በሔለን ተስፋዬ
የአውሮፓ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያደረጉ ያሉትን ልዩ ልዩ ሥራ ለመደገፍ 2.5 ቢሊዮን ብር (60 ሚሊዮን ዩሮ) የሚገመቱ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ፡፡
ለክፍለ አኅጉራዊው ድርጅት ኢጋድ አባል አገሮች የሚሠራጨውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን በኢትዮጵያ በኩል እንዲደርስ ርክክቡ የተደረገው ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡
ድጋፉ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚያደርጉት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴና መርሐ ግብር የሚውል መሆኑ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተወስቷል፡፡
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ከኅብረቱ የተበረከተው ድጋፍ በክፍለ አኅጉሩ ያለውን የኮቪድ-19 መመርመርያ፣ ቅድመ መከላከያና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት ይቀርፋል፡፡ አገሮቹም የተቀናጀ የመከላከል ሥርዓት እንዲኖራቸው ያግዛል፡፡
ማኅበረሰቡን ከወረርሽኙ ከመታደግ ባለፈ ተጋላጭ ለሆኑት የሕክምና ባለሙያዎችንም የደረሰ ድጋፍ መሆኑንም ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት እንዳስታወቀውም ድጋፉ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለይም ለአገር ውስጥ ለውጭ ተፈናቃዮች እንዲሁም ለስደተኞች የሚውል ይሆናል፡፡
ኅብረቱ ከሰጣቸው የመከላከያ ቁሳቁሶች መካከል 3.5 ሚሊዮን ሰርጂካል ማስኮች 3.5 ሚሊዮን ጓንቶች፣ 700 ሺሕ የፀጉር መሸፈኛዎች፣ 35 ሺሕ የፊት መከለያዎች፣ 14 ሺሕ የጫማ መሸፈኛዎች ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም 16 ደረጃቸው የተጠበቀ አምቡላንሶች፣ ሙሉ የሕይወት ድጋፍ የሚሰጡ ስምንት አምቡላንሶች የመስክ ተሽከርካሪዎችም ተበርክተዋል፡፡
በርክክቡ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የመጀመርያው ዙር ድጋፍ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት ለየአገሮቹ እንደሚደርስ አስታውቀዋል፡፡