Wednesday, June 19, 2024

የፖለቲከኞች ፉክክር የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ይሁን!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን የሚችሉት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብን ሲያከብሩ ብቻ ነው፡፡ ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ማስገዛት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ማዕከል ማድረግ ካልተቻለ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ሊኖር አይችልም፡፡ በተለይ የመንግሥትን የሥልጣን ልጓም የጨበጠው ኃይል ከፍተኛ ኃላፊነት ሲኖርበት፣ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚፎካከሩ ፓርቲዎችም የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአምባገነናዊ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያደርገው ሽግግር እየተስተጓጎለ ያለው፣ ኃላፊነት በማይሰማቸው ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሆነ በተደጋጋሚ እየታየ ነው፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድርን ችላ በማለት የጉልበት መንገድ የሚመረጠው ለሕዝብ ፍላጎት ክብር ለመስጠት ስለማይፈለግ ነው፡፡ የተወሰነ ቡድንን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረግ ትንቅንቅ በስሙ የሚነገድበት ሕዝብ ወደ ጎን ይገፋል፡፡ በሕግ ዕውቅና ያገኘው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በግላጭ እየተደፈጠጠ፣ የጥቂቶች ድምፅ ከመጠን በላይ እያስተጋባ ችግር ይፈጠራል፡፡ ለሁሉም የምትመች የጋራ አገር ለመገንባት የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እየተደናቀፈ፣ ጥቂቶች አብበውና ጎምርተው የሚወጡበት ምኅዳር ለመፍጠር የሚደረገው አሻጥር በአገር ላይ ችግር ይዞ ይመጣል፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ አጉል ድርጊቶች ሕዝብን በመናቅ የተከናወኑ ስለሆኑ፣ ከቅራኔና ከውድመት የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡

ከዚህ ቀደም የሚወገዙ ድርጊቶች በዚህ ዘመን ሲደገሙ ማየት ‹ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ› የሚባለውን ምሳሌ ያስታውሳሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት የብዙኃኑን ሕዝብ ቅቡልነት ያገኘው፣ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ የሚያሸጋግሩ ተስፋዎችን ሰንቆ በመነሳቱ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ በይፋ ሹመታቸው ከፀናላቸው በኋላ ባደረጉት አስደማሚ ንግግር፣ ቆየት ብሎም በዘመነ ኢሕአዴግ የተፈጸሙ አሳዛኝ ድርጊቶችን በማውገዝና ይቅርታ በመጠየቅ በገቡት ቃል መሠረት መንግሥታቸው ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱ አይረሳም፡፡ ከዚያም በኋላ ለለውጥ የሚያግዙ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም መንግሥታቸው ሽግግሩን በሰላም መርቶ ወደ ፍትሐዊና እውነተኛ ምርጫ በማድረስ፣ ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊና ከጉልበተኝነት አባዜ እንድትላቀቅ ለማድረግ እምነት ተጥሎበት ነበር፡፡ ነገር ግን በመሀል የንፁኃንን ውድ ሕይወትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ያስከተሉ አሳዛኝ ጥቃቶች በተለያዩ ኃይሎች ተፈጽመዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ላይ ሕግ እንዲያስከብር ከማሳሰብ ያለፈ የከረረ ተቃውሞ አልገጠመም፡፡ ይሁንና በምልዓት የታየው ድጋፍ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሸርሽሯል፡፡ ሕግ በማስከበር ስም አላስፈላጊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ከሕዝብ ጋር ቅያሜ እየተፈጠረ ነው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ባልደራስ በመባል የሚታወቀው ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳዮች ላይ የጠራቸው ስብሰባዎችም ሆኑ ጋዜጣዊ መግለጫዎች፣ በሕገወጥነት ተፈርጀው በተደጋጋሚ ታግደዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የፓርቲው የምሥረታ ጉባዔ እንዳይከናወን በመታገዱ ጎዳና ላይ መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ ግለሰባዊ ጥላቻ እስኪመስሉ ድረስ በአመራሮቹ ላይ በተደጋጋሚ ጉንተላዎች፣ ማወከቦችና የመሳሰሉት ከመድረሳቸውም በላይ ከለውጡ መንግሥት የማይጠበቁ ድርጊቶች ተስተውለዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አሰጣጥና የመሬት ወረራን በተመለከተ ጥናት ያሠራው ኢዜማ፣ ለጋዜጠኞች ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ በፖሊስ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡ መንግሥት ፓርቲው በባለሙያዎች ያሠራውን ጥናት ተመልክቶ የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ ሲገባው፣ ፈቃድ የሌለው ስብሰባ ነው በማለት ጋዜጣዊ መግለጫውን ማስተጓጎሉ ያስገርማል፡፡ ይህ ሕጋዊ የመደራጀት መብትን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትንና የሕዝብን መረጃ የማግኘት መብትን የሚጋፋ ዕርምጃ ነው፡፡ እንዲያውም ጥናቱ ደረጃውን የጠበቀና ተገቢውን መሥፈርት ያሟላ እንደሆነ ማረጋገጥ ሲገባ፣ አደባባይ መውጣት የሌለበት ሚስጥር ለመደበቅ የተደረገ ዕርምጃ አስመስሎታል፡፡ መረጃው ይፋ ሲደረግ ራሱ መንግሥት ጭምር ተጠቃሚ ይሆንበታል ተብሎ ሲታሰብ፣ ጭራሽ ይፋ እንዳይሆን ለማከላከል መሞከር በእርግጥም መድበስበስ ያለበት ሚስጥር አለ ማለት ነው በማለት ሕዝብ ግንዛቤ ይይዛል፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የጎደላቸው ብልሹ አሠራሮች የሰፈኑበት ሥርዓት ውስጥ እንደሚኖርም ያስባል፡፡ በዚህ ምክንያት በምሬት በመንግሥት ላይ ይነሳል፡፡

