፡ ጨፍጫፊና አስጨፍጫፊ አስተሳሰብ ‹‹ለመብትና ለነፃነት በመታገል›› ስም የሐሳብ ገጀራውን ሲስልና ሲሰነዝር ለማየት ተችሏል፡፡ የሐሳብ ገጀራም ወደ የሚዳሰስ ገጀራ ተቀይሮ ደምና ዋይታ ሲረጭ፣ ሥጋ በእሳት ሲጠብስ ታይቷል፡፡

በተወሰነ ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠረውን ጅምላ ጥቃትና ውድመት ያቀናበሩትና ‹‹በኦኤምኤን›› ላይ ግፋ በለው ሲሉ የነበሩ ሰዎች (ዱክትርና የጫኑም ይሁኑ ‹‹የሕግ ሊቅ›› ተብየዎች)፣ የዝምድና ቅርበታቸው፣ ምዕራብ አገሮች ውስጥ ከምናገኛቸው ‹‹ራሰ ልጩ›› በመባልና በስደተኛና በሴም ዘር ጠልነት ከሚታወቁት የናዚዝም ግልገል ደቀመዝሙሮች ጋር ነው፡፡ ራስ ፀጉራቸውን ባይላጩም ልቦናና የሰው ልጅ አክባሪነታቸውን በጭካኔና በጥላቻ ምላጭ የተላጩ ፋሽስታይ በቀለኞች ናቸው፡፡ ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጥረትና ወደ ፋሽስታዊ መጨፋጨፍ የማንሸራተት ጥረት በኢትዮጵያ ግብግብ ላይ ናቸው፣ የኃይል ሚዛኑ አሁን በየት በኩል እንዳለ የታወቀ ቢሆንም ገና አሸናፊው አልለየም፡፡

ቀጭው ማን ነው? ተቀጭውስ?

ቀጪና ተቀጪ ማነው ሲባል መልሱ ቀላል ይመስላል፡፡ ዶፍ የወረደው ‹‹አማራ›› በተባለ ላይ ነበር፡፡ ዱላ፣ ገጀራና ነዳጅ ይዘው ዓይነቱ የበዛ ጥቃት የፈጸሙትን ወጣቶች ደግሞ ቀጪ ወንጀለኞች አድርጎ ማየት ቀላሉ መልስ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱንና የሥራ ዕድል ኪሳራውን ትተን፣ የዚህ ዓይነቱ የተወሰነ ማኅበረሰብ ላይ ያጣጠጠረ ጅምላ ጥቃት፣ የአፀፋ ምትን የሚጎትት ነው፡፡ የሩዋንዳው የቱትሲዎች ፍጅት፣ በስተኋላ ሁቱዎች መሸሽያ እስከ ማጣት ያደረሰ መጠቃትን አስከትሏል፡፡ በትናንትናዋ ዩጎዝላቪያ ውስጥ ሰርቦች በሙስሊሞች ላይ ያካሄዱት ጭፍጨፋ ኮሶቮ ውስጥ ለሰርቦች መጨፍፈጨፍ ጦስ ሆኗል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ የጦስ ቅብብል ካለበት ጥቃት የትኛውም የክትክት ተሳታፊ አትራፊ አይሆንም፡፡

የሰኔ 20ዎችን ግፍ የፈጸሙት ወጣቶች ራሳቸው የግፍ ውጤቶች ናቸው፡፡ በሰብዕናቸው ላይ ግፍ ተፈፅሟል፡፡ ሃሳዊ ጠላት በፈጠረ የጥላቻና የበቀል ውስወሳ የህሊና ሚዛናቸው ተሰልቧል፡፡ ፈጣሪንና አረጋውያንን የሚፈራና የሚያከብር ልቦናቸውን ተነጥቀዋል፡፡ የዋናዎቹ የጭፍጨፋና የውድመት ወንጀለኞች ዱላና ቆንጭራም ተደርገዋል፡፡ እዚህ ደረጃ የደረሰ የነፍስ ሰለባ ቁጥሩ ከግድያ ነው፡፡ ዋናው ቆንጨራና ዱላ ወጣቶቹ እጆች ላይ የተገኘው ሳይሆን የወጣቶቹን ህሊና የሰለበው የአጠባ ቆንጨራና ዱላ ነው፡፡ ዋናዎቹ የጥፋት ወንጀለኞችም የአጠባ ቆንጨራና ዱላውን በጥላቻና በበቀል መልክ እያደራጁ ከውስጥና ከውጪ በሚዲያ፣ ሰው በሰው ውስወሳና በመጻሕፍት መልክ በ‹ነፃነት ንቃትና ትግል› ስም ለወጣቱ የጋቱት የበስተጀርባ ተዋንያን ናቸው፡፡ በጥላቻና በበቀል ዋናዎቹ ልበ ሥውራንም እነሱው ናቸው፡፡ ሃምሳ ዓመታት ያህል የጥላቻና የበቀል ንቃትን እሽሩሩ እያሉ እስከ ዛሬ ድረስ የኖሩ፣ የክርስቲያንነትም ሆነ የሙስሊምነት ታርጋ ኖሯቸው፣ የአማኝ ርህራሄና ፈሪሃ ፈጣሪ ከነመኖሩም የተረሳቸው ጥላቻና በቀል አምላኪዎች፣ በተለይም ሴምን እንደ ጠላት የሚያዩ፣ የዛሬን የኦሮሚያ እውነታንና የኦሮሞን የዛሬ ማንነት በትናንትና ታሪክና ማንነት ለማረም እስከመፈለግ የዞረባቸው፣ ምሁር ነኝ ተብዬ ፅንፈኞች (ምሁርነታቸው የደረቀና መለወጥ የተረሳው) … የመሐንዲሶቹ ባህሪ ይህንን መሳይ ነው፡፡

ከዋናዎቹ አጨፋጫፊዎችና የነሱ ስለትና ክብሪት ሆነው ካገለገሉት ወጣቶች ባሻገር፣ ሌሎች ደም ያጠቀሱ ተዋንያንም አሉ፡፡ ከሰኔ 22 እስከ 24 በተካሄደ የግድያና የውድመት ትርዒት ጊዜ የፈዘዙ/እንዳላየ ያዩ የአስተዳደርና የፀጥታ ሰዎች ሁሉ ቆንጨራ አልጨበጥንም፣ ቤንዚን አላርከፈከፍንም፣ ደም አላፈሰስንም ሊሉ አይችሉም፡፡ በገንዘብ ጥቅም ታውረው በድብቅ ጦር መሣሪያ በማስረግና በማዘዋወር ሰንሰለት የተሳተፉና እየተሳተፉ ያሉ ሁሉ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በመውጋት፣ አገርን ለትርምስ አሳልፎ በመስጠት ሚና ውስጥ ባለድርሻ መሆናቸው ይግባቸው!

 ‹‹ፈረንጅ አገር ወይም አዲስ አበባ ሆናችሁ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ተሸሽጋችሁ፣ በኦሮሚያ አደባባይ ላይ ብትቆሙ ትንፍሽ የማትሉትን ነገር እየተናገራችሁ ኦሮሚያ ውስጥ ያለ ‹መጤ/ነፍጠኛ› ተብዬ ዝንቅ ማኅበረሰብን ለጥቃት አታጋልጡ!” ቢባሉ የማይሰሙ፣ አስተዋይነታቸውን በብሽሽቅ ምርኮኝነትና በዝና ጥማት ቀቅለው የበሉ ምኒሊካውያንና የነፍጠኛነት አወዳሾችም ምራቃቸውን ቢያጣጥሙት፣ የተጠቂዎችን ደምና ዋይታ እነሱም እንደተጎነጩ ይረዱታል፡፡

ከሰኔ 20ዎች ትርዒት በፊትና በትርዒቱ አውራ ዕለት ‹‹የነፍጠኞችን ማዕከል ናድ!›› እያሉ የትርዒቱ የሩቅ ተሳታፊ ከመሆን ተሻግረው፣ የውድመትና የግድያ ድግሱ ከበረደ ወዲያ የፀፀት ስሜት ውል ሳይላቸው፣ ያንን ያክል ሲኦል ስለተፈጸመባቸው ሰዎች ሙጃ የተረጋገጠ ታክል እንኳ መቆርቆር ሳይነካካቸው (ከሰው ተፈጥረናል ለማለት ያህል እንኳ የሚጠቅም የሐዘኔታ ድምፅ ሳይወጣቸው) በሠልፍም ሆነ በሌላ መልክ ምላሳቸውን እየዘረጉ ‹‹በገለልተኛ ወገን ይጣራ!›› በሚል ዘዴ የግፍ ትርዒቱን የመንግሥት እጅ ሥራ አስመስሎ ለማደናገር የሞከሩ፣ ‹‹ኦሮሞ ላይ ተዘመተ! ኦሮሞ ተጨፈጨፈ! መቶ ሺሕ ኦሮሞ ታሰረ!›› እያሉ ግርዶሽ ለመፍጠር የሞከሩ፣ ‹‹ኦሮሞ ተነስ! የነፍጠኛ ማዕከሎችን አሁንም አፍርስ!..›› እያሉ ለሌላ ድግስ የተለማመኑ (እስካሁን በፈሰሰው ደም ጥማቸው ያልታገሰ) የሰው ፍጡርነት የጠፋባቸው ጉዶች የግፍ ኃጢአታቸው ካንድ በላይ ነው!! ገድሎ አስገድሎ፣ እንዳይታወቅ መረጃና መቃብር የማጠፋፋት፣ እያጠፋፉም ደግሞ ሌላ የግፍ ትርዒት የማነሳሳት ድርብርብ ጥፋት! ለአሜሪካ ድምፅ፣ ሐምሌ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ቃለ መጠይቅ የሰጠው ጃልመሮ (ኩምሳ ድሪባ) የቃለ መጠይቅ ዓላማም እዚሁ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ የሃጫሉ ግድያም ሆነ ጅምላ ጭፍጨፋው ውስጥ የለሁበትም በማለት መንግሥትን የጥርጣሬና የቁጣ ዒላማ ማስደረግ! በተግባር የተካሄደ ግፍን በቃላት የማንፃት ተውኔት! ከሁሉም ከሁሉም የውድቀታቸውን ትንቢት እያዩ በምላስ መፈራገጥ!

የሰው ልጅ ጥቃት ጉዳያችን ነው ባይ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ታላላቅ መንግሥታት ‹‹ኦሮሞ ጥያቄና ብሶት አለው፣ መንግሥታዊ ‹ጄኖሳይድ› (የተነጣጠረ ጅምላ ጥቃት) እየተፈጸመበት ነው›› ከሚል የቆርጦ ቀጥሎች ጩኸት ጋር መዳራት ከቀጠሉ፣ የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ሲያዩ፣ የሃጫሉ ገዳዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ የተጮኸውን ጩኸት ሲሰሙ፣ ስለሃጫሉ በመብከንከን ዳስ ውስጥ የተካሄደውን በሰው ልጅ ላይ የተካሄደ የጭካኔ ጭካኔና ማኅበረሰብ የለየ የጅምላ ጥቃት ለማየትና ለማውገዝ ከወላወሉ፣ የዚህ ግፍ መሐንዲስነትና አካሂያጅነት ከዓብይ መንግሥት እንዳልሆነና በጥቂት ቀናት ውስጥ አያሌዎችን የማጨድ ጭፍጨፋ አዘማማጅነት ከሥርም ሊመጣ እንደሚችል ካልተከሰተላቸው፣ ሰዎች ሺሕ በሺሕ ከመርገፋቸው በፊት ካልባነኑና ይህንን የሚያስቀር ሚና መጫወት ካልቻሉ፣ እነሱም የንፅህና ሞራልም አፍም እንደማይኖራቸው ይወቁት! የደም ጥማታቸው የማይረካው ግፈኞች የት እንዳሉ ለማወቅ ከፈለጉ ወደ አውሮፓና ወደ አውሮፓ ከተሞች ይመልከቱ! የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሰላም ለማገዝ ከፈለጉም፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ከተሞች እየተንፈላሰሱ ሃሳዊ መረጃና የአዞ እንባ እየረጩ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የጠመንጃ የሽብር ትግል መረባቸውን ከሰላማዊ ትግል ጋር አዳብለውና የሥውር መንግሥት ዓይነት ባህሪ ይዘው የጋጋታ ሠራዊት የሚያንቀሳቅሱ የፍጅት መሐንዲሶችን በደንብ ያስተውሉ!

