የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የጥናት ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሐዊ ዕደላን አስመልክቶ ጥናት ባደረገባቸው አምስት ክፍለ ከተሞች ውስጥ ከ200 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ መሬት በሕገወጥ መንገድ መወረሩን አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ይህን ጥናቱን ይፋ ያደረገው ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ዓርብ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲሁም ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን ጠዋት በራስ ሆቴል በጉዳዩ ዙሪያ ሊሰጠው የነበረው መግለጫ በፖሊስ መከልከሉ የሚታወስ ነው፡፡
የፓርቲው ጥናት ከመሬት ወረራው በተጨማሪ ኢፍትሐዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላን በተመለከተ የዳሰሰውንም ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች ቦታና የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተሰጣቸው መሆኑን በማስታወስ፣ በአሁን ወቅት ደግሞ ድጋሚ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየታደላቸው መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ከዚህ አንፃር ‹‹ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች ሳር ቤት አካባቢ ከሚገኘው ጽሕፈት ቤት ሁሉም የተመዘገቡ ሠራተኞች በሰኔ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. 20,000 ቤቶች የድልደላ ዕጣ የወጣላቸው ሲሆን፣ የድልድል ዕጣ ለደረሳቸው ሰዎች ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ድልድል ተደርጎላቸዋል፡፡ በዚሁ ቀን ሁሉም ሠራተኞች የኮንዶሚኒየም ብሎክ ቁጥርና የቤቱን ቁጥር በስማቸው ተረጋግጦ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በተሰጣቸው የቤት ቁጥር የነዋሪነት መታወቂያ የተዘጋጀላቸው መሆኑን ለማወቅ ችለናል፤›› በማለት ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር የተያያዘውን የጥናቱን ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንፃዎች ውስጥ የተሠሩ የንግድ ቤቶችን በተመለከተ ደግሞ ‹‹የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች፣ ልጅና የልጅ ልጅ ተብለው በገፍ ስለመታደላቸውና በእግር ኳስ ደጋፊነት ስም ለተሰባሰቡ ማኅበራት መከፋፈላቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች ተገኝተዋል›› በማለት ጥናቱ የደረሰበትን ግኝት ይፋ አድርጓል፡፡
የመሬት ወረራ የተፈጸመባቸውና በጥናት ቡድኑ የተዳሰሱት አምስት ክፍለ ከተሞች ደግሞ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ የካ፣ ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲና ኮልፌ ቀራንዮ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 96,800 ካሬ ሜትር፣ በየካ ክፍለ ከተማ 58,000 ካሬ ሜትር፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ 15 ሺሕ ካሬ ሜትር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 22,500 ካሬ ሜትር እንዲሁም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ደግሞ 21,100 ካሬ ሜትር መሬት በሕገወጥ መንገድ እንደተወረረ በጥናቱ ማረጋገጡን ኢዜማ አስታውቋል፡፡
ከቅርብ ወራት ወዲህ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እጅግ እየተባባሰ የመጣው ‹‹የመንግሥታዊ መዋቅሮች ድጋፍ ያለው›› ሕገወጥ የመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሐዊ ዕደላ ለነዋሪዎች ከፍተኛ ሥጋት ከመፈጠሩ በተጨማሪ፣ ከነዋሪዎቿ በሚሰበሰብ ግብር እንደ መልማቷ ነዋሪዎቿ የተጠቃሚነት እንዲሁም የባለቤትነት ዋስትና እንደሌላቸው የሚያሳይ መሆኑን በጥናቱ አመላክቷል፡፡
ይህን ጥናት ማከናወን ለምን እንዳስፈለገ በሚገልጸው የጥናቱ ክፍል ደግሞ ‹‹ይህን ጥናት ለማድረግ መነሻ የሆኑት ገፊ ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው ከኅብረተሰቡ (የኢዜማ አባላትን ጨምሮ) የመሬት ወረራንና ሕገወጥ የቤት ዕደላን አስመልክቶ የተሰጡ ተደጋጋሚ ጥቆማዎች ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የተለያዩ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ሰፊ የዘገባ ሽፋን በመስጠት ስለጉዳዩ አሳሳቢነት ጠቅሰው መዘገባቸው ነው፤›› በማለት ጥናቱን ያሰናዳበትን ምክንያት ገልጿል፡፡
ጥናቱ በሚዘጋጅበት ወቅት በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፣ ዋነኛው ግን ‹‹በየትኛውም መዋቅር ላይ ያሉና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸው ነው፤›› በማለት አስታውቋል፡፡
ማብራሪያ ከተጠየቁት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል ‹‹በዋነኛነት የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ የጻፍንላቸውን ደብዳቤ ቢቀበሉንም ምላሽ ለመስጠትም ይሁን በአካል በመቅረብ ለማነጋገር የተደረገው ጥረት ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በተጨማሪም ለአዲስ አበባ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ መረጃ እንዲሰጡ የጥናት ቡድኑ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢጠይቅም፣ ደብዳቤውን ለመቀበል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤›› በማለት ከመንግሥት አካላት መረጃ ከማግኘት አንፃር የገጠሙትን ተግዳሮቶች ይፋ አድርጓል፡፡
የመሬት ወረራ በአገሪቱ አዲስ ያልሆነና በተለያዩ ጊዜዎችና አካባቢዎች ትልቅ ችግር ሆኖ መቆየቱን የሚገልጸው የኢዜማ ጥናት፣ ነገር ግን ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ በዚህ ደረጃና ፍጥነት የተስፋፋበት ጊዜ አልነበረም፤›› በማለት የችግሩን ጥልቀትና ስፋት አመላክቷል፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹የመሬት ወረራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ላይ እንደሚስተዋለው በአገልግሎት ላይ የሚውሉ ቦታዎች ስፋት ከፍተኛ ከመሆናቸውም በላይ፣ ወረራው የከተሞችን አረንጓዴ ቦታዎች፣ የወንዝ ዳርቻዎች እንዲሁም ለመሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታ በፕላን የተከለሉ ቦታዎችን ያካተተ ነው፤›› በማለት የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉ ጥናቱ አመላክቷል፡፡
በመጨረሻም ፓርቲው በዚህ ሕገወጥ ተግባር የተሳተፉ የሥራ ኃላፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ‹‹እስከዛሬ በነበረው ሥርዓት እንደሚደረገው በሥልጣናቸው ያለአግባብ የተጠቀሙና ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው ወይም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተጠቀሙ ባለሥልጣናት ከቦታቸው ገለል በማድረግ ወደሌላ ሥልጣን የሚዛወሩበት ሳይሆን፣ ላደረሱት ጉዳትና ለፈጸሙት ወንጀል በሕግ አግባብ የሚጠየቁበት ሥርዓት ሊበጅ ይገባል፤›› በማለት መንግሥትን ጠይቋል፡፡
ገዥው ፓርቲና መንግሥት ተገቢ የዕርምት ዕርምጃ የማይወስድ ከሆነ ግን ‹‹ኅብረተሰቡን በማስተባበር ሌሎች ሰላማዊ የትግልና የማስገደጃ መንገዶችን በመጠቀም የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታችንን የምንወጣ መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን፤›› በማለት ኢዜማ አሳስቧል፡፡