ከአምባገነናዊ አስተሳሰብ ሳይላቀቁ ለውጥ እናካሂዳለን ለማለት አይሞከርም፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጣለው አንዱ ፈቃጅ ሌላው ጠያቂ በሆነበት ዕሳቤ አይደለም፡፡ ገዥው ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበት አሠራር በግልጽ ሊኖር ይገባል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ውስጡን እየፈተሸና እያጠራ፣ ከአድሎአዊ አሠራሮች ራሱን እያራቀ፣ አመራሩንም ሆኑ አባላቱን ከሌብነትና ከዝርፊያ እያስወገደ፣ ከምንም ነገር በላይ ሕዝብን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር እያከበረና በንፅህናና በታማኝነት ከሠራ የሚሸፋፍነው ነገር አይኖርም፡፡ እንዲያውም ከሌሎቹ ተፎካካሪዎቹ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በአርዓያነት ማሳየት ይገባዋል፡፡ እየተስዋለ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ እየሆነ ነው፡፡ የተፎካካሪን ማናቸውም ዓይነት ሕጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማወክና የሕዝብን የማወቅ መብት መጋፋት፣ ለውጡ የተነሳበት ዓላማ ካለመሆኑም በላይ መጪውን ጊዜ አደገኛ ያደርገዋል፡፡ የለውጡ ዓላማ ከአምባገነናዊ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ለማቀላጠፍ እንጂ፣ የተለመደውን የጉልበተኞች መፈንጫ ለማመቻቸት እንዳልሆነ ማስታወስ የግድ ይሆናል፡፡ አሁንም መንግሥትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ ሕዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ፣ የተፈጸመውን አላስፈላጊ ድርጊት ማረም ይኖርበታል፡፡ የሚያዋጣውም ይኸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት መልካም ዕድሎች ሲያጋጥሟት እየተበላሸባት የምትቸገረው፣ በእኩልነትና በመተባበር የተሻለ ሥርዓት ለመገንባት ጥረት ከማድረግ ይልቅ የአንድ ወገን የበላይነት ለማስፈን መራኮት ስለሚፈለግ ብቻ ነው፡፡ ለአገር ግንባታ መዋል ያለበት የሰው ኃይል፣ ሀብትና ጊዜ ለተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦች እየዋለ ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ እንዲበላሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ጠንካራ ፓርላማ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የፍትሕ አካላት፣ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ሚዲያና የመሳሰሉት ሊፈጠሩ ያልቻሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሥልጣን የሕዝብን ተዓማኒነት ባተረፈ ምርጫ መያዝ ያልተቻለውና ጉልበተኝነት የተመረጠው በዚህ ሳቢያ ነው፡፡ ያለፉ አሳዛኝ ስህተቶችና የክፋት ድርጊቶች አገሪቱን ምን ያህል እንደ በደሏትና ሕዝቡንም እንዳሰቃዩት በሚገባ ይታወቃል፡፡ መፍትሔው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አማካይነት ዴሞክራሲን ማፅናት እንደሆነም ግልጽ ነው፡፡ ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ ወይም ከጉልበት ሲመነጭ አገር የጥቂቶች መጫወቻ እንደምትሆን ለኢትዮጵያዊያን አዲስ አይደለም፡፡ የፈቃጅነትና የከልካይነት አባዜ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፀር ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ እያደር እየጠበበ የሚሄደው አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ ሲሆኑ ነው፡፡ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ትግል የማይመች የአፋኝነት ባህሪ መላበስ ተቀባይነት የለውም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለሁሉም እኩል መሆን አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ሰላማዊው የፖለቲካ ዓውድ ወደ ጦርነት ለመለወጥ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ይህ ደግሞ ለአገርም ለሕዝብም ከባድ ኪሳራ ነው፡፡

አሁንም በድጋሚ ለማስገንዘብ የሚፈለገው ካለፉት ስህተቶች መማር እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ሥልጣኑን ለማጠናከር ሲል ብቻ ያልተገቡ ድርጊቶችን ሲፈጽም፣ ተፎካካሪዎችም ለአፀፋ ምላሽ ስለሚዘጋጁ የሚፈለገው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ይደናቀፋል፡፡ መልካም ዕድሎችን በማበላሸት ወደር የሌለው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ታሪክ የሚያስገነዝበውም ይህንን ነው፡፡ ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ የሚገኝበት የጉልበተኝነት መንገድ መዘጋት አለበት፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በነፃነት የፈለገውን የሚመርጥበት ምኅዳር ማመቻቸት ይገባል፡፡ የሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ ዕውን እንዲሆን ለብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በቅራኔ ውስጥ ተሁኖ የጋራ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳር ማዘጋጀት ያዳግታል፡፡ ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት የማይገዛ የሴራ ፖለቲካ ትርፉ መፋጀት ነው፡፡ የአሳዳጅና የተሳዳጅ የፖለቲካ መንፈስ መወገድ አለበት፡፡ ለሕዝብ ዳኝነት በመቅረብ የአሸናፊነትን መንበር መቀዳጀት የመሰለ ሥልጡን አካሄድ እያለ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ‹ዓይንህን ለአፈር› የሚያሰኝ ኋላቀር ድርጊት ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሚቻለው የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ነው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ራሳቸውን ከሴራ፣ ከቂም፣ ከጥላቻ፣ ከስግብግብነትና ከጉልበተኝነት አባዜ ያላቁ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን የሚያዋጣው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ግድያና ውድመት ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የፖለቲከኞች ፉክክር የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ማድረግ ያለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...