ኦሮሞም የአሁኑ ከሰልና አመድ ላይ ቆመህ ንቃ! ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ነው… የዓላማ ልዩነት የለውም›› እያሉ የቂማቸውና የበቀላቸው ፈረስ ሊያደርጉህ ጆሮህን ከግራ ቀኝ ሐሳቦች ሊከልሉ ሌት ተቀን የሚለፉትን፣ የጥላቻና የበቀል ዓላማቸውን የሚቃረን አቋም ይዞ ብቅ የሚል ኦሮሞን በግድያ የሚያወራርዱ፣ አለዚያም ‹‹የነፍጠኛ/አሃዳውያን መሣሪያ›› እያሉ የሚቀጠቅጡ ፀረ ዴሞክራሲ ቆሞ ቀሮችን በደንብ አስተውል!

የኦሮሞ ሕዝብ ግፍ እየተዋለብህ መሆኑንም እወቀው! ግፍ ስል፣ ከወንድም ሕዝብ ጋር እንድትፋጅ እየተሠራብህ ስላለ ደባ፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን በማጋየትና ሌሎች ዕድሎችን ከቱሪዝም ጭምር በማስደንበር በሥራ ዕድሎች ረገድ እየተሠራብህ ስላለ በደል ወይም ሃጫሉ ሁንዴሳን የመሰለ ጀግና ስለማጣትህ እያወራሁ አይደለም፡፡ ከዚያ ጋር ለማወዳደርና ለማበላለጥ ስለማይመች ግፍ እያወራሁህ ነው፡፡ ከአብራክህ የወጡ ወጣት ልጆችህን ለአሮጌ ጥላቻና በቀላቸው መሣሪያ ለማድረግ፣ ለጋ ህሊናቸውን በጭካኔ እየመረዙ፣ የአዛውንት አክብሮታቸውን፣ ርህራሄያቸውንና ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ታዛዥነት እየደመሰሱ በሰብዕናቸው ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ልብ በል! የልጆችህን ለጭካኔ ፖለቲካ ዱላና እሳት መሆን እምቢ በል! የሞት አይፈሬው ሃጫሉ ሕይወት የተቀጠፈው፣ ልጆችህን በቁጣ አስክሮ የፅንፈኞች በቀል ማቀጣጠያ ክብሪት ለማድረግ መሆኑን በምን አንጀት ትሸከመዋለህ!? በሃጫሉ መገደል ‹‹ተንገበገብን›› የሚል ተውኔት በሚዲያ እየሠሩ የኦሮሞ አፍላ ወጣትን በንፁኃን ላይ ያዘመቱ ወንጀለኞችን እንደምን ጎሽ ልትላቸው ትችላለህ!? አፍላ ልጆችህ በቁጣ እንዲያብዱ ተደርገው እናት አባቶችን እንዲቀጡ የተደረገበትን የጉድ ገመና ምን ከምን አድርገህ ታነፃዋለህ!?

ሃጫሉ ሁንዴሳን ማንም ገደለው ማን፣ የእሱን ሕይወት ሰውቶ ‹‹ነፍጠኛ›› የሚል ስም በተለጠፈባቸው ውጥንቅጦች ላይ ወጣት ኦሮሞዎችን ለማዝመት፣ ከፋፍሎ አፋጂዎች ሰኔ ውስጥ ተሳክቶላቸዋል፡፡ ነገም ሌላ ታዋቂ ዝነኛ ሰው ከወዲህም ሆነ ከወዲያ ገድለው በቁጣ አሳብዶ የማፋጀት ሌላ ድል ለማጣጣም መሞከራቸው አይቀርም፡፡ በሰኔው የአፋጂዎች በቀል ተሸናፊዎቹ፡- የፌዴራልና የኦሮሚያ መንግሥታዊ አካላት፣ የፀጥታ ኃይሎች፣ ኦሮሞዎችና በጉያቸው ያሉ ውጥንቅጦች፣ የታሪክ ባለሙያዎችና ዴሞክራት ፖለቲከኞች ናቸው፣ ለምን? ምክንያቱም በቀለኞች ለብቀላ የሚነግዱበትን ትርክታዊ ጥላቻና መሸካከር ባለማጠባቸው፡፡ ይህ ክፍተት እስካለ ሽንፈታቸው ይቀጥላል፡፡ ሽንፈቱ ብዙ ኃይሎችን ይመልከት እንጂ በዋናነት የሚያጎድፈው (በቱግታ ተነድቶ ሰቅጣጭ ግፍና ጅምላ ቅጣት በንፁኃን ላይ ፈጻሚ ተደርጎ የሚታየውን) የኦሮሞ ወጣት ነው፡፡ የኦሮሞ ወጣት መጉደፍ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ መጉድፍ ነው፡፡

ሐፍረት የለሾቹ በቀለኞች ለብዙ ዓመታት በተሠራበት ትርክት ራሳቸው መታወራቸው ሳያንስ ዓይነ ቢስነታቸውን ወደ ኦሮሞ ውሱን ወጣቶች አጋብተውና የሆነ ክብሪት እየጫሩ ግርታ በማስነሳት ኦሮሞነትና የግርታ ጭካኔን እንዲዛመዱ ካደረጉ ውለው አድረዋል፡፡ የምኒልክ ጊዜ የነፍጠኛ ዘመቻን ኦሮሞ ያልነበረበት አስመስለው በ‹‹አማራ›› ላይ ብቻ እየላከኩ፣ በምኒልክ ጊዜ ተፈጸመ የሚሉትን ግፍ ራሳቸው ዛሬ በንፁኃን ላይ እያስፈጸሙ፣ የኦሮሞን ታሪክ የግፍ ቀለም ቀቡ፡፡ የሞጋሳና የጉዲፈቻ ባለፀጋነቱን እየረጋገጡ የግፍ ጉድፍ አለበሱ፡፡ አልቤርጎው እየተንኳኳና ‹‹ውጣ!›› እየተባለ ወጥቶ፣ ጆሮው በዋይታ እየተዋከበ ዘመናዊ ሆቴሎችና ሌሎች ተቋማት ነዳጅ ተርከፍክፎባቸው እሳት ሲለኮሱ ያየ ቱሪስትም፣ አገሩ ሄዶ የሚጽፈው ይህንኑ ማፈሪያነት ነው፡፡ እናም፣ ለኦሮሞ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ጥቃት እንንገበገባለን ባይ በቀለኞች፣ ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የበቀል ግፋቸውን በኦሮሞ ስም ላይ ላክከው፣ ድንጋይ ጠርቦና አሸዋ አላቁጦ ቅርፅ ማውጣት የማያሻው የግፍ ሐውልት አቆሙበት፡፡ ለኦሮሞ እናስባለን ባዮቹ የጥላቻ በቀለኞች በእሳትና በገጀራ ያስገኙለት ትርፍ ይህ ነው፡- ታሪክ ማበላሸት፣ ልጆቹን በጥላቻና በበቀል መርዞ ከሰው የተፈጠረ የማያደርገውን ሥራ ማሠራት፡፡ የተሳካላቸውን ያህል ቀዬና ከተሞቹን የልቅሶ፣ የፍርስራሽ፣ የዓመድና የክስልሳይ ባለሀብት ማድረግ፡፡ እናሳ፣ ከኦሮሞ አብራክ የተፈጠሩ የበቀል ታጋዮች ኦሮሞን እየጠቀሙ ነው ወይስ እየቀጡት?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...