በሱዳንና በዳርፉር አማፅያን መካከል የሰላም ስምምነት ለማድረግ ለዓመታት ውይይት ተደርጓል፡፡ ሆኖም ውይይት ሳይሆን ጦርነቱ የፈታቸው ለመንግሥትና ለአማፅያን የወገኑ ታጣቂዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያንን ሕይወት ቀጥፈዋል፡፡
ላለፉት 17 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ግጭትም ዳርፉር መኖሪያ ሳትሆን የሱዳን ስደተኞች መጠለያ ሆናለች፡፡ ዳርፉር ሴቶች የሚጠለፉባት፣ የሚደፈሩባት፣ ሕፃናት የሚሰቃዩባት ሰላም ያጣች አካባቢ ናት፡፡ በስደተኞች መጠለያ ያሉ ዜጎችም የጥቃት ሰለባት የሆኑባት፣ ረሃብና በሽታ የሚፈራረቅባቸውና ለሰብዓዊ መብት ጥሰትም ተጋላጭ ሆነው ዓመታትን ያስቆጠሩባት ሥፍራ ናት፡፡ በዳርፉር በባህልና በእምነት ልዩነት ሰዎች የሚሰቃዩበትና የሚሞቱበትም ነው፡፡
ይህ የእርስ በርስ ግጭት ያበቃ ዘንድ፣ የአካባቢው ሕዝብም በሰላም እንዲኖር ለማስቻል የተለያዩ ውይይቶች ቢደረጉም በሱዳን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሐሰን አልበሽርና በዳርፉር አማፅያን በኩል ስምምነት መድረስ አልተቻለም፡፡ በአመፅ ከሥልጣን የተነሱት አልበሽርም ከተጠየቁባቸው ጉዳዮች አንዱ በዳርፉር ለደረሰ ጭፍጨፋ እጃቸው አለበት የሚል ነው፡፡
የቀድሞ ፕሬዚዳንት አልበሽር ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ የተቋቋመውን የሽግግር መንግሥት የሚመሩት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ መንግሥት፣ ትልቁን የአማፂ ቡድን የሚይዘውን ዳርፉርን ጨምሮ ከአምስት ታጣቂ ቡድኖች ጋር የሰላም ስምምነት አድርጓል፡፡
አልጀዚራ ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. የሱዳን መንግሥት ከዋና ዋና አማፂ ቡድኖች ጋር በደቡብ ሱዳን ጁባ ያደረገውን ስምምነት አስመልክቶ እንደዘገበው፣ ስምምነቱ ከዚህ ቀደም ሲያጫርሷቸው ለከነበሩ ቁልፍ ችግሮች መልስ የሰጠ ነው፡፡
የደኅንነት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ ከግጭት ወደ ሰላም የመሄዱን ሒደት ፍትሐዊ ማድረግ፣ የሥልጣን ክፍፍል እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተሰደዱ ሱዳናውያን መልሶ ማቋቋምን ያካትታል፡፡
የአማፂ ቡድን አባላትን ትጥቅ ማስፈታትና ከአገሪቱ መከላከያ ጋር ማዋሃድ የሚለውንም ያካተተው ስምምነት፣ በሽግግር ላይ ያለው መንግሥት ሥር የሰደደውን የሱዳናውያን የእርስ በርስ ግጭት ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሏል፡፡
የሱዳን ሪቮሊውሽነሪ ፍሮንት፣ የምዕራብ ዳርፉር አካባቢ አማፂ ቡድን፣ የደቡብ ኮርዶፋን አማፂ ቡድንና ብሉ ናይል አማፂ ቡድን እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ በደቡብ ሱዳን አደራዳሪነት ሲያካሂዱ የነበረውን ውይይት በሰላም ስምምነት መፍታታቸውም የሽግግር መንግሥቱ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለመምታት እንደሚያስችለው አልጀዚራ አስፍሯል፡፡
የዳርፉር አማፂያን መሣሪያ ካነሱበት እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ ከ300,000 በላይ ሱዳናውያን የተገደሉ መሆናቸውን የባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
በካርቱም መንግሥት የኢኮኖሚና የፖለቲካ አድሎና መገለል ተደርጎብናል የሚሉት ሱዳናውያን ከገቡበት ጦርነት ወጥተው ወደ ሰላም መምጣታቸውን አሜሪካ፣ እንግሊዝና ኖርዌይ በጋራ ባወጡት መግለጫ ደግፈውታል፡፡ በሱዳን የተረጋጋ ሰላም ለማስፈን የመጀመርያ ደረጃ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክን ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮች ስምምነቱን ለማድረግ ደቡብ ሱዳን ጁባ ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ጋር እንደተገናኙም ሱና ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክና የሱዳን መሪ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እንዲሁም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በተገኙበት የአማፂ ቡድኖቹ መሪዎች የሰላም ስምምነቱን መፈራረማቸው ከዚህ ቀደም ላለመስማማት ምክንያት የነበሩ ችግሮች መቀረፋቸውን ያመላክታልም ተብሏል፡፡
አማፂ ቡድኖቹ ከስምምነት የደረሱት ከፍላጎታቸው አብዛኛው የተሟላ በመሆኑ እንደሆነ፣ ከዚህ ቀደም ስምምነት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች ውስብስብ እንደነበሩ አሁን ላይ ግን አስተማማኝ ስምምነት መደረጉ ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክና መንግሥታቸው በሱዳን ጉልህ ለውጥ ማምጣት እየቻሉ ነውም ተብሏል፡፡ ባለፈው ወር በሱዳን ለ40 ዓመታት በሥራ ላይ የነበረውን አልኮል የመጠጣት ገደብ፣ ሙስሊም ያልሆኑ አማኞች እንዲጠቀሙ ክልከላውን እንደሚያነሳም አሳውቋል፡፡
የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቀርና ሌሎች አሳሪ ሕጎች እንዲላሉ እየሠራም ሲሆን፣ ይህም ሱዳንን ከአሜሪካ የአሸባሪ መዝገብ ለማሰረዝና የተጣሉ በርካታ ገደቦችን ለማስነሳት ያስችላል ተብሏል፡፡