Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ኢንቨስትመንት የታክሲ አገልግሎት ተጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሔለን ተስፋዬ

በ2.9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ዘርፈ ብዙ የትራንስፖርትና ተጓዳኝ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንደተነሳ ያስታወቀው ዜብራ ራይድ የተሰኘ ድርጅት ሥራ ጀመረ፡፡ ዜብራ ራይድ በዘመናዊ የከተማ ትራንስፖርት፣ በበይነ መረብ ግብይት፣ በመኪና ኪራይ፣ ምርትና አገልግሎት በማጓጓዝ ሥራዎች ላይ የሚሠራ ዜብራ ዴሊቨሪ የተሰኘውን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያጠቃለለ ሥራ ላይ ይሠማራል ተብሏል፡፡

የዜብራ ራይድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ዲማ እንዳስረዱት፣ ከ2,000 በላይ ተሽከርካሪዎችን በስልክና በድረገጽ ጥሪ አማካይነት በጊዜያዊነት ወደ ትራንስፖርት አገልግሎት ያስገባል፡፡ በራሳቸው ተሽከርካሪዎች ወደ ትራንስፖርት አገልግሎት ሥርዓቱ ከሚካተቱት ከእነዚህ በተጓዳኝ፣ ከሦስት ወራት በኋላ ተጨማሪ 5,000 ተሽከርካሪዎችን ለማካተት ከአስመጪዎች ጋር ድርድር መጀመሩን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

ከትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ በበይነ መረብ ወይም በኦንላይን አማካይነት ከአሜሪካ፣ ከአውስትራሊያ እንዲሁም ከእስያ ፓስፊክ አገሮች የቀጥታ ግብይት መፈጸም የሚያስችል ሥርዓት መዘርግጋቱን የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያው ግዥ ለሚፈጽምባቸው ተሽከርካሪዎች ከአዋሽ ባንክ ብድር አገልግሎት እንዳገኘ ጠቅሶ፣ ተሽከርካሪዎቹን የሚረከቡ ግለሰቦችም የ30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም፣ የዜብራ ራይድ አሽከርካሪ መሆን የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ የአንድ ተሽከርካሪ ሙሉ የክፍያ ዋጋ 800,000 ብር ሲሆን፣ የ240,000 ብር ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸምና ቀሪው በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የግላቸው የሚያደርጉበት ሥርዓት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋና በባህር ዳር በቅርቡ የሚጀመር ሲሆን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኬንያ ናይሮቢ በወኪሎች አማካይነት በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡ አቶ ተስፋዬ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ የሥራ ዘርፍ ብዙ ጥናት የተደረገበት ሲሆን በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የትራንስፖርት ችግር ሊቀርፍ የሚችል ፕሮጀክት ነው፡፡ በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች አብዛኛዎቹ የመነሻ ታሪፋቸው 50 ብር ሲሆን፣ ዜብራ ራይድ በ35 ብር መነሻ ሒሳብ ወደ ሥራ እንደገባ አስታውቋል፡፡

 ዜብራ ራይድ በአዲስ አበባ የሚገነባው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት ከሚገኘው ገቢ አምስት በመቶ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከ5,000 በላይ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ሲጠበቅ፣ በቅድሚያ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ይገልጻሉ፡፡

አገልግሎቱ የሚቀርባቸው ተሽከርካሪዎች በላይ አብ ሞተርስን ጨምሮ ሌሎችም ከኩባንያው ጋር በአቅራቢነት ለመሥራት በሒደት ላይ እንደሚገኙ ሲገለጽ፣ ተሽከርካሪዎቹም ከአራት እስከ ሰባት ተሳፋሪ የመያዝ  አቅም እንደሚኖራቸው ተብራርቷል፡፡

የሱዙዚኪ እንዲሁም የግሎሪ ኩባንያዎች ሥሪት የሆኑ መኪኖች ለዜብራ ራይድ አገልግሎት ከተመረጡት መካከል ሲሆኑ፣ 2,000 ተሽከርካሪዎች ግን ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ የገቡት አገልግሎት ሰጪዎች በግል ተሽከርካሪዎቻቸው አማካይነት እንደሚሆን አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች