Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተገልጋይ ንጉሥ ነው

በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል በርካታ ምሬት የሚደመጥባቸው በርካታ ተቋማት አሉ፡፡ ግልጽነት የሰፈነበት አሠራርና ቅልጥፍና ብርቅ የሆኑባቸው፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸው ግድፈትና ክፍተት ተልክቶ አጥፍታችኋልና አስተካክሉ የሚላቸው ተቆጣጣሪ ያጡ ተቋማትን በስም እየጠቀስን እገሌ የተባለው ተቋም እንዲህ ያለ ነገር ያደርጋል፣ ያኛው ድርጅት ይህን ያለ ነገር ይፈጸማል በማለት ጣታችንን የምንቀስርባቸው በርካቶች ናቸው፡፡

በደንብና በሕግ የተቀመጡ አሠራሮችን በአግባቡ ለመተግበር ተነሳሽነቱና ቅንነቱ፣ የአገልጋይት ጠባይን ከመልካም ሥነ ምግባራዊ ሰብዕና የተባለሱ ሠራተኞችን ማየት እንደ ሉሲ ብርቅዬ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዳሻቸው ሊሆኑበት መብት የሰጣቸው የሚመስሉ፣ አገልግሉ ተብለው የተቀመጡ ባለሙያዎች እንኳንና አገልግሎታቸውን ፈልጎ ለሚመጣው ቀርቶ ለሚቀመጡበት ወንበርና ለሚውሉበት የሥራ ቦታ የማይመጥኑ፣ እንዲሁ የሌሎችን ዕድልና አጋጣሚ ተሻምተው የተሰገሰጉ በርካቶች እዚህም እዚያ ተኮልኩለው ማየት ቀላል ነው፡፡

የተገልጋይን መብት በመግፈፍ፣ እንደ ሕዝብ ስልክ ገንዘብ ካልተጣለባቸው፣  ጉቦ ካልተወሸቀላቸው ሁለት መስመር ጽፈውና ፈርመው ለሚሰጡት ወረቀት የዓመት ፍዳ የሚያስቆጥሩ ሠራተኞችና ደንዳኔ ሹማምንት ዛሬም በየተቋማቱ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከሁሉ በላይ በመንግሥት የወጡ መመርያዎችን በአግባቡ የማይፈጽሙና ተገልጋዮችን በምሬት ጭራ የሚያስበቅሉ፣ የመንግሥትን ስም የሚያጠለሹ ተቋማትና ሠራተኞች ጉዳይ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡

ተገልጋዮችን በቅንነትና በታማኝነት ለማስተናገድ የሚተናነቃቸው፣ ተጧሪ የመንግሥት ተቋማትና ሠራተኞቻቸው በግልጽ የተቀመጡ መመርያዎችን ወደ ጎን እያሉ ተገልጋዩን በማጉላላትና ላልተገባ ወጪ በመዳረግ አልፈው፣ እንግልት ያንገሸገሸገውን ባለጉዳይ ለጉቦ በተዘረጋ ሥርዓት ጉዳዩ እንዲፈጸምለት የሚገፋፉ፣ ‹‹በእጅ›› የማይሄደውን በሄደበት እያስቀሩ፣ ባለእጁን በመጣበት ፍጥነት ሸብረብ እያረገዱ የሚያስተናግዱ ሸፍጠኞች የሚመለከታቸው አላገኙም፡፡

እንዲህ ጉዳይ ለማንሳት የወደድሁት ከጥቂት ወራት በፊት ከኮሮና ጋር በተያያዘ አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሠራሮች ላይ ጥቂት ማስተካከያዎች ተደርጎባቸው  ለተገልጋዮች ፋታ በሚሰጥ አግባብ እንዲንቀሳቀሱ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተምታታ አሠራር ተስተውሏል፡፡

እንደ ምሳሌ ማንሳት ካስፈለገ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣንን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ይህ ተቋም ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የተሽከርካሪዎችን ደኅንነት ያረጋገጠ መረጃ ሲቀርብለት ቦሎ መስጠት አንዱ ሥራው ነው፡፡ ከወራት በፊት የ2012 ዓመታዊ የተሽከርካሪ ምርመራ፣ ምዝገባና ተለጣፊ ምልክት ለማግኘት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ለመፈጸም አገልግሎቱን ወይም ቦሎውን ለማግኘት የቀረቡ ተገልጋዮች ግን ‹‹በኮሮና ምክንያት አሁን ሥራው ቆሟል፡፡ ስንጀምር ትመጣላችሁ፤›› ይባላሉ፡፡

ይህንኑ የተሰጣቸውን ምላሽ በመያዝ ሥራው የሚጀመርበትን ጊዜ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሥራው ዳግም መጀመሩ በመገለጹ አገልግሎቱን ለማግኘት ሲሄዱ የጠበቃቸው መስተንግዶ በወቅቱ አልከፈላችሁምና ትቀጣላችሁ የሚል ነበር፡፡

ተገልጋዮቹ የግል ተሽከርካሪ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ለዚህ አገልግሎት ከሚጠየቀው በላይ ቅጣት ክፈሉ መባላቸው የሚገርም ነው፡፡ መደበኛ ክፍያው 250 ብር ሆኖ ሳለ፣ መቀጫው ብቻውን ግን ከ300 ብር በላይ ሆኗል፡፡ ባለጉዳዮቹ አገልግሎቱን ማግኘት በሚጠበቅባቸው ወቅት ሄደው አገልግሎት ሲጠይቁ አናስተናግድም ተብለዋል፡፡ ይህን ያደረገው ተቋም ችግሩን የተገልጋዮቹ ጥፋት እንደሆነ በማድረግ የፈጠረው ትርምስና ኪሳራ የብልሹ አሠራር ሥርዓት አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በኮሮና ቫይረስ ሥጋት ምክንያት በተቋሙ የተወሰደው ዕርምጃ ተገልጋዩን ተጎጂ አድርጎታል፡፡ አገልግሎቱን በራሱ ያቋረጠው ተቋም፣ ባሻው ወቅት ወደ ሥራው ሲመለስ ተቀጡ፣ ተመለጡ ማለቱ የጉድ ነው፡፡ ለተፈጠረው መዘግየት ተገልጋዩ ተጠያቂ መሆን አልነበረበትም፡፡ ቅጣቱ የግዴታ ይከፈል ቢባል እንኳ፣ የመቀጮው ገንዘብ መጠን ከመደበኛ ክፍያ በላይ መደረጉ ምን ይሉት አሠራር ነው?

ይህ እንደ ምሳሌ ተነሳ እንጂ ለኮሮና በማያጋልጥ መንገድ ይተግበሩ የተባሉ አንዳንድ መመርያዎች በቅጡ መሬት ላይ አልወረዱም፡፡ በአግባቡ መመርያዎቹን ለመተግበር ካለመቻልና ከግንዛቤ ማነስ ሳቢያ የተፈጠረ ችግር የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ የወጣው መመርያ ገብቶት ማስፈጸም እየቻለ ያልተገባ ተግባር ላይ የሚገኙ ግለሰቦችም ሆነ ብለው እንደሚያበላሹ እንረዳለን፡፡

ስለዚህ ሥር ነቀል ለውጥ የሚሹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ አትኩሮት ሰጥቶ በመከታተል እንዴት እየሠሩ እንደሆነ መቆጣጠሩ ተገቢ ነው፡፡ ተገልጋዩ በቂ መረጃ እንዲኖረው ማድረግ ያሻል፡፡ ሥራ የሚለካው መመርያ በማውጣት ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ትራንስፖርት ቢሮ ያሉ በርካታ ተገልጋዮች የሚተራመሱባቸው ተቋማት፣ የሚታሙት ከሰሞኑ በታየው ችግር ብቻ እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ ሌሎችም  ሰንኮፋዎች አሉባቸው፡፡ ማሻሻያዎች ተደርገውባቸዋል የተባሉ መመርያዎችና ማስፈጸሚያ ስልት የተቀመጠላቸው አሠራሮች ወደ ተገልጋዩ የሚደርሱበት አግባብ ከወንዝ ማዶ ሲሆን መታየቱ የዲጂታል ዘመን አሠራር አይመስልም፡፡

ከላይ የጠቃቀስነው ጉዳይ ከአንድ ሳምንት በፊት የተከሰተ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ተቀይረዋል፡፡ አዳዲሶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ተመልክተው ሊያስተካክሏቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ነው፡፡ የትኞቹ ተቋማት የመንግሥትን ሕግና መመርያ በአግባቡ እየተረጎሙ ነው ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ የተገልጋዩን ችግር ማድመጥ ይገባል፡፡

ዜጎችን የተቃና ቀልጣፋ አገልግሎት የማግኘት መብት የሚጋፉና ሮሮ የሚስተጋባባቸው ተቋማትን በመለየት የተሻለ አሠራር እንዲሰፍንባቸው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር የወረሳቸውን ተቋማት ሕዝቡ እንዲጠቁም በማድረግ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲሱ አመራር በኩል ትኩረት ያሻቸዋል በማለት ከምንጠቁማቸው ጉዳዮች መካከል አንዱም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ በረባ ባልረባው፣ በቅንነት ባጣ መንገድ ተገልጋይን ቁም ስቅል ማሳየት የሚቀናቸውን ተቋማት አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ከአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹነት ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ለዘመናት ሲንከባለል የመጣ በመሆኑ በአንድ ጀምበር ለውጥ አይናፈቅም፡፡ ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› እንደሚባለው፣ ከሥር ከሥሩ መፍትሔ የሚፈልጉ ችግሮችን ለይቶ መንቀሳቀስ መቻል ለተገልጋዩ ዕፎይታን ሊያስገኝ እንደሚችል በማጤን፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጋር የሚደመጡትን ቅሬታዎች መቀነስና ማስተካከል ትኩረት ይሰጠው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት